
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚኒስትሮቻቸውን ሰብስበው በአገሪቱ ውስጥ እና በመላው ዓለም እያነጋገረ ባለው በኢላን መስክ እና የመንግሥት ወጪን እንዲሁም ሠራተኞችን ለመቀነስ በወሰደው እርምጃ ላይ ተወያይተዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ውይይት የሞቀ እንደነበረ አመልክተዋል።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው በስብሰባው ላይ መስክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በስቴት ዲፓርትመንት ውስጥ የሚጠበቀውን ያህል ሠራተኞችን አልቀነሱም በማለት ከሷቸዋል።
እንደ ጋዜጣው ከሆነ፣ ባለሃብቱ መስክ የአሜሪካ ዋነኛው ዲፕሎማት ሩቢዮ ያከናወኗቸውን ሥራዎች በመተው “ቴሌቪዥን ላይ ጥሩ” እንደሆኑ በመጥቀስ ተችቷቸዋል።
በተጨማሪም ቢሊየነሩ ከትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሾን ደፊ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበረ። ሚኒስትሩ በመስክ የሚመራው የመንግሥት ተቋማት ብቃትን የሚቆጣጠረው መሥሪያ ቤት (ዶጅ) የአየር በረራ ተቆጣጣሪዎችን ለመቀነስ መሞከሩን በማንሳት ተወዛግበዋል።
በአሜሪካ ፌደራል የአቪዬሽን አስተዳደር ስር ያሉት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እጥረት እንዳለ የተነገረ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱም ትራምፕ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ሁለት አውሮፕላኖች በመከስከሳቸው ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል።
በስብሰባው ላይ በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው መካከል የነበረውን ውዝግብ ከሰሙ በኋላ ሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጣልቃ በመግባት በመስክ የሚመራው መሥሪያ ቤት የሚያከናውነውን እንደሚደግፉ፣ ነገር ግን ሚኒስትሮቹ ሥራውን እንዲመሩ የመስክ መሥሪያ ቤት ደግሞ እንዲያማክር አዘዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ የካቢኔ ስብሰባው ለማርኮ ሩቢዮ “ግልጽ እና ውጤታማ ውይይት” የተካሄደበት እንደነበር ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግሯል። ነገር ግን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
በችኮላ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ የመስክ መሥሪያ ቤት በማማከር እንዲገደብ ማድረጋቸው በአስተዳደራቸው የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የስፔስኤክስ እና የቴስላ ባለቤት እንዲያስፈጽም የሰጡትን የመንግሥት ወጪ ቅነሳ ሥልጣን ለመገደብ መወሰናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።
ከሚኒስትሮቻቸው ጋር ያደረጉት ስብሰባን ይዘት በተመለከተ ትራምፕ አስተያየታቸውን የሰጡት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ ከዘገቡ በኋላ ትሩዝ ሾሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው።
በዚህም ባለሥልጣኖቻቸው ከመስክ መሥሪያ ቤት ጋር በጋራ በመሆን “በወጪ ቅነሳ እርምጃዎች” ላይ እንዲሠሩ ትዕዛዝ ማስተላላፋቸውን አመልክተዋል።
“ሚኒስትሮቹ እንደተገነዘቡት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩትን ሰዎች ሲያውቁ እና ሲረዱ፣ የሚቀጥለውን እና የሚቀነሰውን በመለየት ትክክለኛውን እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ” በማለት ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
- ኢሎን መስክ ‘ወጪ ቅነሳ’ በሚል የአሜሪካ መሥሪያ ቤቶችን “ማተረማመሱን” አስተባበለ12 የካቲት 2025
- ኢላን መስክ የአሜሪካ ግምጃ ቤት መረጃዎችን እንዳይመለከት በፍርድ ቤት ታገደ9 የካቲት 2025
- ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ምን ያህል እርዳታ ስታገኝ ነበር? ትራምፕ ዩኤስኤይድን መዝጋት ይችላሉ?6 የካቲት 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ኢላን መስክ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ የተባለውን የመንግሥትን ወጪ እና ሠራተኞችን የመቀነስ ኃላፊነት ከያዘ በኋላ በበርካታ ተቋማት ላይ በተግባር እና በመልዕክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከባድ ተጽእኖን አሳርፏል።
በዚህም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሱ የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ተሽመድምደዋል ወይም ከሥራ ውጪ ሆነዋል።
በተጨማሪም የመስክ መሥሪያ ቤት ከይፋዊ የመንግሥት የኢሜይል አካውንት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የፌደራል መንግሥቱ ሠራተኞች በላከው መልዕክት የወራት ደሞዛቸውን በመቀበል ሥራቸውን እንዲለቁ ሃሳብ አቅርቧል።
እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱ ሠራተኞች በየሳምንቱ ስላከናወኗቸው ሥራዎች ሪፖርት እንዲያቀርቡ ካልሆነ ግን ከሥራ የመሰናበት ዕጣ እንሚገጥማቸው አሳውቆ ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት ሠራተኞቻቸው ለኢሜይል መልዕክቱ መልስ እንዳይሰጡ አዘዋል።
በተጨማሪም የመስክ መሥሪያ ቤት አዲስ የተቀጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች በሙሉ ከሥራ እንዲሰናበቱ አዝዟል። ለዚህም ምክንያቱ ሠራተኞቹ በቅጥር የሙከራ ጊዜ ላይ ስለሚሆኑ ሙሉ የሲቪል ሰርቪስ መብት ስለማይኖራቸው ነው።
የአሜሪካ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ደኅንነት ተቆጣጣሪን የመሳሰሉ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ግን ሠራተኞቻቸው አስፈላጊ መሆናቸውን በመግለጽ ትዕዛዙን ውድቅ አድርገውታል።
ትራምፕ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር ነበራቸው እና የተጋጋለ ምልልስ ስለተካሄደበት ስብሰባ አርብ ዕለት በጽህፈት ቤታቸው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ “ውዝግብ አልነበረም” ብለዋል። ጨምረውም ለማርኮ ሩቢዮ እና ለኢላን መስክ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን ሐሙስ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ላይ ለሚኒስትሮቻቸው ተጨማሪ ሥልጣንን በመስጠት የመስክን ጫና ገለል እያደረጉ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው እየተባለ ነው።
እንዲሁም ይህ እርምጃቸው ከካቢኔ አባሎቻቸው በተለየ የሴኔት ምርመራ እና ይሁንታን ሳያገኝ ከፍ ያለ ሥልጣን እንዲኖረው ባደረጉት ኢላን መስክ ምክንያት ሊገጥማቸው ከሚችለው የሕጋዊነት ጥያቄ እራሳቸውን ለመከላከል የፈጠሩት ዘዴ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።
ይህንን ጉዳይ እየተከታተሉ ያሉ በርካታ የፌደራል ዳኞች ከወዲሁ በኢላን መስክ ሥልጣን ላይ ያላቸውን ስጋት እየገለጹ ነው።
መስክ እና ትራምፕ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ወሳኝ አጋርነትን ፈጥረዋል። መስክ የዓለም ቁጥር አንድ ሃብታም እንዲሁም ትራምፕ የምድራችን ኃያሉ ፖለቲከኛ በመሆናቸው ተጽእኗቸው ቀላል የሚባል አይደለም።
ነገር ግን የሁለቱ ጥምረት ምን ያህል ጠንክሮ ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ በርካታ መላምቶችን ዋሽንግተን ውስጥ ሲያስነሳ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ሲሰነዘሩ የነበሩት ትንበያዎች ብዙውን ጊዜ በሁለቱ ኃያላን መካከል እየታደሱ የሚሄዱ ምልክቶች እያሳዩ በተከታታይ ሲቀጥሉ ቆይተዋል።
ውዝግብ ነበረበት ከተባለው የካቢኔ ስብሰባ እና ትራምፕ መስክ በመንግሥት ተቋማት ላይ የነበረውን ፈላጭ ቆራጭ ሥልጣን ለሚኒስትሮቻቸው ያጋሩበት ውሳኔን ተከትሎም ሁለቱ ግለሰቦች የሚለያዩ አይመስልም።
አርብ ምሽት መስክ የሳምንቱ መጨረሻን ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለማሳለፍ ፍሎሪዳ ውስጥ ወደሚገኘው የትራምፕ ማራላጎ ቅንጡ የመዝናኛ እና የመኖሪያ ሰፈር በፕሬዝዳንታዊው አውሮፕላን ኤር ፎርስ ዋን ሲሳፍር ታይቷል።
በካቢኔው ስብሰባ ወቅት የተነሳው አቧራ ምናልባትም በትራምፕ እና በመስክ መካከል ባለው ግንኙነት የመጀመሪያው ስንጥቃት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ትራምፕ አሁንም የመስክን መጠነ ሰፊ የለውጥ እርምጃ እና ግቦቹን እንደሚደግፉ የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ።