
ከ 8 ሰአት በፊት
ለሰሜን ኮሪያ መንግሥት እንደሚሠሩ የሚታመኑ ክሪፕቶ መንታፊዎች ከዘረፉት 1.5 ቢሊዮን ዶላር የበይነ መረብ ገንዘብ (ክሪፕቶ ከረንሲ) 300 ሚሊዮን ዶላሩን በጥሬው ማውጣታቸው ተነግሯል።
ላዛረስ (አልዓዛር) በመባል የሚታወቀው የመንታፊዎች ቡድን ከሁለት ሳምንት በፊት ባይባይት ከተባለ የበይነ መረብ የገንዘብ ኩባንያ ትልቅ የዲጂታል ገንዘብ ዘርፏል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንታፊዎቹን እና የዘረፉትን ክሪፕቶ ወደ ገንዘብ ከመቀየራቸው በፊት እግር በእግር ተከታትሎ ማስቆም የአይጥ እና ድመት ጨዋታ ሆኖ ሰንብቷል።
ባለሙያዎች የመንታፊዎቹ ቡድን የዘረፈውን ገንዘብ ወደ ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ መሳርያ ማምረቻ ተቋም ለማስተላለፍ ቀን ተሌት ሲሠሩ ቆይተዋል ይላሉ።
የክሪፕቶ መርማሪ የሆኑት እና ኢሊፕቲክ የተባለው ድርጅት መሥራቹ ዶክተር ቶም ሮቢንሰን “መንታፊዎቹ የገንዘቡን ዳና ለማጥፋት በሚያደርጉት ሥራ ውስጥ እያንዳንዷ ደቂቃ ወሳኝ ነበረች፤ እንዲሁም በዚህ ረገድ እጅግ በጣም የተራቀቁ ናቸው” ይላሉ።
ዶ/ር ሮቢንሰን በክሪፕቶ ዘረፋ ውስጥ ከተሳተፉት ወንጀኞች መካከል እንደ ሰሜን ኮሪያ ክሪፕቶን ምርጥ አድርጎ የሚያጥብ [በወንጀል የተገኘን የበይነ መረብ ገንዘብ ወደ ጥሬ ገንዘብ የሚቀይር] የለም ብለዋል።
“እኔ እንደማስበው ይህንን የሚሠራ ዘመን አፈራሽ መሳሪያ እና ለዓመታት ልምድ ያካበቱ በርካታ ባለሙያዎች ሳይኖራቸው አይቀርም። በተጨማሪም በየቀኑ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ እረፍት እንደሚወስዱ ከተግባራቸው እንረዳለን። ምናልባትም ክሪፕቶው ወደ ጥሬ ገንዘብ እንዲለወጥ በፈረቃ ይሆናል የሚሠሩት።”
ኤሊፕቲክ ከባይቢት ጋር በተያያዘ በሠራው ትንታኔ፣ 20 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ “የገባበት አይታወቅም”፤ ይህም ማለት ገንዘቡ የውሃ ሽታ ሆኗል ማለት ነው።
አሜሪካ እና አጋሮቹ ሰሜን ኮሪያውያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገዛዙ ወታደራዊ እና የኒውክሌር ማበልጸግ በገንዘብ ለመደገፍ በደርዘን የሚቆጠሩ የመረጃ ጠለፋዎችን ፈጽመዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።
ባለፈው የካቲት 14 ወንጀለኞች ከባይባይትን አቅራቢ በምሥጢር የገንዘብ ዝውውሩን በመመንተፍ ድርጅቱ ወደራሱ አካውንት የላከ መስሎት ወደ መንታፊዎቹ ልኳል።
የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ቤን ዙ ገንዘቡ እንዳልተወሰደ ለደንበኞቻቸው ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር።
ዘረፋው ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ መረጃ መንታፊዎቹ ጥሬ ገንዘቡን አውጥተው መጠቀም እንዳይችሉ ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቷል።
ድርጅቱ ከዝርፊያው በኋላ የተዘረፈውን ገንዘብ ብድር ወስዶ መተካቱን የገለፀ ሲሆን፤ በላዛረስ ቡድን ላይም ዘመቻ መክፈቱን አስታውቋል።
- የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች ከዘረፉት 1.5 ቢሊዮን የክሪፕቶ ገንዘብ 300 ሚሊዮን ዶላር በጥሬ ማውጣታቸው ተነገረ10 መጋቢት 2025
- ዓለም ሁሉ የሚያወራለት ክሪይፕቶከረንሲ ምንድነው?20 የካቲት 2019
- የቢትኮይን ዋጋ 100 ሺህ ዶላርን ተሻግሯል – ለመሆኑ ታሪካዊ የሚባሉት 7 አጋጣሚዎቹ የትኞቹ ናቸው?5 ታህሳስ 2024

መንታፊዎቹ የዘረፉትን በይነ ገንዘብ በሚታወቁ ማስተላለፊያ አገልግሎቶች እንደ ዶላር ባሉ መደበኛ ገንዘቦች ለመቀየር ከሞከሩ ገንዘቡን መያዝ ይቻላል።
ባይቢት ላዛረስን (አልዓዛር) የተባለውን የሰሜን ኮሪያ የክሪፕቶ መንታፊ ቡድንን ላጋለየ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እሸልማለሁ በሚል ባወጣው ማስታወቂያ ላይ፣ የሕብረተሰቡ አባላት የተዘረፉትን ገንዘቦች እንዲፈልጉ እና በተቻለ አቅም እንዲታገዱ እንዲያርጉ ጠይቋል።
ሁሉም የክሪፕቶ ግብይቶች በሕዝብ ብሎክቼይን ላይ ስለሚታዩ ገንዘቡ በላዛረስ (አልዓዛር) ቡድን ሲዘዋወር መከታተል ይቻላል።
ጠላፊዎቹ ኮይኖቹን ወደ መደበኛ ገንዘብ ለመቀየር የዋናውን ክሪፕቶ አገልግሎት ለመጠቀም ከሞከሩ እና የክሪፕቶ ሳንቲሞቹ ከወንጀል ጋር የተገናኙ ናቸው ተብሎ ከታሰበ ሊታገዱ ይችላሉ።
እስካሁን በዚህ መንገድ 20 የሚሆኑ ሰዎች 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የበይነ መረብ ገንዘብ እንዳይተላለፍ በማሳገድ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሽልማት ገንዘብ ተቀብለዋል።
ባለሙያዎች ግን ሰሜን ኮሪያ የክሪፕቶ ከረንሲ ገንዘብ በመመንተፍ እና ደብዛውን በማጥፋት ረገድ ያላትን ልምድ ከግምት በማስገባት የቀረውን ገዘንዘብ ለማስመለስ እምብዛም ተስፋ አይታያቸውም።
በበይነ መረብ (ሳይበር) ደኅንነት ላይ የሚሠሩት ዶ/ር ዶሪት ዶር “ሰሜን ኮሪያ በጣም ዝግ የሆነ ሥርዓት እና የተዘጋ ኢኮኖሚ ያላት በመሆኗ ለጠለፋ እና ለገንዘብ አጠባ ምቹ የሆነ ኢንዱስትሪ ፈጥራለች፤ ነገር ግን የሳይበር ወንጀል የሚያስከትለው አሉታዊ ስም ግድ አይሰጣትም” ብለዋል።
ሌላው ችግር ሁሉም የክሪፕቶ ኩባንያዎች ለመረዳዳት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው።
ባይቢት ክሪፕቶን ወደ ገንዘብ የሚቀይረው ኢኤክስኤ (eXch) ወንጀለኞቹ ገንዘብ እንዳያወጡ አላደረገም በሚል ተከስሷል።
በዚህ ልውውጥ ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ በተሳካ ሁኔታ መቀየር ተችሏል።
በኢሜይል ማንነቱ በይፋ የማይታወቀው የeXch ባለቤት፣ ጆሃና ሮበርትስ፣ ውንጀላውን አስተባብሏል።
ድርጅታቸው ከባይቢት ጋር ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ውዝግብ ውስጥ በመሆኑ መጀመሪያ ላይ ገንዘቡን ማስቆም አለመቻላቸውን አምኗል።
አክሎም ቡድኑ በእርግጠኛነት ኮይኖቹ ከጠለፋው የተገኙ መሆናቸውን እርግጠኛ እንዳልነበር ተናግሯል።
አሁን በትብብር እየሠራ መሆኑን ከገለጸ በኋላ፣ ነገር ግን የክሪፕቶ ደንበኞችን የሚለዩ መደበኛ ኩባንያዎች ግለሰቦችን እና ማንነታቸውን ይፋ የማያደርጉ ተጠቃሚዎችን እያጭበረበሩ ነው ሲል ተከራክሯል።

ሰሜን ኮሪያ ከላዛረስ ቡድን ጀርባ መኖሯን አምና አታውቅም፤ ነገር ግን በዓለም ላይ ያላትን የመመንተፍ ብቃት ለገንዘብ ጥቅም የምትጠቀም ብቸኛ አገር መሆኗ ይገመታል።
ከዚህ ቀደም የላዛረስ ቡድን መንታፊዎች ባንኮችን ዒላማ ያደረጉ ቢሆንም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ግን የክሪፕቶ ኩባንያዎችን በማጥቃት ረገድ ልዩ ክኅሎትን አዳብረዋል።
እንዲህ ዓይነት ማጭበርበርን ለማስቆም ጥቂት መንገዶች ብቻ ያሉ በመሆኑ ኢንዱስትሪው በጥሩ ሁኔታ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም።
ከሰሜን ኮሪያ ጋር የተገናኙ የቅርብ ጊዜ የበይነ መረብ ምንተፋዎች፡-
- በ2019 በአፕቢት (UpBit) ላይ የተወሰደ 41ሚሊዮን ዶላር
- ከኩኮይን (KuCoin) 275 ሚሊዮን የሚያወጣ ክሪፕቶ ተዘርፎ ኋላ ላይ አብዛኛው ገንዘብ የተመለሰ
- በ2022 መንታፊዎች 600 ሚሊዮን ዶላር ክሪፕቶ የዘረፉበት የሮኒን ብሪጅ ጥቃት
- በ2023 በአቶሚክ ዋሌት ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ክሪፕቶ ተሰርቋል።
በአውሮፓውያኑ 2020 አሜሪካ ሰሜን ኮሪያውያንን የላዛረስ ቡድን አባላት ናቸው በሚል ወንጅላ በሳይበር ወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ አካታቸዋለች።
ነገር ግን ግለሰቦቹ አገራቸውን ለቅቀው ካልወጡ በስተቀር ሊያዙ እና ሊጠየቁ የሚችሉበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው።
ይህ ሁሉ ሲሆን እና ስሙ በከባድ የወንጀል ድርጊት እየተብጠለጠለ የሚገኘው ከአብዛኛው ዓለም ተነጥላ የምትገኘው የሰሜን ኮሪያ መንግሥት በማስተባበል እራሱን ለመከላከል ያለው ነገር የለም።