
March 9, 2025

አሻግሬ ዘውዱ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የምግብና የሥነ ምግብ ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምግብና በሥነ ምግብ ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪነት፣ በአስተማሪነት፣ በረዳት ፕሮፌሰርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ አሁን በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከአማካሪያቸው ጋር በመሆን በሠሩት የጥናት ውጤት የኢትዮጵያ እንጀራ ሳይሻግት ለ12 ቀናት እንዲቆይ በማስቻል እንጀራ ላኪዎችን ከብክነትና ኪሳራ ታድገዋል፡፡ ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ በምግብ ደኅንነት ላይ ከ60 በላይ ጥናቶች ከተማሪዎቻቸውና ከአጋሮቻቸው ጋር ሠርተዋል፡፡ ለምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ባለሙያዎች የጨው ማበልፀግ ዘዴዎችን እንዲለማመዱ ማስቻል፣ የአፍላቶክሲን ምርምር እንዲጀመር ማድረግ፣ ዓምና ይፋ የሆነውን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ማስተባበር፣ መንግሥትን በፖሊሲና ስትራቴጂ ማገዝና በቅርቡ በግብርና ሚኒስቴር ይፋ የሆነው የግብርና ምርቶች ጥራት ደኅንነት ስትራቴጂ ከሠሯቸው ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያን የምግብ ደኅንነት ለማስጠበቅ ራሱን የቻለ ባለሥልጣን ሊቋቋም ይገባልና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይስሙኝ ሲሉም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነት ዙሪያ ከምሕረት ሞገስ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡
ሪፖርተር፡- በምግብ ደኅንነት ዙሪያ የተለየ ትኩረት አድርገው ላለፉት አሥር ዓመታት በመሥራትዎ የምግብ ደኅንነት እንዴት ይገለጻል? የምግብ ዋስትና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እንዴት ማጣጣም ይቻላል?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- የምግብ ደኅንነት ጥያቄን ከአሥር ዓመታት በፊት ስናነሳ የምግብ ደኅንነት ጥያቄ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ነው ብለው የሚያስቡ ነበሩ፡፡ የምትለው፣ የምታልመው፣ ስለጥራትና ደኅንነት የምታነሳው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስላልተገነዘብክ ነው የሚሉኝም ነበሩ፡፡ አንድ ሰው የምግብ ዋስትናው ተረጋግጧል የሚባለው በአራት መገለጫዎች ነው፡፡ አንደኛው ምግብ በበቂ ሁኔታ አለ ወይ? ምርታማነት አለ ወይ? የሚለው ነው፡፡ አገራችን ግብርና አላት፣ አምርታ ኅብረተሰቡን መመገብ አለባት፡፡ ስለዚህ ምርታማነት መኖሩ ይታያል፡፡ ምርታማነት ከሌለ ተገዝቶ ይመጣል፡፡ መግዛት ካልተቻለ ደግሞ ለዕርዳታ መዳረግ ይከተላል፡፡ ስለዚህ በየትም በኩል ምርቱ ሊኖር ይገባል፡፡ ቀጥሎ የምናየው ተደራሽነት ነው፡፡ ምርታማነት ኖሮ ገንዘቡ ላይኖርና የበይ ተመልካች ሊኮን ይችላል፡፡ አቅርቦት ኖረ ማለት ይገኛል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በሚከፈለውና በገቢው ልክ በፍትሐዊነት ያገኛል ወይ የሚለው ነው፡፡ ሦስተኛው የምግብ ደኅንነት ውስጥ የሚካተተው ደግሞ ጤንነቱ ነው፡፡ ዩቲሊቲ እንለዋለን፡፡ እኛ ጤነኛ ያልሆነ ምግብ ምግብ፣ አይደለም እንላለን፡፡ በሳይንስ አንድ ሰው ምግብ በላ የሚባለውም ጤነኛ ያልሆነ ምግብ በልቶ አይደለም፡፡ ጤነኛ የሆነና ንጥረ ነገሩ የተጠበቀ ምግብ ሲበላም ነው የምግብ ዋስትናው ተጠበቀ የምንለው፡፡ አራተኛውና እያስደነገጠን ያለው ዘላቂነቱ ነው፡፡ ምግቡ አለ፣ ተደራሽነቱ አለ፣ ጤነኛ ነው ብለን ዘላቂ ነው ወይ? እንላለን፡፡ ይህን ስናይ ሰዎች ቁርስ አይዘሉም ወይ? ምሳ ወይም እራት አይዘሉም ወይ? አንድ ሰው በቀን የሚፈለገውን 2,200 ካሎሪ ያገኛል ወይ? ካሎሪው ቢሟላ እንኳን ቫይታሚንና ሚኒራል በበቂ ሁኔታ ያገኛል ወይ? ደኅንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ ነው ወይ? በሽታ የለበትም ወይ? የበላው ካንሰር አያስይዘውም? ኩላሊቱን አይጎዳውም? ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡
የምግብ ዋስትና ጉዳይን ስናነሳ የምግብ ደኅንነት ውስጡ እንዳለ ግንዛቤ እንዲያዝ እፈልጋለሁ፡፡ ብዙ ሰው የምግብ ዋስትና መጀመሪያ በኋላ ደግሞ የምግብ ደኅንነት የሚመጣ ይመስለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ትርጓሜ ግን የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠው ምግቡ ደኅንነቱ ሲጠበቅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከኅብረተሰቡ ጋር ልንግባባ ይገባል፡፡ ስለምግብ ዋስትና ስናወራ ደኅንነቱን ሳናስጠብቅ ከሆነ አይሆንም፡፡ እዚህ ላይ የምግብ ሉዓላዊነትም ይነሳል፡፡ የምግብ ዋስትናችንን አምርተን፣ ገዝተን ወይም በዕርዳታ አግኝተን ብናሟላውም ዕርዳታ በገጽታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያመጣብን ነው፡፡ ዕርዳታ የሚቀበል ሰው በራሱ ማሰብ አይችልም፡፡ በተሰጠው ልክ ነው የሚያስበው፡፡ ስለሆነም በስንዴና በሌሎችም ልማት ሉዓላዊነት ያስፈልገናል፡፡ ይህንን ስናረጋግጥ ክፍተት በመጣና ዕርዳታ በተቋረጠ ቁጥር አንደነግጥም፡፡ ለአብነት የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ለ90 ቀናት መቋረጥ ሁላችንንም አስደንግጦናል፡፡ ብዙ ሰዎች ዕርዳታ ተቋርጦባቸው ደንግጠዋል፡፡ እንዲህ መሆን ያለብን አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ወደ ሉዓላዊነት ለመሄድ በስንዴ የጀመረው ልማት እንዳለ ሆኖ፣ ከውጭ የምናስመጣቸውን ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎችም በአገር ውስጥ የምናመርትበትን ሁኔታ ማጎልበት አለበት፡፡ መጀመሪያ ዋስትናውን አረጋግጠን በቀጣይ ወደ ሉዓላዊነት መምጣት ይገባናል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን እንዴት ሊሆን ይችላል?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- ይህንን በሥራ ነው የምናመጣው፡፡ በስንዴ የተሠራ ሥራ አለ፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አለ፡፡ ይህ አቅማችንን ሲያጠናክር ማዳበሪያውንም ሆነ ሌሎች ግብዓቶች አምርተን በራሳችን ሕግና ደንብ ማሰብ፣ ማምረት፣ መኖር፣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ መላቀቅና የጂኦ ፖለቲካ ተፅዕኖን ማስቀረት እንችላለን፡፡ የሁሉም ሰው ትግል የተሻለ የምግብ ደረጃ ላይ ለመድረስ ነው፡፡ አንዴ ከመብላት ወደ ሁለት ከዚያም ወደ ሦስትና ወደ ቅንጦት መሄድ ነው የሰዎች ፍላጎት፡፡ ቅኝ ገዥዎችም ቢሆኑ ምግብ በበቂ ማግኘት የሚያስችል ምርት ለማግኘትና ለመመገብ የሚያደርጉት ትግል ነው፡፡ አገራችንም ከዚህ ትግል የፀዳች ስላልሆነች የምግብ ሉዓላዊንትን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለምግብ ዋስትናና ደኅንነት በዘረዘሩልን መሠረት ኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ ትገኛለች? የሠራችሁት ጥናት ካለ?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና ምን ደረጃ ነች ስንል? የሄደችባቸው ርቀቶች ቢኖሩም፣ አሁንም 15.8 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ ጠባቂ ነው፡፡ የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ሲቋረጥ የደነገጥነውም ለዚህ ነው፡፡ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቂ ምግብ አያገኝም፣ ዕርዳታ ይፈልጋል፡፡ ሲኖር የነበረውም መንግሥት በሸፈነለት ብቻ ሳይሆን በዕርዳታ ነው፡፡ ስለዚህ ለምግብ ዋስትና እየሠራናቸው ያሉ ሥራዎች ብዙ ቢሆኑም፣ በዚያው ልክ ግን ሰውን በበቂ ለመመገብ ምርታማነትን መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንደ አገር ብቻ ሳይሆን እንደ ዓለምም ነው፡፡ ፋኦ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጥናት አሁን ባለው ሁኔታ እየተመረተ ባለው ላይ ሦስት እጥፍ ማምረት ካልቻልን የዓለምን ሕዝብ መመገብ አንችልም፡፡ በአፍሪካና በእስያ ደግሞ ብዙ ሕዝብ አለ፡፡ ችግሩ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ በመሆኑ እንደ አገርም ሆነ እንደ ዓለም ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡
ሪፖርተር፡- በምግብ ደኅንነት ኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- አገራችን የምግብ ደኅንነትን እያሟላች እንዳልሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ አንዱ የሚታየው በሽታ ነው፡፡ ተቅማጥ፣ ካንሰር፣ ኩላሊት፣ የአንቲባዮቲኮች አልሠራ ማለትና የኢንፌክሽን መጨመር ማሳያዎች ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ ብናየውም ኤክስፖርት የምናደርገው በቂ አይደለም፡፡ አገር ውስጥ የሚመረተው ደኅንነቱና ጥራቱ ላይ ክፍተት አለ፡፡ ምግቦች ከባዕድ ነገሮች ተቀላቅለው ይገኛሉ፡፡ ኅብረተሰቡ የሚገዛው ምግብ ላይ ተጠራጣሪ ሆኗል፡፡ የምግብ ደኅንነት መጓደል ደግሞ የምግብ ዋስትናን ያዛባል፡፡ ለምሳሌ ስንዴ አምርተን ጎተራ ካላስገባነው በፈንገስና በነቀዝ ይጠቃል፡፡ ይህ የምግብ እጥረት ያስከትላል፡፡ ይህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምግብ አቅርቦት ላይ ችግር ያመጣል፡፡ አቅርቦቱ ከቀነሰብን ሁሉም ሰው ይቸገራል፡፡ ድኅረ ግብርና ብክነት በተጠኑ ጥናቶች በአፍሪካ 40 በመቶ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ምግብ ይበላሻል ሲባል ቀልድ የሚመስለው ቢኖርም፣ አትክልትም እስከ 50 በመቶ ይባክናል፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ማንጎ ይበሰብሳል፡፡ አሶሳ፣ ወለጋና ሌሎችም ቦታዎች ብንሄድ ማንጎ ወድቆ ይታያል፡፡ እሴት ተጨምሮበት ተመርቶ አይቀርብም፡፡ ነገር ግን በማንጎ ፍሌቨር ጤንነት በማይሰጡ የፈሉ ስኳሮች ጁስ ተመርቶ እንጠቀማለን፡፡ እነዚህ የምግብ ደኅንነታችን መጓደል መገለጫዎች ናቸው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያውቁት ብዬ በየሚዲያው ሐሳቤን የጻፍኩትና የገለጽኩትም ደኅንነቱ ላይ በቂ ቁጥጥር አለመደረጉ እያስከተለ ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ስላሳሰበኝ ነው፡፡ የሚሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ኅብረተሰቡን ሊጠብቁት አልቻሉም፡፡ ከየሱፐር ማርኬቱና ከየገበያው የምንገዛውና የምንበላው ምግብ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እኔም ራሴን፣ ኅብረተሰቡንና ቤተሰቤን ለመጠበቅ ነው ችግሩን እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ ከምርምር ተነስቼ ኅብረተሰቡን ለማዳን ነው ጥረት እያደረግኩ ያለሁት፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት ከኢኮኖሚዋስ ምን ያህል ታጣለች?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- አንዳንዴ የማንደነግጠው ቁጥሩን ስለማናውቀው ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ እ.ኤ.አ. በ2024 አሜሪካ የሚገኙ ሳይንቲስቶች መጥተው በወተት፣ በሥጋና በእንቁላል ላይ በሚገኙ በአራት ባክቴሪያዎች ዙሪያ ብቻ አጥንተዋል፡፡ ነገር ግን አራት ባክቴሪያዎች ብቻ አይደሉም ችግር የሚያስከትሉት፡፡ እነዚህን የሚያጠቁ ሄቪ ሜታል፣ አፍላቶክሲንና ፔስቲሳይድ አሉ፡፡ የተጠናው ግን በአራቱ ላይ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን አራቱ ብቻ ኢትዮጵያን በዓመት 723 ሚሊዮን ዶላር ያሳጧታል፡፡ ይህ ከአገሪቷ ጂዲፒ አንድ በመቶ ይይዛል፡፡ በረሃብና በድርቅ ምክንያትም ወደ 16.5 በመቶ የአገራችን ጂዲፒ ይበላል፡፡ ይህ ከደኅንነትና ጥራት ችግር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም በቂና ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ አለማግኘት ኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዳያደርግ ያደርገዋል፡፡ ያልበላና አዕምሮው በትክክል ያላደገ ልጅ ኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ ሊያደርግ አይችልም፡፡ አገሪቱም ባላት ትውልድ ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት መቀንጨር አሁንም 37 በመቶ ነው፡፡ አምስት ሚሊዮን ሕፃናት ማለት ነው፡፡ እነዚህ አገር ሲረከቡ በሚፈለገው መጠን በብቃት ሠርተው አገር ማሳደግ ስለማይችሉ አገሪቱ በጥራትም በደኅንትም ምክንያት ኢኮኖሚዋን እያጣች መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ምን ያህል ምርት ወደ ውጭ ይላካል? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለሚላከው ምርት ማነስ ምክንያቱ ጥራትና ደኅንነቱን ባለመጠበቃችን ነው፡፡ ለምሳሌ ቡና እንልካለን፡፡ 1.6 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ይገኝበታል፡፡ ነገር ግን ማግኘት ያለብንን ነው ወይ እያገኘን ያለነው? ሲባል የጥራት ችግር አሁንም ይነሳል፡፡ ማግኘት ያለብንን ከፍተኛ ዋጋ እያገኘን አይደለም፡፡ ሥጋም ለውጭ ገበያ በርካሽ ነው እየሸጥን ያለነው፡፡ ውጭ ከሚሸጥበት ሒሳብ ይልቅ የአገር ውስጥ ይወደዳል፡፡ በኢኮኖሚው እንደ አገርም፣ እንደ ግለሰብም እየከፈልን ነው፡፡ ለዚህ ኑሮ ውድነቱን ማየት በቂ ነው፡፡ እራት በባዶ ሆድ እንደር እየተባለ ነው፡፡ ቁርስና ምሳ አንድ ጊዜ እየተበላ ነው፡፡ የምግብ ስብጥሩም ቢታይ ወደ አንድ መሠረታዊ ምግብ እንጀራ ብቻ፣ ቆጮ ብቻና ወደ ተመሳሳይ ምግቦች እየመጣን ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ሳህናችን ላይ የነበረው ስብጥር አንሶ አንድ ዳቦ ወይም አንድ እንጀራ እንዳይቀር እፈራለሁ፡፡ ይህን መቀየር ብዙ ትግልና ሥራ ቢፈልግም፣ የምግብና የምርት ደኅንነታችንን አስጠብቀን ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ ደኅንነት ከደረጃም ጋር የሚያያዝ ነውና የምግብ ተመራማሪ እንደመሆንዎ በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ ደረጃ እንዴት ይገልጹታል?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- እኔ በምሠራበት ዩኒቨርሲቲ የምግብና የግብርና ምርቶች ደረጃ ዝግጅት ክፍል አለ፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴም አለን፡፡ እስካሁን በአገራችን ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ በጠቅላላ ወደ 7,000 ደረጃዎች ተሠርተዋል፡፡ እኔ የሳተፉኩበት የእንጀራ፣ የበርበሬ፣ የቆጮ፣ የቆሎና የሌሎችም ደረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሆኑ የወተት ደረጃዎች አሉ፡፡ የደረጃ ዝግጅቱ ላይ በጥሩ ሁኔታ እየሠራን ነው፡፡ ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮዴክስ፣ የአይኤስኦ ተሳታፊ ነች፡፡ ይህንን በበላይነት የሚሠራው የደረጃ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው ደረጃዎቹ በዚያ ልክ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ወይ? የሚለው ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዶክመንት፣ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ ችግር አለ አልልም፡፡ ብዙ ጊዜ የምናጠፋውም በኮንፈረንስና ዶክመንት በማዘጋጀት ነው፡፡ እዚህ ላይ ጎበዝ ነን፡፡ በዚያው ልክ ወርደን እንሠራለን ሲባል ግን በተጠናው ጥናት ከተዘጋጁት 7,000 ያህል ደረጃዎች ውስጥ 40 በመቶ ብቻ ናቸው ቁጥጥር የሚደረግባቸው፡፡ ለምሳሌ ውኃ ቁጥጥር ይደረግበታል፣ የደረጃ ምልክትም አለው፡፡ ወተት ቁጥጥር አይደረግበትም፣ የደረጃ ምልክትም አይጠቀምም፡፡ የለውዝ ቅቤ ምልክት የለውም፣ ቁጥጥር አይደረግበትም፡፡ ቢራ ቁጥጥር ይደረግበታል፡፡ አንዳንዴ የቁጥጥር ሥራችን የትኛው አካል ይከፍላል ብለን የምንሠራው ነው የሚመስለው፡፡ የቢራና የውኃ ፋብሪካዎች ለደረጃውና ለምልክቱ ይከፍላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ወሳኝ የሆኑና በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ያሉ ምርቶች ቁጥጥር እየተደረገባቸው አይደለም፡፡ በተለይ ከምግባችን በርበሬን ብቻ ብናይ እኛ ወጥተን ባጠናነው እስከ 60 በመቶ የሚሆነው የበርበሬ ምርት የአፍላቶክሲን መጠኑ ከፍተኛ ነው፡፡ ለውዝ በከፍተኛ ደረጃ በአፍላቶክሲን የሚጎዳ ቢሆንም፣ የለውዝ ቅቤ ተመርቶ ይሸጣል፡፡ አፍላቶክሲን በከፍተኛ ሁኔታ ጉበት ሊጎዳ ይችላል፡፡
የመቆጣጠር አቅማችን በተቆጣጣሪ አካላት መበጣጠስ ምክንያት መዳከሙ ወይም ሁሉም ሥራውን በተገቢው አለመወጣቱ፣ መንግሥትም በተገቢው ደረጃ ትኩረት አለመስጠቱ እኔን እያሳሰበኝ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠልን የምግብ ሳይንቲስትም ብሆን እያወቅኩት መሞቴ ነው፣ ኅብረተሰቡም መጎዳቱ ነው ብዬ ሐሳቤን እየገለጽኩ ነው፡፡ ዘርፉ ቁጥጥር ይደረግበት እያልኩ ነው፡፡ የትራፊክ ቁጥጥር አለ፣ በኮሪደር የለሙ ቦታዎች ፅዳትና ቁጥጥር አለ፡፡ እኔም በሚገድለንና በሚጨርሰን ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን እያልኩ ነው፡፡ ብዙዎቹ ተቆጣጣሪ አካላት ደረጃውን ያልጠበቀ ምግብ ተገኘ ይላሉ፡፡ ዕርምጃ ተወሰደ ሲባል ትሰማላችሁ? ጥቂት ኬዞች ናቸው ያሉትም፡፡ የምግብ ደኅንነት ችግር ዛሬውኑ አይገድልም፣ ቆይቶ ነው፡፡ ዛሬ ስለማይገድሉን ጤነኛ የሆንን ይመስላል እንጂ በጊዜ ሒደት ይገድሉናል፡፡ ስለዚህ ቁጥጥር ይደረግ ነው የምለው፡፡ ከዚሁ ጋር አምራቶችና አቅራቢዎችም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሆኖም ለዚህ የሚዳርገን ከአምራቹ ወገን የሚነሳው የገንዘብ ችግር መፈታት አለበት፡፡ ለምሳሌ ወደ ባቢሌ ብንሄድ ኦቾሎኒ አለ፡፡ ነገር ግን የኦቾሎኒ ሽፋን ለማንሳት ለእጅ ቀለል እንዲል በውኃ ይነክሩታል፡፡ ይህ አፍላቶክሲን (ሻጋታ) እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ሊፈለፍል የሚችል ቴክኖሎጂ ማዘጋጀት አለብን፡፡ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ እነዚህ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እያደረገ ነው፡፡ ሌላ ተቃርኖ ደግሞ አለ፡፡ አምራቹ በማሽን ፈልፍሎ አዘጋጀውም በእጅ ፈልፍሎ፣ አፍላቶክሲን ኖረውም አልኖረውም ገበያ ውስጥ ምርቱ አለ፡፡ ገበያው እስካልቆመ ድረስ አምራቹ አይቀየርም፡፡ ስለዚህ ተቆጣጣሪው ቢጠነክር የኢትዮጵያን የምግብ ኢንዱስትሪ የምግብ ደኅንነት ችግር መቅረፍ እንችላለን፡፡
አንዳንዶች ማምረት (ኢንቨስት) ማድረግ የማይፈልጉት፣ ‹እኔም በንፁህና በጥራት አምርቼ ሌላውም ከደረጃ በታች አምርቶና አበላሽቶ በእኩል ዋጋ ይሸጣል› ብለው ነው፡፡ የምግብ ሳይንስ ባለሙያ የሚፈልግ ኢንዱስትሪም ጥቂት ነው፡፡ ላይሰንስ ገዝቶ ነው የሚሠራው፡፡ ተማሪዎቻችን ሥራ ያጣሉ፣ እኔን ዕርዳኝ ብለው የሚጠሩኝ በጣም ጥቂት ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህንን የሚጠይቅ አስገዳጅ ሁኔታ አልገጠማቸውም፡፡ ለአምራቾቹ ማሳወቅ የምፈልገው ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ሁኔታ ስለገባች፣ የውጭ ባለሀብቶችም መግባት ስለጀመሩ፣ ከዚህ እኩል የሚፈለገው ጥራትና ደረጃ ላይ ካልሆኑ፣ የአገራችን አምራቾች በቅርቡ ከጨዋታ ውጪ እንደሚሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የመጡት የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በ600 ሚሊዮን ዶላር በሚሆን ካፒታል የወተት ፋርም ሊጀምሩ መሆኑን ሰምተናል፡፡ መሰል ፋርሞች ምርት የጀመሩ ጊዜ ኅብረተሰቡ ወተት የሚገዛው ከእነሱ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያው ክፍት ስለሆነች ብዙ ኢንዱስትሪዎች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ችግር ውስጥ ይገባሉ፣ አሁንም እየገቡ ነው፡፡ መርካቶ ከደረሰኝና ከምርት ጋር በተያያዘ ችግር እየታየ ነው፡፡ ምርት ይገባል፣ አምራች ፋብሪካው አይታወቅም፡፡ ተቆጣጣሪው አካልም ካገኘኋቸው እቆጣጠራለሁ ብዙዎችን ግን አላውቃቸውም ብሏል፡፡ በየምርቱ ላይ የተለጠፈ ስልክና አድራሻም የውሸት ነው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃ መዘናጋት የለብንም እላለሁ፡፡ አምራቹም ግዴታውን ሊወጣ፣ ኅብረተሰቡም ጠያቂ ሊሆን ይገባል፡፡ የሸማቾች ጥበቃ ማኅበራትም በበቂ መደራጀት አለባቸው፡፡ እኔ ይህንን እየወተወትኩ እንኳን ሥልጣን ፈልጎ ነው በማለት የሚከራከሩኝ አሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ራሱን መጠበቅ የቻለ አይመስለኝም፡፡ ለራሱ ብዬ መከራከሬን የማይገነዘብ አለ፡፡ ራሱን እየጎዳና ደረጃው የወደቀ ምግብ እየበላ መሆኑን እያወቀ ተቀብሎ እየኖረ ነው፡፡ ይህንን ማስተካከል ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች የሚስተካከሉትም መጀመሪያ ጥንካሬው ከመንግሥት ሲመጣ ነው፡፡ ከመንግሥት በኋላ ተቆጣጣሪው፣ በኋላ አምራች፣ ከዚያም ኅብረተሰብ እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከመንግሥት መምጣት አለበት ቢሉም፣ መንግሥት የረጋ ዘይት እንዲገባ ውሳኔ በመስጠቱ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የለውዝ ቅቤ አፍላቶክሲን እንዳለበት ይታወቃል፣ ገበያ ውስጥ ግን አለ፡፡ ችግሮች እንዳሉ እየታወቀ በዚያው ቀጥሏል፣ ውሳኔዎች ሲተላለፉ እንዴት መሆን አለበት?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- ይህ ሙሉውን ለመንግሥት ወይም ለተቆጣጣሪው አካል ብቻ ይተው ብዬ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ በሳይንስ የደረስንበት ለውጥ የ10 እና የ15 ዓመታት ጥረት ነው፡፡ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እንደ አገር ደግሞ ብዙ እጥረቶች አሉብን፡፡ የተማረ ሰውና የላቦራቶሪ እጥረት አለብን፡፡ በቂ የተማረ የሰው ኃይል አሰማርቶ የማሠራት፣ የቴክኖሎጂና ሌሎችም ችግሮች አሉብን፡፡ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉን አማርጣ ለማድረግም ሀብታም አገር አይደለችም፡፡ ነገር ግን ይህንን ለመቆጣጠር የተቋቋሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎችም አሉ፡፡ እነዚህ በበቂ ሁኔታ እንዲሠሩ ከተፈለገ መንግሥት ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ሀብት የት ነው መስጠት ያለብን ብሎ ማየት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የምግብ ተቆጣጣሪዎች አሉ? ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ፋብሪካዎች ያሉት ኢንስፔክተሮች ምን ያህል ናቸው? መኪናና ውሎ አበል በበቂ ቀርቦ ቁጥጥር ሊያደርጉ ይችላሉ ወይ? በአንድ ተቋም ተደራራቢ ኃላፊነቶች የሉም ወይ? አንድ ጉዳይስ ለብዙ ተቋማት ተበጣጥሶ አልተሰጠም ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ የምግብ ደኅንነት ጉዳይ ለምግብና መድኃኒት፣ ለደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ ለተስማሚነት ምዘና፣ ለኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ለግብርና ባለሥልጣን ተሰጥቷል፡፡ እነዚህ የተበጣጠሱትን መሰብሰብ አለብን፡፡ ለምግብ ራሱን የቻለ ባለሥልጣን ይቋቋምለት ስል ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምጠይቀውም፣ ሥራውን በባለሙያ ብቻ በተሻለ ሁኔታ አሠርተን የምግብ ደኅንነታችንን እንድናስጠብቅ ነው፡፡
የምግብ ሳይንስ ሙያን ወደ ተግባር ለማምጣትም ከሁሉም ተሰብስቦ በባለሥልጣን ደረጃ ቢዋቀርና ትኩረት ቢሰጠው፣ መንግሥትም የሚያስፈልገውን በጀት ቢያቀርብ በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያመጣል፡፡ የምግብ ደኅንነት ማጣት ቱሪዝሙን እየጎዳብን ነው፡፡ ከውጭ ውኃ ይዞ የሚመጣ ቱሪስት አለ፡፡ ምግብ በሻንጣው ይዞ የሚመጣና የኢትዮጵያን ግብዓት መጠቀም የሚፈራ አለ፡፡ ቱሪዝሙን ሊጎዱ የሚችሉ ችግሮች አሉ፡፡ እምነት ማጣት አለ፡፡ እንጀራ ላይ ጀሶ ይቀላቀላል እየተባለ ከኢትዮጵያ ከሚላከው እንጀራ ይልቅ፣ ከኤርትራ የሚላከው ተመራጭ እየሆነ ነው፡፡ እነዚህን አሁኑኑ ካላስተካከልን አገሪቱ ትጎዳለች፡፡ በምግብ ቁጥጥር ላይ ያሉ አካላት ልክ እንደ ታክስ ቁጥጥሩ፣ ትራፊክ ማኔጅመንቱና አካባቢ ፅዳቱ ኮስተር ብለው ሊሠሩ ይገባል፡፡ እንደ እኔ ያሉ የምግብ ሳይንስ ባለሙያዎችም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኅብረተሰቡን ሊያስተምሩ ይገባል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት የኤክስፖርት ደረጃ የሚል አለው፡፡ ነገር ግን ጥራት ለሁሉም አሜሪካዊም ሆነ ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ ከእኛ አገር ወደ ውጭ የምንልካቸው ምግቦች ጥራታቸው የተጠበቀ ሆኖ ሳለ፣ አገር ውስጥ የምንጠቀመው ጥራቱና ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ይሆናል፡፡ ለአንድ የሚሠራ ለሌላው የማይሠራ ደረጃ ነው ያለን፡፡ አምራቹ ለውጭ ለመላክ ጥሩ ጥሬ ዕቃ፣ እንዲሁም ደግሞ አገር ውስጥ ለሚሸጠው የወረደውን ጥሬ ዕቃ ይጠቀማል፡፡ ይህ በሁላችንም ዘንድ እንደ ባህል የአስተሳሰብ ለውጥ ሊመጣበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምርት ወደ ውጭ ሲላክ ጥራቱ ተጠብቆ ነው፡፡ ትንሽ ግድፈት ከተገኘም በደረሰበት አገር እንዲወገድ ይደረጋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት በዚህ መጠን ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ምን መደረግ አለበት?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- ሕጋዊ መስመር ተከትለው የሚገቡ ሸቀጦችና ምርቶችን የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና አቅሙን አደራጅቶ የጥራት መንደር በሚባለው ፍተሻ እያደረገ ነው፡፡ እሱ የማይችላቸውን ለሦስተኛ ወገን በመስጠት ያስፈትሻል፡፡ ከዚህ ቀደም በአገር ደረጃ መሠራት የማይችሉት ሳይፈተሹ ይግቡ የሚባለው አሁን ቀርቷል፡፡ ተስማሚነት እየሠራ ያለው ሥራ ሊደነቅ የሚገባው ነው፡፡ በአገሬ አቅም መገንባቱም ያስደስተኛል፡፡ ግን ያለው ላቦራቶሪ አንድ ስለሆነና በቂ ስላልሆነ በየክልሉ የተስማሚነትን የመሰሉ ላቦራቶሪዎች ሊከፈቱ ይገባል፡፡ በሕገወጥ የሚመጣው ሌላው ሲሆን፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚጎዳውም ይኸው ነው፡፡ ብዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ይገባሉ፡፡ ከእነዚህ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምግብ ነው፡፡ እነዚህን ማስተካከል የምንችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ቁጥጥሩ እንዳለ ሆኖ፣ ገበያው ራሱ መልስ እንዲሰጠው ማድረግ ይቻላል፡፡ ከታክስ ጋር አያይዞ ኪውአር ኮድ እንዲጠቀምና እንዲመዘገብ ማድረግ ነው፡፡ ገዥው ያንን አረጋግጦ እንዲገዛ ካልሆነ ደግሞ እንዲተው ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ይህ ኮንትሮባንዱን ይቆጣጠረዋል፡፡ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም፣ መንግሥት ትኩረት ካደረገ መቆጣጠር እንችላለን፡፡ የደረጃ ምልክት ማድረግና የደረጃ አፈጻጸም ለሁሉም አምራች አንድ መሆን አለበት፡፡ ማንም ሰው ምግብ እንደፈለገ የሚገባበት ሥራ መሆንም የለበትም፡፡ ይህ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ተቆጣጣሪው የሚሠራው ሥራ አገር ይቀይራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ባለሙያ ከሌለ የምግብ ፋብሪካ መክፈት አይቻልም ይላል፡፡ ነገር ግን የሙያ ፈቃድ ተከራይተው የሚሠሩ አሉ፡፡ ቁጥጥር ሲኖር ባለሙያ ያሳያሉ፣ ሳይኖር ይተውታል፡፡ እያንዳንዱ የሚወጣ ምግብ የምግብ ባለሙያ ከሌለ መውጣት የለበትም፡፡ ለዚህ ተብሎ እኛ አገር ፈቃድ የሚሰጠው ለባለቤቱ ብቻ ሳይሆን ለጥራት ቁጥጥር ባለሙያውም ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን ምን ያህሉ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል? የምግብ ባለሙያ ሳይኖር ምግብ ተመርቶ ቢሆን ምን ያህል እንቀጣለን? የሚለውን ማየት አለብን፡፡ በሌላ አገር የምግብ ቁጥጥር ባለሙያው ‹የተመሠረተውን ምርት አምኜበታለሁ ጤናማ ነው› ብሎ ፈርሞ ነው ምርቱን የሚያወጣው፡፡ እኛ አገር ባለሙያ ሳይኖር ምርቶች ይወጣሉ፡፡ ይህ ሰው እንደ መግደል ስለሆነ ቁጥጥሮች በየዘርፉ ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ ሚዲያው፣ በዘርፉ ያሉ ተቋማትና እኛ ባለሙያዎች ጉዳዩን ካላሰማን የልጆቻችን ሕይወት ይቃወሳል፣ እየተቃወሰም ነው፡፡ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች ጤና እየተቃወሰ፣ ወጣቶች ድንገት እየሞቱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ ደኅንነት ሲነሳ በዕርዳታ የሚገቡ ምግቦች ቀጥታ ለተጎጂዎች የሚደርሱ ናቸውና እንዴት መታየት አለባቸው?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- እኔ እንዲያውም የዕርዳታ ምግቦቹ የተሻሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ የዕርዳታ ምግቦች በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚደገፉ ናቸው፡፡ ያለ ጥራትና ደኅንነት አይፈቀዱም፡፡ የዓለም ምግብ ድርጅት፣ የሕፃናት አድን ድርጅት፣ ዩኤስኤአይዲና ሌሎችም የሚሰጧቸው ምርቶች የጥራትና የቁጥጥር ሥራቸው ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ፕላንፒነት ከኦቾሎኒ የሚሠራ ምርት ነው፡፡ ይህ የሚመረተው በህሊና ኢንሪች ፉድስ ነው፡፡ ይህ ምግብ ኦቾሎኒ ይጠቀማል፡፡ ኢትዮጵያም የኦቾሎኒ አምራች አገር ነች፡፡ ነገር ግን የአገራችን ለውዝ የአፍላቶክሲን መጠኑ ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ፣ በረጂዎቹ በኩል መጠቀም አትችሉም ተብለው ለፕላንፒነት ምርት ለውዝ የሚመጣው ከስዊድንና ከደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ የለውዝ አምራች የሆንን አገር ከውጭ ጥሬ ዕቃ እናስመጣለን፡፡ በኢትዮጵያ በተለየ ሁኔታ አፍላቶክሲን አለው በተባለው ለውዝ የኦቾሎኒ ቅቤ ተመርቶ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የውጭዎቹ ችግር አለበት ብለው የተውትን አገር ውስጥ እንጠቀማለን፡፡ ይህ ትክክል አይደለም እያልኩ ነው፡፡ ዕርዳታ የሚሰጡን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰርተፊኬት አግኝተው ስለሆነ ደረጃ ያልጠበቀ ምግብ ቢያቀርቡ በሥነ ምግባርም፣ በሞራልም ያስጠይቃቸዋል፡፡ በአገር ውስጥ የተመረተውን በሦስተኛ ወገን አስጠንተው ደረጃ ካልጠበቀ አይጠቀሙም፡፡ ይህ በችግር፣ በድህነትና በረሃብም ቢኮን ምግብ ጤነኛ ካልሆነ ምግብ አይደለም የሚለውን ይነግረናል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በፖሊሲ አውጪዎች፣ በኅብረተሰቡ፣ በተማረው ውስጥ ከመጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነት አደጋ ውስጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያውቁልዎት በየአጋጣሚው ማሳሰብ የጀመሩበት ምክንያት ይኸው የነገሩን ነው? ወይስ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት አለዎት?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- ይህ ዛሬ ያመጣሁት ሐሳብ አይደለም፡፡ ያደረግናቸውን ጥናቶች ሁሉ ለመንግሥት እናሳውቃለን፡፡ ዓምና ይፋ ያደረግነው የምግብ ደኅንነት ፍኖተ ካርታ ከአንድ ዓመት በላይ እኔ ያስተባበርኩት ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ 11 ተቋማት አብረን የሠራነው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሆነውን ነገር ብትጠይቂኝ ግን አላውቅም፡፡ እስከማውቀው እንቅስቃሴ የለም፡፡ በኃላፊነት የሚመራው የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ የግብርና ባለሥልጣን፣ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የተስማሚነት ምዘና፣ የንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ በኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነት የሚመለከታቸው ተቋማትም አሉበት፡፡ በኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነት ችግር እንዳለ ያውቁታል፣ በፍኖተ ካርታውም ተስማምተውበታል፡፡ አገሪቱ ባለችበት መቀጠል አትችልም፣ የምግብ ደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ ነው በሚለውም ሁሉም ተማምነዋል፡፡ አሁን ያሉት መሥሪያ ቤቶች ሥራውን በበቂ እየሠሩ ካልሆነ ድርጅት ማዋቀር ያስፈልጋል፡፡ በፍኖተ ካርታው ላይ የተሰጠው አንዱ ምክረ ሐሳብም ገለልተኛና ነፃ የሆነ የምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ከግብርናው እስከ ገበያ ይመሥረት የሚል ነው፡፡ እኔም ያቀረብኩት ይኼንኑ ነው፡፡ ይህንን እኔ ብቻ ያልኩት ሳይሆን 11 ተቋማት የተስማማንበት ምክረ ሐሳብ ነበር፡፡ አሁን በኢትዮጵያ መሥሪያ ቤቶች ሪፎርም እየተካሄደ ነው፡፡ የምግብ ቁጥጥር ስናካሂድ በቂ የምግብ ቁጥጥር ባለሙያ አለ ወይ? የሚለውን ገምግመን ክፍሎችን መክፈት ያስፈልጋል፡፡ የቁጥጥር ሥራው ሰፊ ስለሆነ ክፍሎችን አዋቅሮ፣ በጀት መድቦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልሎችም መኖር አለበት፡፡ አዲስ አበባ ያለው ቁጥጥር ክልል ሲሄድ ይቀንሳልና እንደ የሌማት ትሩፋት ከፌዴራል እስከ ክልል በአንድ ዓይነት ሁኔታ መያዝ አለበት፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወቁልኝ ያልኩትም ካለንበት ችግር አንፃር ቶሎ ከድጡ የምንወጣው ከላይ ካለው ዕርከን የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ሲመጣ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ሐሳብዎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲደርስ በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር አሠራጭተዋል፡፡ ሐሳብዎ በቅርቡ ዕውን ባይሆን ምን አማራጭ ይዘዋል? መፍትሔ የሚሏቸውስ ምንድናቸው?
አሻግሬ (ዶ/ር)፡- የምግብ ደኅንነትን በተመለከተ ደረጀ በደረጃ የሄድኩባቸው ሒደቶች አሉ፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት ተማሪዎችን በማስተማርና ለመንግሥት አካላት ግንዛቤ በመፍጠር፣ ከፍተኛ የሕግ አውጪ አካል እስከሚባለው ለመንገር ሞክሬያለሁ፡፡ እኔ ውጤት ነው የምለው ሒደቱን ነው፡፡ ምግብ መብላት ብቻ ሳይሆን ጥራቱን መጠበቅ አለብን ብለን ብዙ ርቀት መጥተናል፡፡ እኔም ውትወታውን እቀጥላለሁ፡፡ ለውጦች እየመጡ እንደሆነ አያለሁ፡፡ አገራችን ደሃ በመሆኗ ግን አንዴ ይሳካል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሩን አምነን ከተቀበልን በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ያነሳኋቸው ሐሳቦች በመንግሥት የማይባሉና የማይታወቁ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ጽሕፈት ቤታቸው የምግብ ባህል እንዲቀየር እየሠሩ ነው፡፡ የእነሱ ሥራ እኔ ከምናገረው ጋር ይለያያል ብዬ አላስብም፡፡ የበለጠ ተቀናጅተን ብንመጣና እኛ ባለሙያዎችም ብንተባበር፣ ኅብረተሰቡም ስለሚመገበው ቢያውቅና ቢጠይቅ፣ አምራቹም አዕምሮአዊ ግዴታውን ቢወጣ ለውጡን ማምጣት እንችላለን፡፡ ለምግቦቻችን አምባሳደር ሳይሆን ጥራት ያስፈልገናልና ጥራቱ የተረጋገጠ ምርት መቅረብ አለበት፡፡ ስግብግብነቱ ቢቀር፣ የትርፍ ህዳግ ቢጠበቅም እላለሁ፡፡ እንደ አጠቃላይም ጠንካራ ቁጥጥርና ፍትሐዊ የገበያ ውድድር ቢፈጠር በኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነትን ለማሻሻል ያስችሉናል ብዬ አምናለሁ፡፡