የአሜን ቤተሰቦች እና ጓደኞች በሞቱ የተሰማቸውን ሐዘን ተሰባስበው ገልፀዋል

ከ 5 ሰአት በፊት

በስኮትላንድ ግላስጎው አሜን ተክላይ ከተባለ ታዳጊ ግድያ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የ14 እና የ15 ዓመት እድሜ ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።

የ15 ዓመቱ አሜን ረቡዕ ዕለት በከተማው በሚገኘው ሴይንት ጆርጅ ክሮስ አካባቢ በክላሬንደን ጎዳና ላይ በተፈፀመ ጥቃት በጽኑ ቆስሎ ተገኝቷል።

ምንም እንኳ የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች በስፍራው ቢደርሱም ሕይወቱ እዚያው ማለፉ ተገልጿል።

የስኮትላንድ ፖሊስ ሁለት ታዳጊዎች ከግድያው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ምርመራው መቀጠሉን አስታውቋል።

ፖሊስ ግድያው ከሌላ ነገር ጋር እንደማይያያዝ እና መርማሪዎች ለግድያው መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን ለማጣራት “ሁሉንም አቅጣጫ እየመረመሩ” መሆናቸውን ተናግሯል።

ኤርትራዊ የሆነው አሜን ከአባቱ ጋር በግላስጎው ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ በእንግሊዝ ‘የመቆየት መብት’ ተሰጥቶት እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

የ17 ዓመቷ እህቱ ዴሊና ተክላይ “አሜን የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የማግኘት እና የቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ ዶክተር ወይም መሐንዲስ የመሆን ምኞት ነበረው” ብላለች።

አሜን “ወንድሜ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ነበር” ስትል ለቢቢሲ ስኮትላንድ ኒውስ ተናግራለች።

አክላም “በጣም ተወዳጅ ልጅ፣ በጣም ደግ እና በጣም ብሩህ ነበር” ብላለች።

አሜን በጆርዳን ሂል በሚገኘው ሴይንትቶማስ አኩዊናስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ክሌር ማኪንሊ ሞቱ “ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አስደንጋጭ” ነበር ብለዋል።

የስኮትላንድ ፖሊስ በአሜን ግድያ ላይ ሰፊ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል።

ሱፐርኢንቴንደንት ቼሪል ኬሊ እንዳሉት “መልሱ ያለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ነው” ካሉ በኋላ ባልደረቦቻቸው የመንገድ ላይ ካሜራዎችን እየተመለከቱ እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ ጥያቄዎችን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም “በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ሀሳባችን ሁሉ ከአሜን ቤተሰቦች እና ወዳጆች ጋር ነው። ለእነሱ ልዩ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።” ብለዋል።

ፖሊስ ግድያውን በሚመለከት መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው ለዚህ ምርመራ ተብሎ በተከፈተው የመረጃ መቀበያ በኩል ጥቆማውን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።