የሞት ወንበር

ከ 7 ሰአት በፊት

በአሜሪካ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ አንድ ሞት የተፈረደበት እስረኛ በአልሞ ተኳሾች በጥይት አርብ ዕለት ተገድሏል።

የደቡብ ካሮላይና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብራድ ሲግሞን የተሰኘው ፍርደኛ የሞት ቅጣቱ በጥይት ተፈጻሚ እንዲሆንበት ብይኑን ረቡዕ ዕለት ነበር ያስተላለፈው።

በሕጉ መሠረት የዓይን እማኞች ግድያው ሲፈጸም እንዲከታተሉ ተፈቅዶላቸዋል። ነገር ግን ከዚህ ጋር ተያይዞ ስጋቶች መነሳታቸው አልቀረም።

የሲግሞን ጠበቆች ደንበኛቸው በጥይት መገደልን መምረጡን ገልጸዋል። ነገር ግን ፍርደኛውን በጥይት ወይም ስቃይ በበዛበት ገዳይ መርፌ ለመሞት እንዲመርጥ የሚያስችለው በቂ መረጃ እንደሌለው እና አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ጠበቆቹ ተናግረው ነበር።

ሲግሞን የቀድሞ የሴት ጓደኛውን ወላጆች ግላዲስ እና ዴቪድ ካርክን በመኖሪያ ቤታቸው በቤዝቦል ዱላ ደብድቦ በመግደል ወንጀል ነው በአውሮፓውያኑ 2002 ሞት የተፈረደበት።

በአልሞ ተኳሾች የሚፈጸም የሞት ቅጣት

ደቡብ ካሮላይና ከአውሮፓውያኑ 1985 ጀምሮ ከ40 በላይ እስረኞችን በኤሌክትሪክ ወንበር እና በመርፌ በመግደል የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ አድርጋለች።

ግዛቲቷ ከሦስት ዓመታት በፊት አልሞ ተኳሾች በጥይት የሚገድሉበትን የሞት ቅጣት ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችል ሕግ አጽድቃለች።

ለዚህ ሕግ በተወሰነ መልኩ መነሻ የሆነው ግዛቲቷ በመርፌ ለመግደል የሚያስችላትን ገዳይ መድኃኒቶችን ማግኘት ባለመቻሏ መሆኑን መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ‘ዴዝ ፔናሊቲ’ የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የመረጃ ማዕከል ገልጿል።

ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ብዙም ሳይቆም የደቡብ ካሮላይና ማረሚያ ቤቶች መሥሪያ ቤት በአልሞ ተኳሾች መግደል የሚያስችለውን ሁኔታ ማሻሻሉም ተገልጿል።

መርፌ በመጠቀም እስረኞች ይገደሉበት የነበረው የሞት ክፍል በአሁኑ ወቅት በጥይት ለመገደል እንዲያመች ተደርጓል። መሥሪያ ቤቱ ፍርደኞች በጥይት በሚገደሉበት ወቅት ምሥክሮች እንዲገኙ ይደረጋል።

ሞት የተፈረደባቸው ግለሰቦች ወደ መግደያው ክፍል ከገቡ በኋላ የመጨረሻ ንግግራቸውን እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል። ታራሚው ሲግሞን በሞት ክፍሉ ውስጥ በሚገኘው ወንበር ከታሰረ በኋላ ጭምብል በራሱ ላይ ይጠለቃል።

በመቀጠልም አልሞ ተኳሾቹ በልቡ ላይ መሳሪያቸውብ ያነጣጥራሉ። የማረሚያ ቤቱ አዛዥ የሞት ቅጣት ትዕዛዙን ካነበቡ በኋላ ተኳሾቹ ጥይት መተኮስ ይጀምራሉ።

ከተኩሱ በኋላ ዶክተሮች ታራሚው መሞቱን ያረጋጡና ምስክሮች ክፍሉን ለቀው ይወጣሉ። አልሞ ተኳሾቹ የማረሚያ ቤቱ በጎ ፈቃደኞች መሆናቸው ተነግሯል።

በጥይት እንዲገደል የተበየነበት ብራድ ሲግሞን
የምስሉ መግለጫ,በጥይት እንዲገደል የተበየነበት ብራድ ሲግሞን

በስፍራው የሚገኙት የዓይን እማኞች እነማን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ጋዜጠኞች፣ የሕግ ባለሙያዎች እና የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት ቤተሰቦች ከሞት ክፍሉ ፊት ለፊት በመስታወት በተከፈለ ስፍራ ላይ ይቀመጣሉ። የዓይን እማኞቹ ታራሚው፣ ሲግሞን ሞቷል እስኪባል ድረስ መመልከት ይችላሉ።

በደቡብ ካሮላይና በሚገኘው ማክሊን በተሰኘው የጦር መሳሪያ ማሠልጠኛ አካዳሚ የጦር መሳሪያ መምህር የሆኑት ድሪው ሶፍት በጥይት ስለመገደል የሞት ቅጣት ላይ ያላቸውን ስጋት ለአሜሪካው የዜና ወኪል ኤንፒአር አጋርተዋል።

“አሰቃቂ እንደሚሆን አያጠራጥርም” የሚሉት መምህሩ “ሦስቱም ጥይቶች በታራሚው አንድ የአካል ክፍል ላይ የሚተኮሱ ከሆነ ትልቅ ክፍተት ይፈጠራል። ይህም ከፍተኛ የደም መፍሰስ ያስከትላል” ብለዋል።

በተጨማሪም የጥይት ፍንጣሪዎች ሰዎችን እንዲሁም የቤት ዕቃዎችን ሊመቱ እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት አጋርተዋል።

በአንድ ክፍል ውስጥ ግድያው በሚፈጸምበት ወቅት መርዛማ ጋዞች የመለቀቅ ስጋት እና ከፍተኛ ድምጽም በአልሞ ተኳሾቹ ላይ የመስማት ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል ብለዋል።

አርብ ምሽት በጥይት በተፈጸመው የሞት ፍርድ ሲግሞን በሰባት ደቂቃ ውስጥ መሞቱ በአንድ ዶክተር ተረጋግጦ ሂደቱ አብቅቷል።

በስፍራው በሲግሞን የተገደሉት ሰዎች የቤተሰብ አባላት፣ የፈርደኛው መንፈሳዊ አማካሪ እና ሌሎችም በምሥክርነት ተገኝተው ነበር።

ሲግሞን ከመገደሉ በፊት በሰጠው የመጨረሻ ቃል የዓይን እማኞቹ የሞት ቅጣት እንዲቀር እንዲጥሩ በመጠየቅ ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ “በጣም አላዊ” እንደነበር በመጥቀስ ድርጊቱ ምን ያህል የተሳሳተ መሆኑን በጸጸት ገልጿል።

የመጨረሻ ቃሉን ከሰጠ በኋላም ፊቱ እንዲሸፈን ተደርጎ አልሞ ተኳሾቹ በደረቱ ላይ በተቀመጠው የዒላማ ምልክት ላይ በማነጣጠር ሦስት ጊዜ ተኩሰው ፍርዱን ተፈጻሚ አድርገዋል።

በጥይት መግደል የሞት ፍርድ

በአልሞ ተኳሾች መገደል የሞት ፍርድ አመጣጥ

ከአውሮፓውያኑ 1977 ጀምሮ በአሜሪካ ሦስት ፍርደኞች በአልሞ ተኳሾች የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል። ሦስቱም የተፈጸሙት በዩታ ግዛት ሲሆን፣ የመጨረሻውም በአውሮፓውያኑ 2010 ነበር።

ነገር ግን በጥይት መገደል በአሜሪካ ረጅም ታሪክ አለው። በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ቢያንስ 185 ሰዎች በጥይት መገደላቸውን በክሊቭላንድ ሎው ሪቪው ላይ የወጣ ጽሁፍ ያመለክታል።

በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ሁለቱም ወገኖች በአልሞ ተኳሾች በጥይት መግደልን እንደ የአደባባይ ትርዒት በመጠቀም ወታደሮች ከትዕዛዝ እንዳያፈነግጡ ለማሸበሪያነት ይጠቀሙበት እንደነበር በደቡብ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ስሚዝ ይናገራሉ።

የማነቂያ ገመድ

የሞት ቅጣት አለም አቀፋዊ ገጽታ

የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው 144 አገራት የሞት ቅጣትን በሕግ ወይም በተግባር ተፈጻሚ ማድረግን አቁመዋል።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2023 አምነስቲ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት 1153 የሞት ቅጣቶች ተፈጻሚ ሆነዋል።

ይህ አሃዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በየዓመቱ በሞት ትቀጣለች ተብሎ የሚታመነውን ቻይናን ያካተተ አይደለም። አገራት የሚፈጽሟቸው የሞት ቅጣቶች በስቅላት፣ አንገትን በመቅላት፣ በኤሌክትሪክ ወንበር፣ በጥይት በመግደል እንዲሁም በመርፌ ነው።

አምነስቲ በአውሮፓውያኑ 2020 ቢያንስ ስምንት አገራት በጥይት መግደልን ተፈጸሚ እንዳደረጉ አስታውቋል። እነዚህም አገራት ቻይና፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሶማሊያ፣ ታይዋን እና የመን ናቸው።

“ከረጅም ጊዜ በፊት የሰው ልጅ ሊተወው የሚገባ ቅጣትን ለማስቀጠል የሚደረግ ሙከራ ነው” ሲሉ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአሜሪካ የምርምር ምክትል ዳይሬክተር ጀስቲን ማዞላ ተናግረዋል።

አክለውም “መንግሥት አንድን ግለሰብ የሚገድልበት ምንም ዓይነት ሰብዓዊ መንገድ የለም። በጥይትም ይሁን በገዳይ መርፌ፤ በስቅላትም ይሁን በኤሌክትሪክ ወንበር የሞት ቅጣት የመጨረሻው ጨካኝ፣ ኢሰብዓዊ፣ ሰውነትን የሚያወርድ ቅጣት ነው። ይህ የጭካኔ ምልክት እንጂ መፍትሄ አይደለም” ብለዋል።