https://www.ethiopianreporter.com/139026

ዳዊት ታዬ

March 9, 2025

 የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባል አገሮች ውስጥ የሚገኙ ነጋዴ ሴቶችን ለማስተሳሰር ያለመ የኮሜሳ የንግድ ትርዒትና የቢዝነስ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን 6ኛው የኮሜሳ ነጋዴ ሴቶች የንግድ ትርዒትና የቢዝነስ ኮንፈረንስን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው የኮሜሳ አባል አገሮች ነፃ የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩና ይህም ውጤት እየመጣ ነው ተብሏል፡፡ የኮሜሳ ነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ስምረት ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት ኮሜሳ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ በንግድ አማካይነት በአባል አገሮች መካከል ቀጣናዊ ትስስር መፍጠር በመሆኑ በዚሁ አግባብ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህንን ትስስር ለመፍጠርም በኮሜሳ የተዘጋጁ የተለያዩ ስምምነቶች ያሉ በመሆኑ በዚሁ አግባብ አባል አገሮች ይህንን ስምምነት እየተቀበሉ የሚተገብራቸው ናቸው፡፡ ይህም ስምምነት አባል አገሮች ከቀረጥ ነፃና ከኮታ ነፃ በሆነ መንገድ ግብይት እያደረጉ እያስቻላቸው ነው፡፡

ለምሳሌ እንደ ዛምቢያ ያሉ አገሮች ረዥም መንገድ መሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ዛምቢያ ከምትዋሰናቸው ከስምንት አገሮች ውስጥ አራቱ የኮሜሳ አባል አገሮች ሲሆኑ ድንበራቸውን ከፍተው ያለ ቀረጥና ኮታ እየተገበያዩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ በገበያ አማካይነት ግብ ለመምታት የሚታሰበውን ቀጣናዊ ትስስር ከማረጋገጥ አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያመለክታልም ብለዋል፡፡ 

በኮሜሳ አማካይነት የተተገበሩ የነፃ ድንበር ቀጣናዎች አገሮች ተስማምተው የሚወስኗቸውን የምርት ዓይነቶች ከቀረጥ ነፃ የሚገበያበት ሁኔታ መፍጠር እንደመሆኑ ከነዚህ አንፃር ጥሩ ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡  እንዲህ ያለው የገበያ ሥርዓት መፈጠሩ ደግሞ በይበልጥ ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የገለጹት ወ/ሮ ስምረት ከቀረጥና ከኮታ ነፃ የሆነውን የግብይት ሥርዓት መጀመሩ አገሮች በፈጠሩት ግብይት ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ 80 በመቶ ወጣትና ሴቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከቀረጥና ኮታ ነፃ በሆነው ግብይት ውስጥ እየተሳተፉ አለመሆኑ ለምን? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ ስምረት ከኮታና ከቀረጥ ነፃ ግብይቱን ሁሉም አገሮች በእኩል ደረጃ እየተገበሩት እንዳልሆነ ገልጸው ከዚህ አንፃር አሁንም ብዙ መሠራት ያለበት ሥራ መኖሩን አልሸሸጉም፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥም ኮሜሳ የተለያዩ ፕሮግራሞች ቀርፆ እየሠራበት እንደሆነና ከኢትዮጵያ አኳያም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውም አክለዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 1 ቀን የሚካሄደውም የኮሜሳ የነጋዴ ሴቶች ቀጣናዊ የንግድ ትርዒትና ባዛር አንዱ ዓላማውም እዚህ ያሉ ነጋዴዎች ልምድ ወስደው ወደ ግብይት ትስስሩ እንዲገቡ ለማስቻል ነው፡፡ በተለይ ነጋዴ ሴቶችን ከሁሉም የኮሜሳ አባል አገሮች ሴት ነጋዴዎች ጋር በማገናኘት ትስስሩ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ማሳየት ነው ብለዋል፡፡ ስለ ቀጣናዊ ትስስር ግንዛቤ የሚፈጠርበት መድረክም ስለሚኖር ፖሊሲ አውጪዎች ይህ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚደረግ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአፍሪካ የእርስ በርስ ንግድ አራት በመቶ እንኳ አይሞላም እየተባለ ነውና ይህንን ቁጥር ከፍ ከማድረግ አንፃር የኮሜሳ ሚና ምንድነው? ለሚለው ጥያቄም ወ/ሮ ስምረት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ የንግድ ትስስሩ ወደሚፈለገው ደረጃ መድረሱ አይቀርም ይላሉ፡፡ ነፃ የንግድ ግንኙነት መፍጠር ብቻ ሳይሆን በሒደት በነፃነት የሰዎችን እንቅስቃሴ እስከመፍቀድ ያለ ቪዛ የሚንቀሳቀሱበትን ዕድል መፍጠር የሚል ዓላማ ያለው በመሆኑ ከዚህ አንፃር ብዙ ሥራ የሚቀርብ ቢሆንም ወደዚያ ለመድረስ ያስችላሉ የተባሉ ዝግጅቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከስምንቱ የኢኮኖሚ ዞኖች በርከት ያሉ አገሮችን የያዘው ኮሜሳ በመሆኑ የንግድ ትስስሩን ማስፋት የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ኢትዮጵያም እንደ አንድ አባል በዚህ ተጠቃሚ መሆን ችላለች የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

እንደ ኮሜሳ ያሉ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ከተቋቋሙ ነፃ ንግድ ዞኖች ሌላ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነውና የዚህ ቀጣና መፈጠር እንደ ኮሜሳ ካሉ ዞኖች ጋር የሚኖረው ግንኙነትን በተመለከተም ወ/ሮ ስምረት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የራሱ ሴክሬታሪያት ያለውና በአፍሪካ ዩኒየን አካማይነት የሚተገበር ነፃ ገበያ ቀጣና ነው፡፡ በራሱ እንደዚህ ያሉ ሪጅናል የሆኑ ቀጣናዎችን ፕሮሞት የሚያደርግ በመሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ አብረው ተናበው የሚሠሩ ጠቅሰው አካሄዳቸውና አፈጻጸማቸው በአብዛኛው ተቀራራቢ ነው ይላሉ፡፡ አገሮች በትልቁ ገበያ ከሚያደርጉት ከኮታና ከቀረጥ ነፃ ግብይት ባሻገር በራሳቸው በየአካባቢው ባሉት እንደ ኮሜሳ ዓይነት ሪጅናል አደረጃጀቶች የሚያደርጓቸው ነፃ ግብይቶች ለዛኛውም ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ኮሜሳን ከመሠረቱ አገሮች አንዷ ስትሆን ወቅታዊ ተሳትፎን በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ ዓመታዊ መዋጮችን በመክፈል የሰው ኃይል በማዋጣት ትልቅ አስተዋጽኦ አላት፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ከመተግበር አንፃርም የራሷን ሚና እየተጫወተች ነው ተብሏ፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ከሕዝብ ቁጥጥር አንፃር በቀጣናው ትልቅ አስተዋፕኦ ያላትና ገበያው በሰፋ ቁጥር ዋነኛ ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ እንደሚታሰብም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ‹‹A Thriving COMESA through Gender Responsive Regional Integration: Unlocking Opportunities in Green Investments, Value chains, Tourism and Mining›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የኮሜሳ ነጋዴ ሴቶች የንግድ ትርዒትና ቢዝነስ ኮንፈረንስ በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እንዲሁም በቅርቡ እንደ አዲስ የተመሠረተው ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ጋር በመተባበር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

በንግድ ትርዒቱና ቢዝነስ ኮንፈረንሱ የ21 የኮሜሳ አባል አገሮች ሥራ ፈጣሪ ሴችቶን አቅም በማጎልበት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የተገለጸ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ላይ ከ600 በላይ አጋር ድርጅቶች ይሳተፋሉ፡፡ 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ዴኤታ ወ/ሮ ሰሚን ውሃብረቢና ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ራሳቸውን ይበልጥ የሚያስተዋውቁበት ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ነው፡፡ የኮሜሳ የነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ሚስ ማውሬን ሱምቦዌ በበኩላቸው ሴቶችና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች በቀጣናው በንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ላይ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እየተወጡ እንዳልሆነና ለዚህም እንቅፋት ከሆኑ ምክንያቶች በዚህ ፕሮግራም ይዳሰሳል ብለዋል፡፡ በተለይ የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር፣ የገበያ እጥረትና ሥር የሰደደ ማኅበራዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ እነዚህንና መሰል እንቅፋቶችን በማስወገድ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ቀጣናዊና አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ትስስር ማጠናከርና የሥራ ዕድል አማራጮችን ማስፋፋት፣ የፋይናንስ ችግርን መቅረፍ እንዲሁም ሴቶችንና ወጣቶችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በማሳተፍ ለምርቶቻቸው የገበያ ዕድሎችን ማስፋፋት ላይ በአጀንዳነት ተይዘው በኮንፈረንሱ ውይይት እንደሚደረግባቸውም ገልጸዋል፡፡ 

የኮሜሳ ነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን የንግድ ትርዒትና ቢዝነስ ኮንፈረንስ በአፍሪካ ደረጃ ትልቁና ታሪካዊ የጋራ መድረክ መሆኑንና ዓላማውም የሥራ ፈጣሪ ነጋዴ ሴቶች ቁጥርና ሚናን በማሳደግ በቀጣናው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሆነ ታውቋል፡፡