በሶሪያ የባሕር ዳርቻ ከተማ በሆነችው ላቲካ የጸጥታ ኃይሎች የፍተሻ ኬላዎችን አቋቁመዋል

ከ 7 ሰአት በፊት

የሶሪያ የጸጥታ ኃይሎች በአገሪቱ የባሕር ዳርቻ አካባቢው በቀጠለው አለመረጋጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአላዋይት ማኅበረሰብ አባላትን ገድለዋል የሚል ውንጀላ ቀረበባቸው።

መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ (SOHR)፣ አርብ እና ቅዳሜ በአላዋይት ማኅበረሰብ አባላት ላይ ባነጣጠረ ጥቃት 30 “ጭፍጨፋዎች” ተካሄደዋል ያለ ሲሆን በአጠቃላይ 745 ንፁኃን ዜጎች ተገድለዋል ብሏል።

ቢቢሲ ይህንን መረጃ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጎሳዎች የሆኑ ማኅበረሰብ አባላት ከሚኖሩበት ከዚህ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሰደዳቸው ተነግሯል።

በሶሪያ በታኅሣሥ ወር አማፂያን የአሳድን መንግሥት ካስወገዱ በኋላ ከፍተኛ ነው በተባለው የሰሞኑ ግጭት በጠቅላላው ከ1,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አስታውቋል።

ይህ ቁጥር ከሐሙስ ጀምሮ በባህር ዳርቻ አካባቢ በሚገኙት ላታኪያ እና ታርቱስ ግዛቶች በመንግሥት ወታደሮች እና ለአሳድ ታማኝ በሆኑ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭትም ያካትታል።

የሶሪያን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሚከታተለው ተቋም በግጭቱ 125 የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና 148 የአሳድ ደጋፊ ተዋጊዎች ተገድለዋል ብሏል።

የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለአገሪቱ የሳና የዜና ወኪል፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ “የሽምቅ ጥቃት” ለማድረስ ተሞክሮ እንደነበር ገልጸው አሁን ግን በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድተዋል።

በከተማዋ የሚኖር አንድ አክቲቪስት ለቢቢሲ፣ ጥቃቱ የአላውያንን ማኅበረሰብ አባላት “አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ጥሏቸዋል”፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው መሰደዳቸውን ተነግሯል።

የሮይተርስ የዜና አገልግሎት በበኩሉ ብዙ ሰዎች በላታኪያ በሚገኘው ሃሜሚም የሩሲያ ጦር ሰፈር ተጠልለዋል ብሏል።

በሮይተርስ የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል በርካታ ሰዎች ከጦር ካምፑ ውጪ “የሩሲያን ጥበቃ እንፈልጋለን” እያሉ ሲጮሁ ይታያል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ሶሪያውያን ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሊባኖስ መሰደዳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ገይር ፔደርሰን በበኩላቸው፣ በሶሪያ የባህር ጠረፍ አካባቢዎች በሲቪሎች ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት “አሳሳቢ” መሆኑን እና “በጣም እንዳስጨነቃቸው” ተናግረዋል።

ሁሉም ወገኖች አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት ከሚያስገቡ እና “ተዓማኒ እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሽግግርን” አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

በሶሪያ አብላጫ ቁጥር ያላቸው የሱኒ ሙስሊሞች ሲሆኑ በተቃራኒው አላዋይቶች ደግሞ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ 10 በመቶ ከሆኑት የሺዓ ሙስሊሞች መካከል ናቸው።