ዶናልድ ትራምፕ

ከ 5 ሰአት በፊት

ለዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሌላ የተመሰቃቀለ ሳምንት ሆኖ አልፏል።

ዓለም በዶናልድ ትራምፕ እና በቮልዲሚር ዜሌንስኪ መካከል ያልተለመደ የተባለውን የተካረረ የቃላት ልውውጥ በቀጥታ ተከታትሎታል።

የዩክሬን መሪ መከላከያቸውን ለማጠናከር ወደ ተግባር የገቡትን የአውሮፓ አጋሮቻቸውን ጎብኝተዋል።

የሩስያ ቦምቦች ዩክሬንን ላይ በተከታታይ መዝነባቸውን ቀጥለዋል።

ነገር ግን እነዚህ ዋና ዋና ተዋንያን በሚቀጥለው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ እንደ አዲስ በሚካሄደው የአሜሪካ-ዩክሬን ንግግር ዙሪያ ምን እያሰቡ ይሆን?

የቢቢሲ ዘጋቢዎች የሳምንቱን ክስተቶች እንደሚከተለው ተንትነዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፡ የትራምፕ ተቃዋሚዎች ከሩሲያ ጋር እንደወገኑ በተናገሩበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ ሞስኮ ላይ ባልተለመደ መልኩ ትችት ሰንዝረዋል

ዶናልድ ትራምፕ እና ጄዲ ቫንስ በዜሌንስኪ ላይ ከፈጸሙት አሳፋሪ ጥቃት በኋላ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሰኞ ዕለት ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ እና የስለላ ድጋፍ አግደዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ይህም በጊዜ ሂደት ዩክሬን ራሷን በመከላከል አቅሟ ላይ መሠረታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። የትራምፕ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ ጎን መሰለፋቸው ላይ ጥያቄ አቅርበዋል።

አስተዳደሩ እርምጃውን የወሰደው የማዕድን ስምምነት ለመፈረም እና ፈጣን የተኩስ አቁም ለማድረግ በዜሌንስኪ ላይ ጫና ለመፍጠር መሆኑን በግልጽ አስታውቋል።

የትራምፕ መልዕክተኛ ጄኔራል ኪት ኬሎግ የአሜሪካን ወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጡን “በቅሎን [በእንጨት] ፊቷ ላይ እንደመምታት ነው… ትኩረታቸውን ለማግኘት ስለሆነ በጣም አስፈላጊ ነው… ቀጥሎ [ፕሬዚዳንቱ የሚፈልገውን] ማድረግ የእነሱ ጉዳይ ይሆናል” ሲሉ ገልጸውታል።

ከዚህ ሁሉ እጅ ጥምዘዛ በኋላ፣ በሚቀጥለው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ ከዩክሬናውያን ጋር ንግግር እንደሚኖር በአንዳንድ የትራምፕ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቡድን መገለጹ ሳምንቱን ይበልጥ በሚያስማማ ሃሳብ እንዲያበቃ አድርጓል።

በዩክሬን ላይ እየጠነከረ ያለውን የቦምብ ጥቃት ለመከላከል ቀደም ሲልም ከፍተኛ የነበረውን የሞስኮን ማዕቀብ እንደሚያጠናክሩት ትራምፕ አርብ ዕለት ማሳወቃቸው ለሩስያ ያልተለመደ ትችት ነበር።

ከዚህ ውጪ ግን ይህ አስተዳደር አጋር ነው የተባለውን ደጋግሞ እየወቀሰ፣ ነገር ግን ተቃዋሚውን ከመተቸት የተቆጠበ ነው።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የአውሮፓ ሰላም አስከባሪ ኃይል በዩክሬን ሊኖር አይገባም ሲሉ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስን ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በምዕራባውያን ዘንድ “ለመደራደር ቦታ የሌለው የጥላቻ ዒላማ” ሲሉ ገልጸውታል።

ብሩስ ምንም እንኳን ትራምፕ ዘሌንስኪን በተመለከተ “ለሰላም ዝግጁ አይደለም” ማለታቸውን ደጋግመው ቢናገሩም፤ በውጪ አገራት መሪዎች ወይም ሚኒስትሮች ንግግር ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ በመግለጽ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቭላድሚር ፑቲን

ሩሲያ፡ በዩክሬን ላይ የሚያካሄዱት ተከታታይ የአየር ጥቃት በቀጠለበት በዚህ ወቅት የምዕራባዊያን አለመግባባት በደስታ እየተከታተሉ ነው

የትራምፕ የማዕቀብ ዛቻ እስኪሰማ ድረስ፣ ጫና ሁሉ በኪዬቭ ላይ ብቻ የመሰለበት ሌላ ሳምንት ነበር።

ይህም ሩሲያ የማጥቃት ፍላጎቷን ለመግራት ኢምንት ምክንያት እንኳ አላሳየችም።

ወረራው ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ አሜሪካ የምትሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ እና የስለላ መረጃን ማገዷ ለዩክሬን ትልቁ ኪሳራ ሲሆን ለሩሲያ ደግሞ ትልቅ አጋጣሚ ነው።

በዩክሬን የተፈጸሙ ጥቃቶች መቀጠላቸው ሞስኮ ጦርነቱን በተለመደው መልኩ ለመቀጠል ደስተኛ እንደሆነች ይጠቁማሉ ።

የመጀመሪያው “የልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ዓላማዎችን ማሳካትና ተጨማሪ የዩክሬን መሬት መያዝን አጥብቆ መቀጠሉን ያሳያል።

የዩክሬን ደጋፊዎች በድርድር ወይም በሰላም አስከባሪ ኃይል በኪየቭ ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል ያደረጉት ጥረት ፍሬ አላፈራም።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ሳምንት የትራምፕ አሜሪካ ከአሁን በኋላ “ከእኛ ጎን ላትቆም ትችላለች” ማለታቸው ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጆሮ መልካም ሙዚቃ ሆኖላቸዋል።

ፑቲን ቁጭ ብለው በምዕራቡ ዓለም ውስጥ በሚታዩት ክፍተቶች የሚዝናኑበት ጊዜ ነው። ለአስር ዓመታት ባይሆን እንኳን ለዓመታት ሲሠሩበት የነበረ ሁኔታ ነው።

ይህንንም ያሳኩት ደግሞ በጦር ሜዳ በተተኮሰው ጥይት ሳይሆን የዩክሬን ትልቁ አጋር ባደረገችው አስደናቂ ለውጥ ነው።

የፊታችን ማክሰኞ የዩክሬን እና የአሜሪካ ተወካዮች በሳዑዲ አረቢያ ለመነጋገር ይቀመጣሉ። ሩሲያ ውይይቱን በራስ መተማመን እና በቅርበት ትከታተለዋለች።

ቭላድሚር ዜለንስኪ

ዩክሬን፡ ስሜታቸው ከተሰበረበት ሳምንት በኋላ ዜለንስኪ ከአሜሪካ ጋር አዲስ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል

ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ እየገለፁ፣ የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቀጥል ሲማፀኑ ለነበሩት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት በጣም አሳዛኝ፣ ስሜታዊ እና ከባድ ሳምንት ነበር።

ከትራምፕ ጋር ባደረጉት አስደናቂ የኦቫል ኦፊስ የተካረረ የቃላት ልውውጥ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ዕርዳታ እና የስለላ መረጃ ልውውጥ አቁማለች።

ለዩክሬን ቅርብ የሆኑ አንድ ምንጭ “አየሩ በክህደት ሽታ ተሞልቷል። ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ መላው አገሪቱ ይህ ይሰማቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ የትራምፕን “ግልጽ የይቅርታ” ጥያቄ አልተቀበሉም።

ይልቁንም ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ደብዳቤ በመጻፍ የዋይት ሐውስ ውይይታቸውን “አሳዛኝ” ሲሉ ጠርተዋል።

ጉዳቱን ለመቋቋም እና የአውሮፓን ድጋፍ ለማግኘት ዜሌንስኪ እንደገና መሥራት ጀምረው ነበር።

የትብብር ማሳያዎችን ቢያረጋግጡም ሲጠብቁት የነበረው ጠንካራ ወታደራዊ ቃል ግን አልተገባላቸውም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዜሌንስኪ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች በባህር እና በአየር ላይ የተወሰነ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሃሳቡን ደግፈዋል።

የዩክሬን እና የአሜሪካ ልዑካን በሚቀጥለው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ ይነጋገራሉ። ወደ ሰላም የሚወስደው መንገድ በእርግጠኝነት አይታወቅም።

ምንም እንኳን መሰናክሎች ቢኖሩትም ለፕሬዚዳንቱ ቡድን ቅርብ የሆኑ ምንጭ “ከሦስት ዓመት በፊት ሊገደሉ ይችሉ የነበሩ ቢሆንም ግን በኪዬቭ ለመቆየት ወስነዋል። የበለጠ ጫና እየደረሰባቸው በሄደ ቁጥር እየጠነከሩ ይሄዳሉ” ብለዋል።

ኢማኑኤል ማክሮን

አውሮፓ፡ የአሜሪካ ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ ፈረንሳይ ኒውክሌሯን ለመከላከያነት ልትጠቀም ትችላለች?

ብዙ የአውሮፓ ስብሰባዎች ስለነበሩ ሁሉንም ለመከታተል አስቸጋሪ ነበር፤ ሌሎች ስብሰባዎችም ይቀጥላሉ።

የአውሮፓ መሪዎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሲተማመኑ የቆዩበት ወታደራዊ ከለላ በድንገት ሊቀየር እንደሚችል ተረድተዋል።

አውሮፓ ዩክሬንን መርዳት አለባት የሚል ሰፋ ያለ መግባባት አለ።

ፈረንሳይ እና እንግሊዝ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ግንባር ላይ የሚሰማራ “የፍቃደኞች ጥምረት” ሃሳብን እያቀረቡ ነው።

ሩሲያ ሃሳቡን ብትጠላውም ግን ማክሮን ማክሰኞ ዕለት የጦር አዛዦችን በመሰባሰብ ዕቅድ ለማውጣት ይጥራሉ።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን “ግልጽ እና ወቅታዊ አደጋ” ብለው ከሚጠሩት ስጋት አውሮፓ እንዴት ራሷን ትጠብቃለች የሚለውን ብዙዎች እየጠየቁ ነው ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ለመርዳት ካልፈለገች “ዝግጁ መሆን አለብን” ብለዋል ማክሮን።

የአውሮፓ ኅብረት መከላከያውን ለማጠናከር ባለ ብዙ ቢሊዮን ዩሮ ዕቅድ ላይ እየተነጋገረ ነው።

የፈረንሳይ የኒውክሌር ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔዎች የሚሰጡት በፓሪስ ቢሆንም ማክሮን ያንን ተቀብለዋል።

ይህ ደግሞ የአውሮፓ የመከላከያ ችግር ዋና ማዕከል ነው።

ያለ አሜሪካ ድጋፍ የአውሮፓ አገራት ለየብቻቸው ኃብታቸውን አሰባስበው እርስ በእርሳቸው ሊተማመኑ ይችላሉን?

እንደ ሊቱዌኒያ ላሉ ትናንሽ አገሮች ይህ ምንም ምርጫ የለውም።

ክርክሩ ተጀምሯል። የፖላንድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ተስክ “የራሳችን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቢኖረን” በማለት የበለጠ ደህንነት እንደሚሰማቸው በግልጽ ተናግረዋል።