March 9, 2025

ርዕሰ አንቀጽ

መሰንበቻውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሆሚቾ ጥይት ፋብሪካ ጉብኝታቸው ባደረጉት ንግግር፣ ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ ተተኳሽ ጥይቶችን የማምረት ሙከራዎች ቢኖሩም ከሦስት ዓመታት በፊት ድረስ ከውጭ ስታስገባ እንደነበርና አሁን ግን እዚሁ በማምረት ለውጭ የመላክ አቅም መገንባቱን ገልጸዋል፡፡ ለበርካታ አገሮች ጥይቶች ለመሸጥ ስምምነት መፈጸሙን፣ በሦስት ወራት ውስጥ 30 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ መገኘቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹…ክላሽና ስናይፐርን ጨምሮ ሌሎች መሣሪያዎችን እናመርታለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ከመግዛት ወጥተን ለአገሮች ለመሸጥ በመብቃታችንና ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ይህ አቅም ተገንብቶ በማየቴ ከፍተኛ ክብርና ደስታ ተሰምቶኛል…›› ብለው፣ ‹‹…የመከላከያ ኢንዱስትሪ ብቻ ያመጣው ዕድገት በጣም ተስፋ ሰጪና ኢትዮጵያ በእውነትም እያንሠራራች መሆኗን ማሳያ ነው…›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ‹‹አገር ሁልጊዜም ቢሆን ማምረት የሚገባት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነሱም ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት ናቸው፡፡ እነዚህን በበቂ ሁኔታ የማታመርት አገር ለማንኛውም አደጋ ትጋለጣለች…›› ያሉት ግን አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለችው ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ታዳጊና ወጣት ስለሆነ ሌሎች ዘርፎችም ትኩረት ይሻሉ፡፡ ወጣቱን ኃይል ግብርና ውስጥ አጥሮ ማኖር ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ይሸጋገራል ሲባል፣ ብዙኃኑ ወጣቶች ትምህርት ቤት ገብተው የቴክኖሎጂ ዕውቀት መገብየት ይኖርባቸዋል፡፡ የተቀቀሩት ደግሞ በማዕድናት ፍለጋና ልማት፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎችም በስፋት መሰማራት አለባቸው፡፡ የኢንዱስትሪው ሽግግር የሚቀላጠፈው በተማረ የሰው ኃይል በመሆኑ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ በተጨማሪም በያሉበት አካባቢ ያለውን የአርብቶ አደርና የእርሻ ማኅበረሰብ ማገዝ አለባቸው፡፡ በተለይ ድርቅ በተደጋጋሚ የሚጎበኛቸው አካባቢዎች ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ለድርቅ የማይበገር ማኅበረሰብ መፍጠር ካልቻሉ ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ ይቆጠራሉ፡፡ ከመከላከያ ኢንዱስትሪ በተጨማሪ መንግሥት ለሌሎች ዘርፎችም ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበትን ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ ዕምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ ዕድልና ተስፋ ያላት አገር ግን ፈተናዋ በዝቶ የግጭት፣ የድህነት፣ የተረጅነትና የተስፋ ቆራጭነት አባዜዎች ሊለቋት አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚመነጩት ከታሪኳና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካሉት ውጣ ውረዶች ጋር ቢሆንም፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ከድጡ ወደ ማጡ እያንሸራተቷት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የኢኮኖሚ መንገዳገድ፣ የምግብ ዋስትና ዕጦት፣ የተለያዩ ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስና መስፋፋት፣ እንዲሁም ከትምህርትና ከጤና ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች መበራከት በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎችን ያሳስቧቸዋል፡፡

ዓለም በሁሉም መስኮች በፍጥነትና በቅፅበት እየተለወጠች ነው፡፡ በፈጣን ግስጋሴ ውስጥ ካለችው ዓለም ጋር ቢቻል እኩል ካልሆነ እግር በእግር መከታተል፣ ካልተቻለ በሁሉም ዘርፎች ያሉ ፉክክሮችን ተቋቁሞ ካሰቡበት ለመድረስ ያዳግታል፡፡ ዘመን አፈራሽ ዕውቀቶችን በመቅሰም ከጊዜው ጋር የሚራመዱ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምም ሆነ፣ እንዲሁም በራስ አቅም አምርቶ የጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን የሚቻለው በሁሉም ዘርፎች ለዘመኑ የሚመጥን ቁመና ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በውትድርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርትና በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ለመሆን ዘመኑን የሚመጥን አቅም መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁሉም መስኮች ጥራት ያለው ዕውቀትና ክህሎት ማዳበር የግድ ይላል፡፡ ዓለም በዕውቀትና በቴክኖሎጂ በፈጣን ግስጋሴ ላይ ሆኖ ወደፊት ሲመነጠቅ፣ ሁለገብ ዕውቀቶችን በመታጠቅ ራስን ለመቻል መነሳት የግድ ነው፡፡

ሌላው ተጠቃሽ ችግር በምግብ ራስን አለመቻል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያን በምግብ ራሷን እንዳትችል ካስቸገሯት ምክንያቶች መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ፣ ግጭትና የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆን ናቸው፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦች ቢቀርቡም፣ በየጊዜው የተለዋወጡ መንግሥታት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ለምሳሌ ድርቅን ለመቌቌም፣ ጦሙን የሚያድር ሰፊ መሬት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ለማረስ፣ አገሪቱ አሉኝ የምትላቸውን የዳበረ ክህሎትና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ለመጠቀም፣ እንዲሁም በዘርፉ የዳበሩ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ፍላጎት ማጣትና የመሳሰሉ እንቅፋቶች ሲጠቀሱ ኖረዋል፡፡ ከላይ ለቀረቡት ምክረ ሐሳቦች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በቂ ሀብት መድቦ ኢንቨስት ማድረግ ቢቻል፣ በምግብ ራስን መቻል ከመፈክር አልፎ በተግባር እንደሚረጋገጥ የብዙዎቹ እምነት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይደረጋሉ ከሚባሉ ጥረቶች ጎን ለጎን መንግሥት ከድህነት አዘቅት ውስጥ ሊያወጡ የሚያስችሉ የተለያዩ አማራጮችን መቃኘት ይጠበቅበታል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት የመጀመሪያው ትኩረት መሆን ያለበት ግብርና ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በመጠቀም የተትረፈረፈ ምርት ማስገኘት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ በባለሙያዎች ዕገዛ እንደ የመስኖ እርሻ፣ ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ዘሮች፣ የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ፀረ አረሞችን በስፋት ሥራ ላይ ማዋል ይጠቀሳሉ፡፡ በአዋጭ ፖሊሲ የሚመሩ የግብርና ሥራዎች በሙሉ አቅም ተግባራዊ ሲደረጉ በምግብ ራስን ከመቻል ታልፎ ለአርሶ አደሮች ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የእሴትና የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማጠናከር፣ የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበሪያዎችና ለገበያ እንዲደርሱ በማድረግ ከፍተኛ ገቢና ሥራ መፍጠር ያስችላል፡፡ ከድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት ግን ለሁሉም ዘርፎች እኩል ትኩረት ይሰጥ!