ዜና
ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች 40 በመቶ የሚሆኑት ዓመታዊ ክፍያቸውን እንደማይከፍሉ ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: March 9, 2025

ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን ዓመታዊ ወጪ ከአኅጉሩ ውጭ ካሉ የአውሮፓና አሜሪካ ምንጮች በሚገኝ ገንዘብ ዓመታዊ ወጪውን የሚሸፍነው የአፍሪካ ኅብረት፣ 40 በመቶ የሚሆኑ አባል አገሮች ዓመታዊ የአባልነት ክፍያቸውን እንደማይከፍሉ ተጠቆመ፡፡

በኅብረቱ ድረ ገጽ ከሰሞኑ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኅብረቱ የሚያወጣቸውን ፕሮግራሞች፣ ዕቅዶችና ተግባራት በአባላት አገሮች የማይደገፉ በመሆናቸው፣ ተገማች፣ ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዳደማይመራና ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘቡ ለሌላ ዓላማ መዋሉን ጠንካራ ተጠያቂነት አለመኖሩ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የአባል አገሮቹ የኅብረቱን ዓመታዊ በጀት ለማቀድና በዕቅዱ ለመመራት ያላቸው ሚና ዝቅተኛ መሆኑን የገለጸው የኅብረቱ መረጃ፣ የፋይናንስ አመራር መዘርዝርና በተጠያቂነት መርሕ የሚመራበት ሥርዓት አለመኖሩን አስታውቋል፡፡

መረጃው እንደሚያሳየው ሕግና መመርያ፣ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ዘዴ እንደሌለውና ሀብት በምን ሁኔታና በምን መልኩ ሥራ ላይ መዋሉን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት የለውም ብሏል፡፡

የሚያወጣቸውን አጀንዳዎችና ዕቅዶች ለማስፈጸም ባለመቻሉ፣ ወቀሳ የሚቀርብበት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ ራሱን የሚችልበት ጠንካራ የሀብት ምንጭ በአኅጉሩ ውስጥ እንዲፈጥርና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል፡፡

ፖሊሲ ሴንተር ፎር ዘኒው ሳውዝ የተሰኘ ተቋም የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ፣ የኅብረቱ የፋይናንስ ምንጭ ከውጭ መሆኑ ተቋሙን ደካማ ማድረጉንና ራሱን ችሎ እንዳይንቀሳቀስ ስለማድረጉ አስቀምጧል፡፡

በዚህም ኅብረቱ ያስቀመጣቸውን የ2063 አጀንዳዎች ራሱን ችሎ መቆምና መፈጸም እንዳይችል ማድረጉን የገለጸው ይህ ተቋም፣ በአባል አገሮች ላይ 0.2 በመቶ የገቢ ምርት ላይ በሚጣልበት ሀብት ለማመንጨት የወጣውንና በሩዋንዳ የተፈረመውን የኪጋሊ ስምምነት፣ ከኅብረቱ ቢያንስ 30 አገሮች መፈጸም አለመቻላቸውን ያነሳል፡፡ አባል አገሮች ክፍያ የሚከፍሉት ወቅቱን በጠበቀ መልኩ አለመሆኑንም የአፍሪካ ኅብረት መረጃ ያስረዳል፡፡