በጦርነት የወደመችው ጋዛ

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል በመላው ጋዛ ሰርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጠች።

የአገሪቱ የኃይል ሚኒስትር ሐማስ ቀሪ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለመፍጠር በሚል ይህ እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ኤሊ ኮኸን ይህንን ያስተላለፉት እስራኤል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ጋዛ ማንኛውንም የእርዳታ አቅርቦት ካቋረጠች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

“ታጋቾቹን ለማስመለስ እንዲሁም በጦርነቱ ማግስት ሐማስ በጋዛ ውስጥ አለመኖሩን ለማረጋገጥ በእጃችን ያሉ ማንኛውንም መሳሪያዎች እንጠቀማለን” ሲሉ ኮኸን እሁድ ዕለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መግለጫ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በዋነኝነት ለግዛቲቷ ንጹህ መጠጥ አቅርቦት ወሳኝ በሆነው የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ስራ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የእስራኤል መንግሥት የውሃ አገልግሎት ሊያቋርጥ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው “ለጋዛ ሰርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በአስቸኳይ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ፈርሜያለሁ” ብለዋል።

እስራኤል በጦርነቱ ወቅት ጋዛን በሙሉ ከበባ አስገብታ ኤሌክትሪክን ጨምሮ መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ማቋረጧ ይታወሳል።

የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአስር ቀናት በፊት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህንን ያልጸና ስምምነት ለማራዘም የሚደረገው ውይይት በያዝነው ሰኞ በኳታር ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነትን መራዘምን ሐማስ እንዲቀበል ትፈልጋለች።

ሐማስ በበኩሉ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት ያለመው ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ ይሁን እያለ ነው።

የጋዛ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መቋረጥ በታጋቾቹ ላይም ተጽእኖ እንደሚያሳድር ያስጠነቀቀው ሐማስ በበኩሉ ከግብጽ አደራዳሪዎች ጋር የተደረገው የተኩስ አቁም ውይይት መጠናቀቁን ገልጿል።

በተጨማሪም የተኩስ አቁሙ ሁለተኛው ምዕራፍ በአስቸኳይ እንዲጀመር ጥሪውን አቅርቧል። የጋዛ የባህር ዳርቻ ግዛት እና የመሰረተ ልማት አውታሮች በእስራኤል የተቀናጀ እና የማያቋርጥ ጥቃት ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል።

የግዛቲቷ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ጄኔሬተሮችን እንዲሁም ሶላሮችን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። እስራኤል የጋዛን መሰረታዊ አገልግሎቶች በማቋረጧ ነቀፌታ እየተሰነዘረባት ይገኛል።

“የሰላማዊ ዜጎችን መሰረታዊ አገልግሎቶች መንፈግ የጅምላ ቅጣትን የሚያመለክት ነው” ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አርብ ዕለት አስታውቋል።

ፍልስጤማውያን ፕሬዚዳንታዊ እንዲሁም የፓርላማ ምርጫ እስኪያካሂዱ ድረስ ጋዛን የሚያስተዳድር ገለልተኛ ኮሚቴ ለመቋቋም ለቀረበው ሐሳብ ሐማስ ድጋፉን ገልጿል።

ኮሚቴው እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ) ጥላ ስር ተግባራቱን ያከናውናል። እስራኤል የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ) በጋዛ የትኛውንም ሚና አልቀበልም ያለች ሲሆን፤ ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ ሊኖር ስለሚችል አስተዳደር አማራጭ አላቀረበችም።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺህ189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።