
ከ 7 ሰአት በፊት
ታዋቂዋ ደራሲ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቼ የመጀመሪያ ልጇን አርግዛ በነበረበት ወቅት “አስደንጋጭ በሆነ መልኩ መጻፍ አልቻልኩም ነበር” ትላለች።
“በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘት በጣም አስፈሪ ነው። ምክንያቱም ለሕይወቴ ትርጉም የሚሰጠኝ መጻፍ ብቻ ነው” ስትል የ47 ዓመቷ ተወዳጇ ናይጄሪያዊት ደራሲ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“[ክስተቱ] ሙሉ በሙሉ አካላዊ ስለመሆኑ እርግጠኛ አልነበርኩም። ነገር ግን አንድ የሆነ ነገር እንደተቀየረ ተሰማኝ። እናም ልብወለድ ልጽፍ ወደምችልበት ወደዚያ ምትሃታዊ ስፍራ መሄድ አልቻልኩም” ብላለች።
ቺማማንዳ የመጀመሪያ ሴት ልጇን በአውሮፓውያኑ 2016 የወለደች ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት መንታ ወንድ ልጆችን ከወለደች አሁኑ 11 ወራት ሆኗቸዋል።
ደራሲዋ ነፍሰጡር እያለች “አዕምሮዋ ጥርት አድርጎ ማሰብ” ይሳናት እንደነበር እና “ጭፍግግ ያለ ስሜት ይሰማኛል” ስትል ለቢቢሲ አስስረድታለች።
“ግልጽ ላለ ሃሳብ ከፍተኛ ስፍራ ከሚሰጡት ሰዎች አንዷ ነኝ። እናም በእንደዚያ ዓይነት ቦታ ላይ መሆን በጣም አስፈሪ ነው” ብላለች።
ቺማማንዳ “ድሪም ካውንት” የሚለውን ልብወለዷ የመጨረሻ ሥራዋ ከወጣ ከአስር ዓመት በኋላ ለህትመት በቅቷል።
መጽሐፉ ሕይወት በዕቅዳቸው መልኩ እየሄደላቸውን ያልሆኑ የአራት ሴቶችን ሕይወት ይዳስሳል።
“ለተወሰነ ጊዜ መጻፍ አልቻልኩም ነበር፤ ከዚያ እንደገና መጻፍ ጀመርኩ” ትላለች።
ቺማማንዳ ፌሚኒዝምን፣ ሥርዓተ ፆታን እንዲሁም ስደትን የመሳሰሉ ጭብጦችን በሚዳስሱ ጽሁፎቿ ትታወቃለች።
“ሁላችንም ፌሚኒስት መሆን አለብን” በማለት በአውሮፓውያኑ 2012 በቴድ ቶክ ላይ ያደረገችው ንግግር ዝናዋ በዓለም እንዲናኝ አድርጓል።
- https://www.bbc.com/amharic/extra/diyd5gtsh3/demolished_heritages_amharic
- የሰባት ወር ነፍሰጡር ሆና በፓሪስ ኦሊምፒክ በመሳተፍ ዓለምን ያስደመመችው ስፖርተኛ23 የካቲት 2025
- እናትነትን ሸሽተው በፈቃዳቸው መካን መሆንን የሚመርጡት ሴቶች26 የካቲት 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ይህ ንግግሯም ቢዮንሴ በአውሮፓውያኑ 2013 ባወጣችው ‘ፍላውለስ’ በተሰኘው አልበሟ ተካቷል።
ቺማማንዳ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ሰፊ ቃለ ምልልስ ስለ ወላጅነት፣ ሐዘን እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይን) በተመለከተ ማብራሪያዎችን ሰጥታለች።
ደራሲዋ ስለ ሥርዓተ ፆታ ያላት እምነት ወንድ ልጆቿን እንዴት ማሳደግ እችላለሁ የሚለውንም በደንብ እንድታስብበት አድርጓታል።
“ጥሩ ወንዶችን ለማሳደግ ቆርጫለሁ” ብላለች።
“ልጆቼ በሚሰሟቸው ስሜቶች ምቾት እንዲያገኙ፣ ከስሜቶቻቸው ጋር ቁርኝት እንዲኖራቸው፤ ስሜቶቻቸውን እንዳይፈሩ እንዲሁም ፍርሃትን እንዳይፈሩ አድርጌ ማሳደግ እፈልጋለሁ” ስትል ገልጻለች።
ደራሲዋ ከሴቶች ታዳጊዎች ጋር ሲነጻጸር ወንዶች ብዙ “ጤናማ አርአያ” እንደሌላቸው ታምናለች።
“ብዙ መርዛማ በሆኑ ገጸ ባህርያት እና እሳቤዎች የተሞላ ነው” ትላለች።
ደራሲዋ አክላም ልጆቿ “የትኛውንም ጠብ በራሳቸው የማይጀምሩ ነገር ግን ጠብ ካመጣችሁባቸው የማይፈሩ” እንዲሆኑ እንደምትፈልግ አስረድታለች።
አሁን ለህትመት የበቃውን ልብ ወለዷን በጻፈችባቸው ዓመታት ሦስት ልጆቿን ከመውለዷ በተጨማሪ ፤ ሁለቱንም ወላጆቿን በሞት ተነጥቃለች።
“ሐዘን እየቀነሰ ይሄዳል። ነገር ግን ልክ እንደ ማዕበል ነው አካሄዱ፤ እንደገናም ተመልሶ ይመጣል” ስትል ደራሲዋ ታስረዳለች።
ቺማማንዳ ሐዘን ምን ያህል አካላዊ ጫና እንደሚያደርስ በዚህ ወቅት ተረድታለች።
“ልቤ ከብዶ ነው የሚሰማኝ። ሰውነቴ የልቤን ክብደት መሸከም የማይችል መስሎ ተሰማኝ” ብላለች።
በአባቷ የልደት ቀን ከአራት ዓመታት በፊት ድንገት የሞተችው እናቷ ሐዘን አዲሱን ልብ ወለድ በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ደራሲዋ ታስረዳለች።
እናቷ ከሞተች በኋላ መጽሐፉን መጻፍ ስትጀምር “ስለ እናቴ የምጽፍ አይመስለኝ ነበር” ብላለች።
ነገር ግን ልትጨርስ ስትቃረብ መልሳ ስታነበው “ስለ እናቶች እና ሴት ልጆች” ብዙ እንዳለ ተረዳች።
“በአንዳንድ መንገዶች እናቴ ልብ ወለድ መጻፍ ወደምችልበት ወደዚህ ምትሃታዊ ቦታ መመለስ እንድችል በሩን እንደከፈተችልኝ በጣም ተሰምቶኛል” የምትለው ቺማማንዳ “እያጽናናችኝ እንደሆነ አስብ ነበር። ይህንን ማወቄ ስሜታዊ ያደረገኝ ነበር” ስትል ትገልጻለች።

ከፈጠራ ሂደት ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያላት ቺማማንዳ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ውይይቱ ወደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ሲቀየር ጠንከር ያለ አቋም ማንጸባረቋ የሚገርም አልነበረም።
በሰው ሰራሸ አስተውሎት የሚመረቱ የጽሁፍ ይዘቶችን ታሪኮች ልንላቸው እንደማይገባ እና ይህንን ቴክኖሎጂ በሰፊው ከተቀበልነው ሁላችንንም “በጣም ደደብ” ያደርገናል ብላለች ደራሲዋ።
ኤአይ የሰው ልጅ ፈጠራን ሊገድበው እንደሚችል የምትከራከረው ደራሲዋ “በምንም መንገድ ሊተካ እንደሚችል በጭራሽ ማሰብ የለብንም” ትላለች።
እንደ ሥራ ኢሜይሎችን ጠቅለል አድርጎ ለመጻፍ ኤአይን መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ትላለች።
“ጠቅለል አድርጎ መጻፍ የተወሰነ ደረጃ የፈጠራ ችሎታን፣ ምናብን እንዲሁም ብልህነትን የሚጠይቅ ነገር ነው። ይህንን ሥራ ሌላ አካል እንዲሠራ ከተውነው አእምሯችን ምን እንዲያደርግልን ነው የምንፈልገው?” ስትል ትጠይቃለች።