የኮንጎ አማጽያን መሪ

ከ 3 ሰአት በፊት

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት በአብዛኛው የአገሪቱን ምስራቃዊ ክፍል የተቆጣጠሩት አማጽያን ሶስት አመራሮች በቁጥጥር ስር ለማዋል እገዛ ለሚያደርግ አካል የ5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቅርቤያለሁ አለ።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ የነበሩት ኮርኔይ ናንጋ የኤም23 አማጺ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ታጣቂዎችን አጣምሮ የያዘውን የኮንጎ ሪቨር አሊያንስ ይመራሉ።

መሪው በቁጥጥራቸው ስር ካሉ ከተሞች በአንዷ በነበረ ከፍተኛ የድጋፍ ስብሰባ ላይ ከሰሞኑ ንግግር አድርገዋል።

ከኮርኔይ በተጨማሪ ይህ ሽልማት የሚሰጠው የኤም23 መሪ የሆኑትን ሱልጣን ማኬንጋ እና በርትራንድ ቢስምዋን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው እገዛ ነው።

ባለፈው ዓመት ሶስቱ አመራሮች በሌሉበት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተከሰው የሞት ፍርድ ተበይኖባቸዋል።

በተጨማሪም በግዞት ላሉ ሁለት ጋዜጠኞች እና ሌሎች የአማጽያኑ ተባባሪ ተብለው የተፈረጁ ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግ ለሚያግዙ ተጨማሪ 4 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ቀርቧል።

ነገር ግን በዚህ መንገድ የትኛውም አመራር የመታሰር እድሉ ኢምንት ይመስላል።

ባለፉት ሳምንታት በሩዋንዳ የሚደገፉት አማጺያን በማዕድን የበለጸገችውን ምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊን ኮንጎ ግዛትን ጨምሮ የክልሉን ሁለት ታላላቅ ከተሞች፣ ጎማ እና ቡካቩን የአገሪቱን ጦር በማሸነፍ መቆጣጠር ችለዋል።

በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ሩዋንዳ ለአማጽያኑ በምትሰጠው ድጋፍ ምክንያት ማዕቀብ እንዲጣልባት ዓለም አቀፍ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ባወጣው ሪፖርት እስከ 4 ሺህ የሚደርሱ የሩዋንዳ ወታደሮች ከኤም23 ጋር ተሰልፈው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ተሰማርተው እንደሚገኙ ነው።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቀያቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

የኮንጎ መንግሥት ከአሜሪካ ድጋፍ የሚሻ ሲሆን በምላሹም የአገሪቱን ብርቅዬ ማዕድናትን እሰጣለሁ ብሏል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሞባይል ስልኮች እና ኮምፒውተሮች እንደ ግብዓቶች የሚጠቀሙባቸውን ወርቅ እና ኮልታን ጨምሮ የአገሪቱን ማዕድናት ለመቆጣጠር ሩዋንዳ እየሞከረች ነው ስትል ትከሳለች።

ኮንጎ አማጽያኑን ለመዋጋት ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ስትል በምላሹ ማዕድኗን ለመስጠት ማቅረቧን አስመልክቶ የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ቲና ሳልማ ምላሽ ሰጥተዋል።

“የአሜሪካ ኩባንያዎች መሰረታዊ የሚባሉ ጥሬ ማዕድናትን ከሩዋንዳ ይገዛሉ። እነዚህ ማዕድናት ከኮንጎ ተዘርፈው ወደ ሩዋንዳ በህገወጥ መንገድ የተዘዋወሩ ናቸው። እናም ፕሬዚዳንቱ ከዋናው ምንጩ (ባለቤቱ) ኮንጎ እንዲገዙ ነው ሃሳብ ያቀረቡት” ብለዋል።

ሩዋንዳ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ማዕድናትን እየዘረፈች ነው መባሏን አስተባብላለች። ሩዋንዳ አማጽያኑን ኤም23 መደገፏን የማትክድ ሲሆን ነገር ግን ግጭቱ ወደ አገሬ እንዳይዛመት ለማድረግ እየተከላከልኩ ነው የሚል ምክንያትን ትሰጣለች።

በተጨማሪም ሩዋንዳ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መቀመጫቸውን ያደረጉ በአውሮፓውያኑ 1994 በተፈጸመባት የዘር ጭፍጨፋ ግንኙነት ያላቸው ቡድኖችን መንግሥቱ ይደግፋል ሲል ይተቻል።