
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማኅበር ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን አምስተኛ ዓመታዊ የተዋልዶ ጤና ጉባዔውን ባደረገበት ወቅት
ማኅበራዊ አገር በቀል መፍትሔ የሚሹት ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች
ቀን: March 9, 2025
በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኩል ይሰጥ የነበረው ዕርዳታ በመቋረጡ በርካታ ድርጅቶች ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ በመቋረጡ ሠራተኞችን ለመቀነስና ይሰጡት የነበረውን አገልግሎት እስከ ማቋረጥ መድረሳቸውን ያስረዳሉ፡፡
የጤናው ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ደግሞ የበለጠ ተጎጂ በመሆናቸው አፋጣኝ የመፍትሔ አማራጮችን የሚሹ ስለመሆናቸው የዘርፉ ተዋናዮች ያስረዳሉ፡፡
የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማኅበር ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን ‹‹ከዓለም ወደ አካባቢ›› (from giobal to local) በሚል መሪ ቃል አምስተኛ ዓመታዊ የተዋልዶ ጤና ጉባዔውን የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲያካሂድ የተነሳውም ድርጅቶቹ ለችግር መጋለጣቸው ነው፡፡
በዚሁ ጉባዔ ላይ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን፣ በተለይ በጤናው ዘርፍ የሚሠሩት በዩኤስኤአይዲ በኩል ይደረግላቸው የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ፣ ከፍተኛ ጉዳትን እያስተናገዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
አቶ የማነ ጉዑሽ ሴቭ ዩር ሆሊ ላንድ (ቅድስት ምድርህን አድን) የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡
ድርጅታቸው ወጣቶችና እናቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ የማነ፣ በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች መዳረሻውን በማድረግ ላለፉት 23 ዓመታት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችና አሁንም ያለው የሰላም እጦት ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው፣ በጦርነቱ የሚፈርሱ የጤናና የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግም አስቸጋሪ እንደሆነ ያክላሉ፡፡
የጤናና የትምህርት ተቋማት በጦርነት ወቅት ቀድመው ከሚጎዱ ተቋማት እንደሚመደቡ፣ እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው ለመውለድ እንደተቸገሩና መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለማግኘትም ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ትምህርት የማይታሰብ ነው›› ያሉት አቶ የማነ ተማሪዎች በወቅቱ ወደ ትምህርት ቤት ካልሄዱ ለፆታዊ ጥቃት እንደሚጋለጡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንደሚስፋፋና ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዲውሉ በር የሚከፍት ስለመሆኑ ያክላሉ፡፡
እንደ ዩክሬን፣ ሶሪያና ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በመበራከታቸው ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ ለጋሽ ድርጅቶች ፊታቸውን ካዞሩ ሰነባብተዋል ያሉት አቶ የማነ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ያደርገው የነበረውን ድጋፍ በማቋረጡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ ተጎጂ መሆናቸውን፣ በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ በርካታ ሠራተኞችም የችግሩ ሰለባ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
በተለይ የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መቋረጥ ድንገተኛና ያልታሰበበት ነው ያሉት አቶ የማነ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግሥትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ዋና ዋና ችግሮችን በጥናት በመለየት አፋጣኝ መፍትሔን ማበጀት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከሰቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባሻገር መንግሥትና የልማት ድርጅቶችም ቆም ብለው ሊያስቡበት እንደሚገባ፣ ከተረጂነት ዕሳቤ በመውጣት በራስ መንቀሳቀስ እንዲቻል በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አስፈላጊ እንደሆነ አክለዋል፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በሥነ ተዋልዶ ጤናና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ዘርፎች ላይ ሰፊ አገልግሎትና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ከበደ ናቸው፡፡
ዩኤስኤአይዲ በጤናው ዘርፍ ይሰጥ የነበረው ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በማቋረጡ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ችግር ውስጥ መሆናቸውን አቶ አበበም ጠቅሰዋል፡፡
በመሆነም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ሆነው የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ማጥናት፣ ተቀራርቦ በመወያየት በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን በትኩረት መመልከት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹ለችግሩ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ በምናስብበት ጊዜ ከውጭ ዕርዳታዎች ጋር መንጠልጠል የለብንም›› የሚሉት አቶ አበበ፣ ለችግሮች አገር በቀልና ዘላቂ መፍትሔዎችን በጋራ ማፈላለግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምን ዓይነት ፕሮግራሞ መተግበር አለባቸው? የሚለው ሐሳብ መታየት አለበት የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በአሁኑ ወቅት በተለይ የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ላይ ችግር የፈጠረው የውጭ ድጋፍን መሠረት አድርገው በነፃ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች መቋረጣቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ አበበ ገለጻ፣ ቀደም ሲል ለማህበረሰቡ በነፃ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ክፍያ መሰጠት አለባቸው ወይስ በነበሩበት መቀጠል አለባቸው? የሚለው ጉዳይ ብዙ ጥናት የሚፈልግና መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ ነው፡፡
‹‹እናቶች ለወሊድ ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ በነፃ ያገኙት የነበረውን አገልግሎት ዛሬ ላይ በነፃ ለመገልገል የማይችሉበት ሁኔታ ሊመጣ ይችላል፤›› በማለትም ጉዳዩ ችግሩ በደንብ እንዲታይ የሚያስገድድ ስለመሆኑ አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል በጤናው ዘርፍ የተጋረጠውን ችግር ለማቃለል እንደ መፍትሔ የተቀመጠው አማራጭ፣ ከትንባሆና ከአልኮል መጠጦች የሚሰበሰበውን ታክስ ለጤናው ዘርፍ ማዋል ሲሆን ይህም በመንግሥት በኩል ቃል መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተግባር ላይ ለመዋል ብዙ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ የተናገሩት አቶ አበበ፣ ምን ያህል ታክስ ተሰበሰበ? ምን ያህሉስ ለጤናው ዘርፍ ገቢ ይደረግ የሚሉትና ሎሎች ከገንዘብ ሚኒስቴርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስፋት ውይይት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
‹‹ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ተቋረጡ ማለት የእናቶችና የሕፃናት ሞት በእጅጉ ጨመረ ማለት ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ መንግሥት ራሱን በመፈተሽና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ሊፈጠሩ የሚችሉ ከፍተቶችን ከወዲሁ መድፈን ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶች የጤናውን ዘርፍ በእጅጉ እንደጎዱት፣ ከማኅበረሰብ በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎችን ሥነ ልቦና እየጎዳ ስለመሆኑ፣ የጤና ባለሙያዎችም ምቹ ሁኔታ እንዲያገኙና እንዲረጋጉ ማድረግ እንደሚገባ ያክላሉ፡፡
በዓመት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዘ አገልግሎትን እንደሚሰጥ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር በበኩሉ የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መቋረጥ ከፍተኛ ችግር እንደደቀነበት ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ክሊኒካል አገልግሎት ማናጀር ጴጥሮስ ጌቼሬ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በዩኤስኤአይዲ መቋረጥ ይሠሩዋቸው የነበሩ አራት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተዘግተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በመዘጋታቸው ደግሞ ለማህበሩ ፈንድ ይደረግ የነበረ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡ በርካታ የድርጅቱ ሠራተኞችም ከሥራ እንደሚሰናበቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ድርጅቶቹ በአማካይ ከ20 እስከ 70 የሚደርሱ ሠራተኞችን ይዞ እንደነበር፣ ሠራተኞቹ ይሰጡት የነበረው አገልግሎት አብሮ እንደተቋረጠ፣ በተቋሙ ላይ የደረሰው ጉዳት በፐርሰንት ሲሰላ 50 በመቶ መሆኑንና ወጣቶች የከፋ ችግር ወስጥ ሳይገቡ የራሳቸው የሆነ የገቢ ምንጭ ለማሰባሰብ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡