የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ

ከ 4 ሰአት በፊት

ጀስቲን ቱሩዶን ለመተካት ያሸነፉት ቀጣዩ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አለመረጋጋት የገጠማትን አገር ሲረከቡ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር አገራቸው የገባችውን የንግድ ጦርነት ለማሸነፍ ቃል ገብተዋል።

የቀድሞው የብሄራዊ ባንክ ገዢ ሦስት የሊበራል ፓርቲ ተቀናቃኞቻቸውን በማሸነፍ የሥራ መልቀቂያ ያስገቡትን ጀስቲን ቱሩዶን ይተካሉ።

የ59 ዓመቱ ማርክ ካርኒ ድላቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ካናዳ ላይ ታሪፍ የጣሉትን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመወረፍ “አሜሪካ ስህተት ልትሰራ አይገባም” ብለዋል።

“እንደ ሆኪ ጨዋታ በንግድም ካናዳ ታሸንፋለች” ብለዋል።

በሚቀጥሉት ቀናት ቃለ መሀላ ፈፅመው አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ሲሆን ለቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ሊበራል ፓርቲን ይመራሉ ተብሏል።

ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ ቀደም በሕዝብ ምርጫ የሚያዙ ስልጣኖችን ይዘው አያውቁም።

የፓርቲው የስልጣን ፉክክር የጀመረው ባለፈው ጥር ፕሬዝዳንት ቱሩዶ 10 ዓመት ከሚቃረብ የስልጣን ቆይታ በኋላ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።

ቱሩዶ በኑሮ ውድነት እና በመኖሪያ ቤት ቀውስ ምክንያት ሕዝባዊ ተቀባይነታቸው በመቀነሱ ከስልጣን እንዲለቁ ከፓርቲያቸው ውስጣዊ ግፊት ገጥሟቸዋል።

እሁድ ምሽት በተካሄደ ምርጫ ማርክ ካርኒ 85.9 በመቶ ድምፅ በማግኘት የቅርብ ተፎካካሪያቸውን የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር ክርሲታ ፍሪላንድን አሸንፈዋል።

በዚህ ምርጫ 150 ሺህ ሰዎች ድምፅ መስጠታቸውን ፓርቲው አስታውቋል።

በእንደራሴዎች ምክር ቤት አናሳ ወንበር ያለውን መንግሥታቸውን የሚመሩት ካርኒ፤ አጠቃላይ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባሉ አሊያም ተቀናቃኞቻቸው በሚቀጥለው ወር እምነት በማጣት ድምፅ ከስልጣን ሊያሰናብቷቸው ይችላሉ።

ገዥው ሊበራል ፓርቲ ከቱሩዶ መልቀቂያ ማስገባት በኋላ ያልተጠበቁ የፖለቲካ ለውጦችን ያስተናገደ ሲሆን፤ በተለይም አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የንግድ ዛቻ እና ካናዳን የመጠቅለል ፍላጎት ካናዳዊያንን አስደንግጧል።

የተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር የድል ንግግር በአብዛኛው የአሜሪካ ትልቋ የንግድ አጋር በሆነችው ካናዳ ላይ ትራምፕ በጣሉት “ያላግባብ ታሪፍ” ላይ ያተኮረ ነበር።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በካናዳ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጥላለች።

ካናዳም ለእርምጃው ምላሽ በመስጠት በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ የጣለች ሲሆን፤ የአሜሪካ እርምጃ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመጣል የተወሰደ ነው የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ካርኒ በንግግራቸው ትራምፕ “ካናዳዊያን ሠራተኞችን፣ ቤተሰቦችን እና ንግዶችን እያጠቁ ነው” ብለዋል።

ታዳሚው አሜሪካንን የሚቃወም ድምፅ ሲያሰማ “እንዲሳካለት አናደርግም” ሲሉ አክለዋል።

ማርክ ካርኒ መንግሥታቸው አሜሪካ ክብር እስክታሳያቸው ድረስ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የተጣለው ታሪፍ እንደሚፀና ተናግረዋል።

የካናዳ ኢኮኖሚ ከአሜሪካ ጋር ባለው ትልቅ የንግድ ልውውጥ የተመሰረተ ሲሆን፤ በትራምፕ የሚጣለው ታሪፍ ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ ከሆነ ኢኮኖሚው የውድቀት ስጋት ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል።