
ኪንና ባህል ከቁጫ የሚቀዳው ባህላዊ ምግብና ሥሪቱ
ቀን: March 9, 2025
ቁጫ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን የሚገኝ ብሔረሰብ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የራሱ ታሪክ ባህልና ማንነት ያለው መሆኑ ይነገራል፡፡
የሥነ ሰብ (አንትሮፖሎጂ) ባለሙያው ሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ አይዛ የቁጫ ሕዝብ ታሪክ እስከ 2007 ዓ.ም. በሚሉት መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ‹‹ቁጫ›› የሚለው ቃል አካባቢውን፣ ሕዝቡንና ቋንቋውን የሚወክል ነው፡፡ በንጉሣዊው፣ በወታደራዊ [በሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ] እና በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊው ዘመነ መንግሥታት አካባቢው ‹‹ቁጫ ወረዳ›› እየተባለ መጠቀሱ፣ የነዋሪውን ሕዝብም ሆነ የመሬቱን መጠሪያ የሚያመለክት እንደሆነም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

የእኩለ ሌሊት ወገግታ፡- የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተሰኘ መጽሐፋቸው ወንድዬ ዓሊ ስለ ቁጫ መልክዓ ምድር እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡
‹‹ቁጫ በወንዞች የተከበበች አገር ናት፡፡ በሰሜን ከኦሞ ወንዝ፣ በምዕራብ ከማዜ ወንዝ፣ በምሥራቅ በደሜና ጎገራ ወንዞች፣ በደቡብ ከጋሞ ትዋሰናለች፡፡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ትንሽ፣ ነገር ግን ጠንካራ ሥርወ መንግሥት መሥርታ እንደነበር አፈ ታሪካዊ ምንጮች ያረጋግጣሉ፡፡››
የመጀመርያ እትሙን በ2008 ዓ.ም. ያደረገው የቁጫ ሕዝብ ታሪክ መጽሐፉ በአራት ምዕራፎች ማለትም የቁጫ አጠቃላይ ገጽታ፣ ፖለቲካዊ ታሪክ፣ ማኅበራዊ ታሪክ እና የኢኮኖሚ ታሪክ በሚል የተደራጀ ነው፡፡
የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የሆነው የቁጫ ማኅበረሰብ ካሉትና ጎልተው ከሚታወቁት መገለጫዎች መካከል ባህላዊ የምግብ ዓይነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህንም በመጽሐፉ ምዕራፍ ሦት በማኅበራዊ ታሪክ ሥር ቀርበዋል፡፡
በቁጫ የአመጋገብ ባህል ከሌላው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ እምብዛም ልዩነት የሌላቸው የምግብ አሠራሮችና የምግብ ዓይነቶች እንደሚገኙ የገለጹት ጸሐፊው አቶ ሀብታሙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቁጫና በአካባቢው ብቻ የሚዘወተሩ የምግብ አዘገጃጀትና የምግብ ዓይነቶችን በተለይ በመጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፡፡
‹‹ቁጫ በአብዛኛው የሥራ ሥርና ተዛማጅ የእህል ውጤቶችን ይመገባል፡፡ ከእነዚህም ዋነኞቹ እንሰት፣ ቦዬ፣ ጎደሬ፣ ካሳቫ ማለትም ሚታ ቦይያ (mitta boyyiyaa) ቡንዱቡቺያ (bundubuchiyaa) ማለትም በዛፍ ላይ ተንጠልጣይ የቦዬ ዝርያ፣ ደለኳ (dalakkuwaa) ማለትም ጎደሬ የሚመስና የድንች ዝርያ የሆነ ቀጫጭን ሥራ ሥር፣ ድቡልቡል ድንች፣ ዱባ፣ ስኳር ድንችና የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ከእንሰት የተለያዩ ምግቦች ይዘጋጃሉ፡፡ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ ኡንጫ ኮሴታ (unca koosettaa)፣ ኢቲማ ኮሴታ (itima Koosettaa)፣ ኢቲማ ሼንዴራ (itima shenderaa) እና ጊንዴታ (gindetta) ናቸው፡፡
‹‹ኢንጫ ኮሴታ የሚሠራው ከቆጮ ሲሆን፣ ቆጮው በመጀመሪያ ከተጠቀለለበት የእንሰት ቅጠል ይፈታና በትልቅ ቆጮ መክተፊያ ቢላዋ እጅግ ልሞ ቃጫው እስኪጠፋ ድረስ ገበቴ ላይ ይከተፋል፡፡ ከዚያም በሰማ የሸክላ ምጣድ ላይ ይደረግና እየታመሰ በሙቀት እንዲበስል ይደረጋል፡፡ መብሰሉ ከተረጋገጠ በኋላ በትልቅ የሸክላ ምጣድ ጎድጓዳ ሳህን ማለትም ኬሪያ (keriyaa) ውስጥ የቅቤ፣ የወተትና የጨው ውህድ ይዘጋጅና ምጣዱ ላይ የበሰለው የላመ የቆጮ ዱቄት ይጨመርበታል፡፡ ከዚያም ቆጮው በሚገባ ይዋሃዳል፡፡ ውጤቱም ኡንጫ ኮሴታ ይሆናል፡፡ ይህ ምግብ የሚበላው በአብዛኛው በወተት ነው፡፡ ኢቲማ ኮሴታ ከኡንጫ ኮሌታ ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ሆኖ ልዩነታቸው ዱቄቱ ላይ ብቻ ነው፡፡ ማለትም ኡንጫ ኮሴታ የሚዘጋጀው ከተከተፈ የቆጮ ዱቄት ሲሆን ኢቲማ ኮሴታ ግን ከቡላ ነው፡፡
‹‹ኢቲማ ሼንዴራ ማለት የቡላ ገንፎ ሲሆን፣ የሚዘጋጀውም በሌላ መልኩ ከእንሰት ግንድ ለየትና ረዘም ባለ ሒደት ነው፡፡ ቅቤ የተጨመረበት ኢቲማ ሼንዴራ በአብዛኛው ለአራስ ሴት ይቀርባል፡፡ እንዲሁም ኢቲማ ኮሴታ በቁጫ አካባቢ ተወዳጅ የምግብ ዓይነት ነው፡፡ አዘገጃጀቱም ከኡንጫ ኮሴታ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ጊንዴታ የሚለው ቃል ትርጉሙ አንድን ዱቄት ከሌላው ጋር መቀላቀል ማለት ነው፡፡ ጊንዴታ ወይም ኡንጫ ጊንዴታ በከፊል ቆጮ፣ በከፊል የበቆሎ ወይም የሌላ እህል ዱቄት ገብቶበት የሚጋገር ወፈር ያለ ቂጣ ማለት ነው፡፡ ይህ ጊንዴታ የሚበላው በአብዛኛው በወተት ነው፡፡
‹‹በቁጫ ለምግብነት ከሚውሉት የጓሮ አትክልት አንዱ ዱባ ማለት ሌሌሂያ (lelleiehiyaa) ነው፡፡ ዱባ ተሰነጣጥቆ ፍሬዎቹና ፍሬዎቹን የከበበው ስብ የዱባው ውስጠኛ ክፍል ወይም ወልጓ (wolguwaa) ተፈልቅቆ ይወጣና ዱባው ይቀቀላል፡፡ ተቀቅሎ ሲወጣ የተቀቀለበት ውኃ የዱባውን ውስጠኛው ክፍል በመጠኑ ሊያጠቁረው ስለሚችል ያ በውኃው የጠቆረው ክፍል በቢላ ተወግዶ የዱባው የላይኛው ቅርፊት ይላጥና በጥሩ ሁኔታ በተቀመመ በርበሬ ማለትም ዳታ በምበሪያ (daatta bemberiya) ይበላል፡፡ የዱባ ፍሬዎች ከዱባ ከወጡ በኋላ ከዱባው ስስ አካል ወይም ወልጓ በሚባል ተለይተው ፀሐይ ላይ ተሰጥተው በደንብ እንዲደርቁ ይደረጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ተፈትገው ሊቆሉ ከሚችሉ የተለያዩ ጥራጥሬዎች ጋር ተቀላቅለው ይቆሉና ለቆሎ ማጣፈጫነት ይጠቅማሉ፡፡
‹‹ዱባዎች በቁጫ ለምግብነት የሚያገለግሉና ለምግብነት የማያገለግሉ በሚል በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ ቀለማቸው ቢጫ የሆኑ ዱባዎች ጥሩ ጣዕም ያላቸውና ለምግብነት የሚያገለግሉ ሲሆኑ፣ ቀለማቸው ነጭ የሆኑት ዱባዎች ጥሩ ጣዕም የሌላቸው፣ ነገር ግን ተከታትፈው ለከብቶች የሚሰጡ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ የእነዚህ ዱባዎችን ስም ፓራ ሌሌሄ (para lellehe) ማለትም ‹‹የፈረስ ዱባ›› ወይም ‹‹የፈረስ ቀለብ›› ይባላል፡፡
‹‹ጎደሬ ማለትም ቦይና (boynaa) ወይም በእንግሊዝኛ ታሮ (taro) ተቀቅሎ በሁለት ዓይነት መንገድ ይበላል፡፡ የመጀመሪያው ተልጦ ወይም ሳይላጥ ይቀቀልና የሚበላበት ነው፡፡ ከእነቅርፊቱ የሚበስል ከሆነ በሚበላበት ጊዜ ይጣላል፡፡ ነገር ግን ጥሬው መጀመሪያ ተልጦም ሊቀቀል ይችላል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ጎደሬው ከተቀቀለ በኋላ ይፈረፈርና በሚገባ ከተለነቀጠ በኋላ በበርበሬ ይበላል፡፡ ይህ የጎደሬ ፍርፍር ጨዲያ (cadhiyaa) ይባላል፡፡ በቁጫ ለበርካታ ምግቦች ማባያነት የሚያገለግል ግሩም የሆነ በርበሬ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ይህ በርበሬ ሰዎች በምበሪያ (sawo bambariyaa) ይበላል:፡ አሠራሩም እንደሚከተለው ነው:: ነጭ ሽንኩርት፣ በሶቢላ፣ ድምብላልና ሚጥሚጣ አንድ ላይ ተለንቅጠው ይዋሃዳሉ፡፡ ጨውና ቅቤ ተጨምሮበት እሳት ላይ ሞቅ ይደረጋል፡፡ አንዳንዴ ወተትም ይገባበታል፡፡
‹‹ቦዬ በቁጫ እጅግ በጣም ተወዳጅ ምግብ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች ተዘጋጅቶ ይበላል፡፡ ጥሬው ቦዬ በቢላዋ ይላጥና ከታጠበ በኋላ ተቆራርጦ ይቀቀላል፡፡ ከዚያም በወተት እያጣጣሙ ይበሉታል፡፡ ከመቀቀል በተጨማሪ ቦዬ አንዳንድ ጊዜ ቀጥታ በእሳት ተጠብሶ ሊበላም ይችላል፡፡ በዘመን መለወጫ ጊዜ ደግሞ ግሩም ጣዕም ያለውና ከኮቦዬ የሚሠራው ተወዳጅ ምግብ ፒጫታ (picaataa) ይባላል፡፡
‹‹ፒጫታ የሚሠራው ተቀቅሎ ከበሰለ ቦዬ ሲሆን፣ ለፒጫታ የሚፈለገው ሁሉም የቦዬ ዓይነት ሳይሆን ሀጢዬ ቦዬ (haxiye boye) የተሰኘውና ሲበላ ጠፈፍ ያለው የቦዬ ዓይነት ነው፡፡ የበሰለው ቦዬ ገበቴ ላይ ይፈረፈርና በወተት፣ በቅቤና ጣዕም ባለው ሰዎ በምበሬ ውስጥ ተነክሮ ፒጫታ ሆኖ ይዘጋጃል፡፡ ፒጫታ የሚበላው ሞቂያ (mooqiyaa) በሚባለው ከቀንድ የሚሠራ ረዥም ባህላዊ ማንኪያ ነው፡፡