ተላላኪነት፣ እንጦርጦስ ካፒታሊዝም… እና የአሰብ ወደብ!

ኢሣያስ አፈወርቂ ብዙ ነገር ሊሆን ይችላል፣ ተላላኪ ግን አይደለም! ሂድና የመንን ውጋልን!፣ ተነስና እንዲህ አድርግ ቢባል – ማንንም – አፍንጫችሁን ላሱ! የማለት ቆፍጣናነቱ አለው።

ስለዚህ በቀይባህር ዙሪያ ሌላ ታዛዥ፣ አድርባይና ተላላኪ ኃይል እንዲኖር ተፈልጓል በአያ እንቶኔዎቹ! ለዚህ የታጨችው ደሞ ላለፉት ሠላሳ ምናምን ዓመታት አንጋፋ የተላላኪነት ልምድ ያካበተችው የኢህአዴግ-ብልፅግናዋ ጉደኚት ሀገራችን ሆና የተገኘች ይመስላል! እና 7ኛው ንጉሥ የአሰብን ጥያቄ እንዲገፋበት green light ሳይሰጡት አይቀሩም! (የቀበሩትን ፈንጂ የመምዘዣ ትክክለኛ ጊዜ እንደመጣላቸው ሳያምኑ አይቀሩም!)

ሳዳምን የተጫወቱበት እንደዚያ ነበር፣ ኩዌትኮ ያንተ ናት ትገባሃለች ብለው አይዞህ ብለው አነሳሱት! ዓይናቸው እያየ ራሱን አደራጅቶ ኩዌትን ሲይዝ ሉዓላዊ ሀገር በጉልበት ወረረ ብለው ዘመቱበት! The Bush plot ይባላል ይሄ ሤራ!

አሁን አጅሬውም ባህር በሌለበት የባህርኃይል ሲያደራጅ ቆይቷል፣ አሁን ደሞ አሰብን እያለ ነው! (ሌላ ሰው ቢለው ምን ነበረበት? ባህር ተሻግሮ ደቡብ አረቢያ እንደዘመተው እንደ ንጉሥ ካሌብ፣ እሱም የተላላኪነት ማዕረጉን ተቀብሎ ሶማሊያ እንደዘመተው፣ የመንም ላይ ለመዝመት ቋምጧል! ከዚያ የsecurity partnerራችን ነው ተብሎ (ቢያንስ የወያኔን ያክል ዕድሜ) በሥልጣን ላይ ይቆያል!

Politics is dirty. Political prostitution ከዚህም ይከፋል! ትናንት ከእገሌ ጋር፣ ዛሬ ከእገሌ፣ ነገ ደግሞ ከእነ እገሌ! የፖለቲካ ዝሙት የሚቀፍ ነገር አለው! ሀገር Integrity ባላቸው ሰዎች እጅ ስትገባ ብቻ ነው ቋሚ ነገር የሚኖራት። አለዚያ ሥራችን ሁሉ መትከልና መንቀል ሆኖ ይቀራል! የማያድግ ችግኝ፣ ይተከላል፣ ይነቀላል! በመትከል በመንቀል ተጠምደን፣ ዛፍ የሚሆን አንድም ችግኝ ሳናፈራ ጊዜው አልፎብን እንነቀላለን!

ዲዛስተር ካፒታሊዝም የሚያብበው በChaos ውስጥ ነው ትላለች ናዖሚ ክሌን The Shock Doctrine በሚል መፅሐፏ! የእንጦረጦስ ካፒታሊዝም አመሉ ብጥብጥን፣ ጦርነትን፣ ግጭትን፣ ትርምስን እንደ ህይወት ማስቀጠያ የደም ሥሩ አድርጎ መቁጠሩ ነው!

እንጦረጦስ ካፒታሊዝም እንደ ኦፖርቹኒስቲክ ዲዚዝ ነው! በየቦታው ከግራና ከቀኝ ሳይድ እየያዘ ጦርነትን ይቆሰቁሳል፣ የሀገሮችን ራሳቸውን የመከላከል አቅም፣ ተላላኪነትን የመቋቋም ብቃት ብርቅስቅሱን የሚያወጣለት አንዳች መቅሰፍት ውስጥ እንዲነከሩለት ተግቶ ይሠራል! ገደል እንዲገቡ ይገፋቸዋል፣ ገደል ከገቡ በኋላ ነፍስአድን ሆኖ ኮተቱን ጭኖ ይመጣል! ዲዛስተር ካፒታሊዝም አውሬያዊ፣ ይሉኝታቢስ አመሉ ይሄ ነው!

አሁን ዩክሬይንን እያት፣ አይዞሽ አይዞሽ ብለው ገፋፍተው ጦርነት ውስጥ ከተቷት። ሁሉነገሯን ቅርጥፍ አድርጋ ከበላችና ሙሉበሙሉ በእነሱ ይሁንታና ቸርነት ላይ ህልውናዋ እንደተንጠለጠለ ሲያውቁ፣ ማዕድኖችሽን ጠቅልለሽ አምጪ አለዚያ ራስሽ ተወጪው አሉ።

ሊንድሴይ ግራሃም የሚባለው ሴናተር ሰሞኑን የዜለንስኪን ትከሻ መታ መታ እያደረገ፣ እስካሁን የኛ መንግሥት ዩክሬን ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ምንም አሳማኝ ምክንያት አልነበረውም፣ አሁን ግን ሚነራሎቻችሁ ላይ ኢንቬስት እናደርጋለን፣ ከዚያ ምክንያት አገኘን ማለት ነው፣ protect የምናደርገው interest ይኖረናል ማለት ነው! የምንቆምለት የራሳችን ጥቅም ካለ፣ መንግሥታችን ያን ጥቅሙን ለመጠበቅ ከጎናችሁ ይቆማል! ይለዋል በሚዲያ ፓነል ፊት!

ይህን ሲሰማ የዩክሬኑ ተላላኪ ምን እንደሚሰማው አላውቅም! በመጨረሻ ሁሉም ነገር ስለምን እንደነበር ይገለጥለት ይሆናል፣ የእንጦረጦስ ካፒታሊዝም ሁለለመና ወለል ብሎ ይታየው ይሆናል! But it’s too late for anything! እና ወይ የሀገሩን ሚነራል ገልቦ ለእንቶኔዎች ማስደፈር፣ ወይ ሀገሩን ማጣት ነው አማራጩ! በመሐሉ ከሥልጣኑ የሚመነግሉት ደሞ ይነሱበታል! ለማንም ሳይበጅ ሀገሩንና ሕዝቡን አስበልቶ ቀኑ የከፋ ዕለት ቤተሰቡን ይዞ ያመልጣል ወዳንዱ ሀገር!

ሶሪያን ተመልከታት። እንጦርጦስ ካፒታሊዝም በነፃነት፣ ሽብርን በመፋለም፣ አምባገነንን በማስወገድ፣ የሆነ ዘርን ከሆነ ዘር ጥቃት ለመከላከል፣ በምናምን ሰበብ በሶርያ ጦርነት፣ አመፅ፣ ብጥብጥ ቀሰቀሰ። አንዴ ያኛውን አንጃ፣ አንዴ ይሄኛውን ከመርዳት አልፈው ራሳቸው ጦራቸውን አሠማርተው፣ ጄቶቻቸውን ጭነው የሚፈልጉትን ሲያነሱና ሲያወድሙ ቆዩ።

አሁን አለ የሚባለውን የሶርያን በነዳጅ ሀብት የበለፀገ ክፍል በአሜሪካኖቹ ቁጥጥር ሥር ነው! ግርግር የተፈጠረላቸውና ያመቻቸው እስራኤሎች የሶርያን ወታደራዊ ተቋማትና አቅሞች እንደ ጦር መለማመጃ ቆጥረውት በሠማይ ቦምብና በሚሣኤል ያርሱታል!

ሊቢያን እንይ፣ ስክሪፕቱ ይለያል እንጂ ታሪኩም ሆነ ፍፃሜው ያው ነው! ዛሬ ላይ የሊቢያን በየትኛውም ዓለም የማይገኝ ንፁህ ክሩድ ኦይል ጦራቸውን አስፍረው የተቆጣጠሩት ኦነ አያ እንቶኔ ናቸው! ሀገሪቱ ባዶ እጇን አጨብጭባ እየተተራመሰች ነው!

ዛሬ የኢራቅ የነዳጅ ጉድጓዶች በእነ እንቶኔ የእንጦረጦስ ካፒታሊስቶች ዕዳ የተያዙ ናቸው! ዕዳው ደሞ ሳዳምን ልናስወግድላችሁ ያወጣነው ወጪ ተብሎ የተቆለለ ነው። ዲዛስተር ካፒታሊዝሙ የትም የትርምስ ጭስ በሸተተው ቦታ ከማንም ቀድሞ ከተፍ ይላል፣ ከተብረከረኩ መንግሥቶችና የሀገራቸውን የመከላከል አቅም ቅርጥፍ አድሮገው ከበሉና ካስበሉ የሥልጣን አሞሮች እጅ፣ የሚፈልገውን የየሃገሩን አንጡረ ሀብት ይቆጣጠራል! ያሻውን ማዕድን ያወጣል፣ ያሻውን ንግድ ይሸቅላል!

ዲዛስተር ካፒታሊዝም እኛ ሀገር ገና አሞራ በሠማይ ሲያይሽ ዋለ ሲል ደጋግሜ የናዖሚ ክሌይንን ትንቢተኛ ሃሳቦች ስፅፍ ነበር።

ይኸው ዕድሜ ለሥልጣን አልቅቶቻችን፣ በአውዳሚ ጦርነት ሀገራችንን አዳክመው፣ ኢኮኖሚውን ገድለው፣ በያቅጣጫው ገና እያገረሸ የሚቀጥል ትርምስና ግጭት ፈጥረው፣ የሀገሪቱን የመቋቋም አቅም ሁሉ ካነከቱት በኋላ አሁን ቀሚሷን ገልበው በእንጦረጦስ ካፒታሊዝሙ የገንዘብ ኮርማዎች (በእነ አይኤምኤፍና ወርልድባንክ) እያስጠቋት ነው!

ይህም አልበቃም! እንጦረጦስ ካፒታሊዝሙ እንደ ልቡ ለመሆን የሚያስችለው ምሱ፣ ቅልጥ ያለ ትርምስ ነው። አሁን ትርምሱ በረድ ያለ እየመሰለ ነው! ስለዚህ ትልቅ ትርምስ ያስፈልጋል! ኢትዮጵያ ለምን የሚገባትን ወደብ አትጠይቅም? እንደግፋለን! ሳዳምን፣ አሳድን፣ ጋዳፊን፣ መለስን፣ ሁሉን በየተራ ፈንግለን የቀሩን ሁለት አምባገነኖች ኪም ጆንግ ኡንና ኢሣያስ ናቸው! የሚሉ ይመስለኛል ዲዛስተር ካፒታሊስቶቹ እርስበርሳቸው!

እና በኤርትራው አምባገነን ላይ (ታዛዥ አልሆንም ያለ ሁሉ አምባገነን ነው!) ለምን 7ኛውን ንጉሥ አናስነሳበትም? ልክ እግዜሩ መልካምን ነገር ሁሉ እንፍጠር ብሎ አነደፈጠረው፣ ከእንጦረጦስ የሚያተርፉና ሥልጣናቸውን የሚያስቀጥሉ ሁሉ፣ እስቲ እንጦርጦስን እንፍጠር… ብለው በተደሰተ ልብ ቀናቸውን የሚጀምሩ ይመስለኛል! ዲዛስተር – ለጥቂቶች ሥልጣን ማስቀጠያ ነው፣ ለጥቂቶች ደሞ ሥልጣንን መቆናጠጫ፣ ለእንጦርጦስ ካፒታሊስቶች ደሞ የሚታለቡ ላሞችን የመረከቢያ፣ አልደፈር ያሉ ሀገሮችን የመሠረሪያ ምቹ አጋጣሚ ነው!

የአሰብ ወደብ ለእኛ ፊጋ በሬ የእንጦርጦስ ካፒታሊዝም ያቀረበለት አዲስ ጨሌ (ለምለም ሣር) ነው! በሬ ሆይ በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ… ብሎ መተረቻ ጊዜው አሁን ነው! ትርምስ የደም ሥር ሆኗል!