የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች በእግር፣ በመኪና እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች ሕገወጥ ስደተኞች ድንበሩን እንዳያቋርጡ ሌት ተቀን ክትትል ያደርጋሉ
የምስሉ መግለጫ,የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች በእግር፣ በመኪና እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች ሕገወጥ ስደተኞች ድንበር እንዳያቋርጡ ሌት ተቀን ክትትል ያደርጋሉ

ከ 5 ሰአት በፊት

ዓይን አፋሩ እና በዝግታ የሚናገረው ኢትዮጵያዊው ዳዊት (ስሙ ተቀይሯል) በፓላንድ በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ ነው ቢቢሲ ያገኘው።

ዳዊት ራሱን ከፖላንድ ቅዝቃዜ ለመከላከል ቢጫ እና ጥቁር ባለ ፀጉር ኮት ለብሷል።

ከአገሩ የወጣው ከግዳጅ ውትድርና ለማምለጥ ብሎ መሆኑን የሚናገረው ዳዊት በሩሲያ እና በቤላሩስ አድርጎ ወደ ፖላንድ ለመምጣት ለደላሎች ሰባት ሺህ ዶላር መክፈሉን ይናገራል።

ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ በቤላሩስ ድንበር በኩል ወደ ፖላንድ ያቋረጡ ስደተኞች ቁጥር በሺህዎች የሚቆጠር ነው።

ዳዊትም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

የፖላንድ እና የቤላሩስ የድንበር አካባቢ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነው። በደን መሸፈኑ ብቻ ሳይሆን በእሾሀማ ሽቦ ታጥሯል።

ይህ የቢያሎዊዛ ጫካ ተብሎ የሚታወቀው ታሪካዊ ደን በዩኔስኮ በቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን፣ ጥበቃ ይደረግለታል።

አሁን ግን ስደተኞች ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት ለመግባት እንደ መተላለፍያ መንገድነት ይገለገሉበታል።

በጫካው ውስጥ የፖላንድ መንግሥት ስደተኞችን ወደ አገሩም ሆነ ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ ለመከላከል በሚል በ2022 ያስገነባው 193 ኪሎ ሜትር የሚረዝም አጥር ይገኛል።

የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች ቀን ተሌት በእግራቸው፣ የጦር መሳሪያ በተደገነባቸው መኪኖች፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በመጠቀም ምድሩን እና ሰማዩን ይቃኛሉ።

የድንበር ጠባቂ መኮንን የሆነው ሚካል ቡራ ከአምስት ሜትር በላይ ርዝመት ያለውን አጥር እያሳየ፣ ሕገወጥ ስደተኞችን ለመከላከል በሚል በሚገባ የተደራጀ አጥር ነው ይላል።

አጥሩን በፀሐይ ሲመለከቱት ለመዝለል የሚሞክሩትን ለመከላከል ያለሙ የሾሉ ብረቶች፣ እንደ እሾህ የሰሉ ሽቦዎች ነጸብራቅ ዓይንን ያጥበረብራሉ።

“ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ አንድ እርምጃ ቀድመን መገኘት አለብን።ከጠላቶቻችን አንድ እርምጃ የቀደምን መሆን አለብን” ይላል ቡራ።

ቡራ የቤላሩስ የድንበር ጠባቂዎች ላይ ጣቱን ይቀስራል። እነርሱንም “ጠላት” አድርጎ ነው የሚመለከታቸው።

“የቤላሩስ ድንበር ጠባቂዎች ከሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ጋር ይሠራሉ” ሲል ይወነጅላቸዋለች።

“ድንበሩን በሕገ ወጥ መንገድ የሚሻገሩበትን ቦታ ይጠቁሟቸዋል። እንደ መሰላል እና የሽቦ መቁረጫዎች የመሳሰሉ መሳሪያዎችን ይሰጧቸዋል” ይላል።

የፖላንድ ባለሥልጣናት የስደተኞቹ ሕገወጥ ባህሪንም በማንሳት ይወቅሳሉ።

በታኅሣሥ 2024 የወጣው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት የፖላንድ ባለሥልጣናት “በሕገወጥ መንገድ እና አንዳንድ ጊዜ በኃይል ጭምር ወደ አገራቸው ለመግባት የሚሞክሩትን ስደተኞች የጥበቃ እና የከለላ ፍላጎታቸውን ከግንዛቤ ሳያስገቡ ወደ ቤላሩስ እንዲመለሱ ያስገድዷቸዋል” ብሏል።

ዳዊት እና የቢቢሲ ጋዜጠኛ
የምስሉ መግለጫ,ዳዊት ፖላንድ ውስጥ ለመቆየት የወሰነ ቢሆንም፣ በርካታ የፖላንድን ድንበር የሚያቋርጡ ስደተኞች ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት ያልማሉ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የቤላሩስ የ2020 ምርጫን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ጠንከር ያለ ማዕቀብ ከጣለ በኋላ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ከመካከለኛው ምሥራቅም ሆነ ከአፍሪካ የሚመጡ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ ፖላንድ ድንበር የሚያደርጉትን ጉዞ እንደማያስቆሙ ተናግረዋል።

ሉካሼንኮ በ2021 ለቢቢሲ “ነግሬያቸዋለሁ [ለአውሮፓ ኅብረት] ድንበሩን ለማቋረጥ የሚሞክሩ ስደተኞችን አላስርም። መምጣታቸውን የማያቋርጡ ከሆነ አላስቆማቸውም። ምክንያቱም ወደ እኔ አገር አልመጡም። ወደ እናንተ አገር ነው የመጡት” ብለዋል።

በዚህ በፕሬዝዳንቱ ቸልተኝነት የተሞላበት ንግግር ብቻ ሳይሆን፣ ቤላሩስ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት ይህን መንገድ እንዲጠቀሙ ታበረታታለች በሚል ትከሰሳለች።

በ2021 በሉካሼንኮ መንግሥት የሚመራ የጉዞ ወኪል ወደ ድንበሩ የሚመጡትን ፍልሰተኞች ጉዞ በማቀላጠፍ በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ተጥሎበታል።

ይህ የጉዞ ወኪል በ2021 ለቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለበርካታ ኢራቃውያን፣ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ጨምሮ፣ ለአደን ቱሪዝም በሚል ቪዛ መጠየቁን ቢቢሲ ተመልክቷል።

ቪዛው ሰዎቹን ለፖላንድ በጣም ቅርበት ባለው እና ጥበቃ በሚደረግለት የቢያሎዊዛ ደን አካባቢ የመቆየት ሕጋዊ መብት ይሰጣቸዋል።

የቤላሩስ የድንበር ባለሥልጣን ስደተኞች ድንበሩን እንዲያቋርጡ ይረዳሉ መባላቸውን አስተባብለው ለቢቢሲ ከድንበር ደኅንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ቀደም ሲል የሰጡትን መግለጫ ጠቅሰዋል።

መግለጫው “የስደቱ ሁኔታ ከተባባሰ ጊዜ ጀምሮ ለአውሮፓ ኅብረት አገራት የአገሪቱ የድንበር ኮሚቴ የገንቢ ውይይት አስፈላጊነትን እና ሕገወጥ ስደትን ከመዋጋት ጋር የተያያዙ ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ፕሮጀክቶችን የማስቀጠል አስፈላጊነት በመግለጽ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል” ይላል።

አክሎም “እንደ አለመታደል ሆኖ ጎረቤት የአውሮፓ ኅብረት አገራት ገንቢ ውይይት ከማድረግ ይልቅ በድንበሩ አካባቢ ወታደራዊ ኃይልን ማጠናከር፣ እሰጥ አገባን የመረጡ ሲሆን የድንበር ትብብር ጉዳዮችን ችላ ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ እየተፈጠረ ያለውን የስደት ችግር ለመፍታት ስር ነቀል ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው።”

ፖላንድ ከቤላሩስ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር፣ በእሾሀማ ሽቦ አጥራለች
የምስሉ መግለጫ,ፖላንድ ከቤላሩስ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር፣ በእሾሀማ ሽቦ አጥራለች

የፖላንድ-ቤላሩስ ድንበር ግንኙነት

በፖላንድ እና በቤላሩስ ድንበር በኩል የስደተኞች ፍሰት መጨመር የሚያሳየው በሁለቱ አገራት በኩል ድንበሩን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት በተሰጣቸው አካላት መካከል ያለው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ መሸርሸሩን ነው።

“ከጥቂት ዓመታት በፊት. . . እናወራቸው ነበር፣ አብረን ሲጋራ እናጨስ ነበር። አሁን ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም” ይላል ቡራ።

ምንም እንኳ ከፖላንድ ወገን ጥረቱ ቢጨምርም፣ በ2024 ድንበሩን ለማቋረጥ ወደ 30,000 የሚጠጉ ሙከራዎች መደረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም ከ2021 ወዲህ የታየ ሁለተኛው ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል ።

በርካታ ስደተኞች አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት ገጥሟቸውም ቢሆን ድንበሩን ማቋረጥ ይሳካላቸዋል።

“ከሮጥክ በውሻ ነው የሚያባርሩህ”

ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነው። መልክዓ ምድሩም ለእግር ጉዞ አመቺ አይደለም።

በድንበሩ ዙሪያ 5.5 ሜትር ርዝመት ያላቸው የሽቦ አጥሮች አለ። ይህንን ዘሎ ለመሻገር ለሚሞክር ለማንኛውም ሰው ርህራሄ የላቸውም።

‘ዊ አር’ የተሰኘው የቁጥጥር ቡድን እንደገለጸው ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ 89 ሰዎች ሞተዋል።

ምንም እንኳ የቤላሩስ ባለሥልጣናት ለስደተኞቹ ድንበሩን ለማቋረጥ የሚረዳቸው ቁሳቁሶች ቢሰጧቸውም ከግዛታቸው በፍጥነት ወጥተው ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት እንዲገቡ በሚል በውሾች ያሳድዷቸዋል።

በክረምት ያለው ሁኔታ ደግሞ አይጣል ነው። ካለው ከፍተኛው ቅዝቃዜ የተነሳ የገዛ አካል አይታዘዝም፤ በድን ይሆናል።

ከድንበር ተቆጣጣሪዎቹ ለማምለጥ “ከሮጥክ ውሻ ከኋላህ ይለቅቁብሃል” ይላል ዳዊት።

“አንገታቸው እና እግራቸው ላይ የተነከሱ ሰዎችን አይቻለሁ።”

ኦልጋ
የምስሉ መግለጫ,ኦልጋ ከቤላሩስ ድንበሩን አቋርጠው ወደ ፖላንድ የሚገቡ ስደተኞችን ለመርዳት የተቋቋመው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በጎ ፈቃደኛ ነች

ኦልጋ ለአዲስ መጤዎች እርዳታ ለመስጠት በጫካው ዙሪያ የሚሠራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባ ናት።

የምታገኛቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ በፍርሃት የተረበሹ እና የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።

“በአጥሩ ሽቦ ምክንያት ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ከአጥር ላይ ሲዘሉ ክንዳቸው እና እግራቸው ይሰበራል።”

በአቅራቢያው ካለ መንደር ዳርቻ፣ ከበጎ ፈቃደኛ የተሰጠ ባለ ሦስት ክፍል ቤት ይገኛል።

በስደተኞች መጉረፍ የተናደዱት የአገሬው ሰዎችን ጥቃት በመፍራት ቤቱ በምስጢር የተያዘ ነው።

ቤቱ በተለያዩ ቁሳቁሶች የተሞላ ነው። ለብርድ የሚሆኑ ልብሶች፣ ምግቦች፣ የቁስል ማሰርያዎች እና የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ቁሳቁሶች በግድግዳዎች ላይ ከፍ ብለው ተደርድረዋል።

ጥግ ላይ ተረኛ በጎ ፈቃደኞች የሚተኙባቸው ሁለት አልጋዎች አሉ።

እንቅልፍ ግን የሚታሰበው ስደተኞች የማይመጡ ከሆነ ብቻ ነው፤ አለበለዚያ የድረሱልን ጥሪው በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ ስለሚችል። ስደተኞች ባሉበት ሁሉ እርዳታ ለመስጠት መሯሯጥ የዕለት ተዕለት ተግባር ነው።

“በአብዛኛው በክረምት ወጣት ወንዶች በበጎ ፈቃደኝነት ይሳተፋሉ። ነገር ግን በመስከረም እና በጥቅምት በጎፈቃደኞቹ ግማሽ ያህሉ ወጣት ሴቶች ነበሩ፤ ብዙ ታዳጊዎችም አሉ።”

ከተቻለ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የመጀመሪያ እርዳታ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ የጥገኝነት ምክር ይሰጣል።

በበረዶ የተሸፈነ የጫካ ክፍል
የምስሉ መግለጫ,በጫካ ውስጥ የስደተኞች እንቅስቃሴ በጨመረ ቁጥር የብዝኀ ሕይወቱን እየቀየረው መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በተከለከለው የደን አካባቢ ውስጥ በሚያልፉ ሰዎች የሚቀጣጠለው እሳት እና የተጣሉት ቆሻሻዎች የቢያሎዊዛ እንስሳትን ባህሪ እየለወጠ ነው።

የአውሮፓ ጎሽ መንጋዎች የሰውን ጠረን ለመሸሽ በሚያደርጉት ጥረት ቀደም ሲል ወደ ማይሄዱባቸው የጫካው ክፍሎች እየገቡ ነው።

በጫካው ውስጥ የሰው እግር ዳና በጨመረ ቁጥር አብሮት የሚመጣውን ለአካባቢው ባዕድ የሆኑ ፍጥረታትን ለማስወገድ የደን ባለሙያዎችን ይሠራሉ።

ማቴዩስዝ ስዚሙራ በደን ጠባቂነት ከ20 ዓመታት በላይ ሠርቷል፤ ሕይወቱን በሙሉ በቢያሎዊዛ ኖሯል። ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ በበረዶ በተሸፈነ ድልድይ ላይ ሲጓዝ በሥራው ወቅት ብዙ ጊዜ ስደተኞችን እንደሚመለከት እና ከቤላሩስ በኩል የሚወሰደው እርምጃ አለመኖር እንደሚጨነቀው ይናገራል።

“የቢያሎዊዛ ጫካ ችግሮች የሚጨምረው፣ እነሱ [ቤላሩስ] ስደተኞች ጥበቃ በተደረገላቸው አካባቢዎች እንዲገኙ መፍቀዳቸውን ከቀጠሉ ብቻ ነው” ይላል።

ይኹን እንጂ ለብዙዎች ይህ ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚያደርጉት ጉዞ ጊዜያዊ መቆያ ብቻ ነው።

ሕገወጥ ስደት የቤላሩስ የፖለቲካ ጨዋታ ፈርጣማ ክንድ አካል እስከሆነ ድረስ ይህ ቀውስ በአውሮፓ ድንበሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይቀጥላል።

ዳዊት በጉዞው ላይ ያገኛቸው ብዙ ሰዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት የሚያስቡ መሆናቸውን አስተውሏል።

እሱ ግን በፖላንድ ጥገኝነት ጠይቆ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ነው።

“ደኅንነቴን ብቻ ነው የምፈልገው። ለዚህ ነው እዚህ ለመቅረት የወሰንኩት።”