Jemal Abdulaziz

“‘ቁርጭምጭሚት’ የሚለው ቃል ያስቀኛል” ለ23 ዓመታት ለፈረንጆች አማርኛን ያስተማረችው ፖላንዳዊት፣ ዶ/ር ኤቫ ቮልክ-ሶሬ

ክፍል ፩

ፓላንዳዊት ናት። አማርኛን ከ40 ዓመት በፊት ነው የተማረችው።

ያኔ አማርኛን በዲግሪ ተመርቃ እስከዛሬ ታስተምራለች።

ላለፉት 23 ዓመታት በርካታ ፈረንጅ በአማርኛ ቋንቋ ዲግሪ አስይዛለች።

ዶ/ር ኤቫን ‘አንቺ’ እንበላት እንጂ በሥራዋ አንቱታን የተጎናጸፈች ሴት ናት። የአማርኛ የቁልምጫ ስሟ ሔዋን ይባላል።

ብታምኑም ባታምኑም፣እሷ የምታስተምርበት ዋርሶ ዩኒቨርስቲ አማርኛን ማስተማር ከጀመረ 75 ዓመት አልፎታል።

ለነገሩ ይሄ ምኑ ይደንቃል?

በምኒልክ ጊዜ አማርኛ በአውሮፓ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ይሰጥ ነበር።

ኔፕልስ፣ ፓሪስ እና ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲዎች አማርኛ ማስተማር ከጀመሩ 100 ዓመት አልፏቸዋል።

ይህ ለብዙ ሰው ዜና ነው።

በኔፕልስ አማርኛን ማስተማር የጀመሩት አፈወርቅ ገብረየሱስ ናቸው። ይህ ማለት በ1890ዎቹ መሆኑ ነው። ጥንት በዓድዋ ዘመን።

አማርኛ በጀርመን፣ ሐምቡርግም ዩኒቨርስቲም ይሰጣል። እዚያም ድሮ ነው የተጀመረው። ዛሬም ድረስ አለ፤ ለዚያውም ሳይቋረጥ።

ይቆጠር ከተባለ 105 ዓመት ሆኖታል፣ ዘንድሮ።

የመጀመሪያው መምህር ወልደማሪያም ደስታ የሚባሉ ሰው ናቸው። በ1909 ከአንኮበር-ሐምቡርግ ሄደው አምስት ዓመት አስተምረዋል።

በዶክተር ኤቫ አገር፣ ፖላንድ አማርኛን ማስተማር የጀመሩት ፕሮፌሰር ስቴፋን ስትሬልሲን ናቸው።የዛሬ 75 ዓመት ገደማ።

እሳቸው አማርኛን ያጠኑት በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ነው። ቋንቋውን የተማሩት ደግሞ በፈረንሳይ ነው። እኚህ ሰው ከባድ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነበሩ ይባላል።

በዚህም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወርቅ ኒሻን ተበርክቶላቸዋል።

1950ዎቹ የአፍሪካ ጥናትን ከመሠረቱ ወዲህ ብዙ ለፉ። አማርኛን በአውሮፓ አስፋፉ።

እንደ አውሮፓዊያኑ በ1981 ሕይወታቸው አለፈ።

እርሳቸው የመሠረቱት ተቋም ሰፍቶ፣ አድጎ እና ተመንድጎ በ1977 የአፍሪካ ቋንቋዎች እና ባሕል ትምህርት ክፍል ተባለ።

ከአማርኛ እና ከግዕዝ ሌላ ሐውሳ እና ስዋሂሊ ቋንቋዎችን ማስተማር ጀመረ።

ዶ/ር ኤቫ በዚህ ዘመን ባስቆጠረ ተቋም ነው አማርኛን የምታስተምረው።

እሷ ፕሮፌሰር ስቴፈንን አልደረሰችባቸውም። በዝና ነው የምታውቃቸው።

ዘገባው የቢቢሲ ነው።