
ከ 8 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ከፊል የተኩስ አቁም ለማድረግ ያቀረበችው ምክረ ሀሳብ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናገሩ።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እህንን ያሉት የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት በሳዑዲ አረቢያ ተገናኝተው ከመወያየታች አስቀድሞ ነው።
ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ማርኮ ሩቢዮ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት “ይህ ብቻውን በቂ ነው እያልኩ አይደለም ነገር ግን ግጭቱን ለማስቆም ማየት ያለብን ዓይነት ስምምነት ነው” ብለዋል።
ኪየቭ ማክሰኞ በሚደረገው ድርድር ከሩሲያ ጋር በአየር እና በባህር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሀሳብ እንደምታቀርብ ይጠበቃል ሲሉ አንድ የዩክሬን ባለስልጣን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ሩሲያ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሀሳብን ጊዜ ለመግዛት እና የዩክሬን ወታደራዊ ውድቀትን ለመከላከል የሚደረግ ሙከራ ነው በሚል ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በአገራቸው እና በአሜሪካ መካከል በሚደረገው ውይይት ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም፣ ከልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር ለመገናኘት ሰኞ ዕለት ሳውዲ አረቢያ ገብተዋል።
ዜሌንስኪ ሰኞ ከሰዓት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ከውይይቱ “ተግባራዊ ውጤት” እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፣ የዩክሬን አቋም “ፍፁም ገንቢ” እንደሚሆን ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ቡድን በዜለንስኪ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አንድሪይ ያርማክ፣ በአገሪቱ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ እና በርካታ የውጭ እና የመከላከያ ሚኒስትሮች ይወከላል።
በሩቢዮ የሚመራው የአሜሪካ ልዑካን ቡድን እንዲሁ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪውን ማይክ ዋልትዝ እና የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍን አካትቷል።
ሩቢዮ ሰኞ ዕለት ጅዳ ከመድረሳቸው በፊት ለሰላም ስምምነቱ “የዩክሬን ዓላማ በግልፅ ማስቀመጥ” አስፈላጊ እንደሆነ እና አገሪቱ “ይህን ለማስቆም ሩሲያውያን እንደሚወስኗቸው ከባድ ውሳኔዎችን ለመወሰን ዝግጁ መሆን አለባት” ብለዋል ።
አክለውም “ማድረግ የሚገባቸውን ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አላስቀምጥም” ብለዋል።
“እኛ ምን ያህል ለመሄድ ፈቃደኞች እንደሆኑ ለማየት፣ለማዳመጥ ዝግጁ ነን። እና ያንን ሩሲያውያን ከሚፈልጉት ነገር ጋር በማነፃፀር ምን ያህል ልዩነት እንዳለን ለማየት እንፈልጋለን።”
ሁለቱም ተፈላሚ ወገኖች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ለግጭቱ “ወታደራዊ መፍትሄ የለም” ያሉት ሩቢዮ፣ ሊፈታ የሚችለው በ “ዲፕሎማሲያዊ መንገድ” መሆኑን ሁለቱም ወገኖች ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።
- ከዩክሬን ጋር በተያያዘ ከሚካሄደው አዲስ ንግግር በፊት አሜሪካ፣ ሩሲያ እና አውሮፓ ምን እያሰቡ ይሆን?9 መጋቢት 2025
- ከስምምነት ለመድረስ ከሩሲያ ይልቅ ዩክሬን ‘አስቸጋሪ’ ናት ሲሉ ትራምፕ ወቀሱ8 መጋቢት 2025
- ዜሌንስኪ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ልታደርገው ያቀደችው ውይይት “ፍሬያማ” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገለጹ7 መጋቢት 2025

በሳዑዲ የሚደረው ይህ ውይይት የመጣው ዜሌንስኪ ከሞስኮ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጫና እያደረጉ ባለበት እና ምንም ዓይነት የደህንንት ዋስትና ባልሰጡበት ወቅት ነው።
ይህ ንግግር ዜሌንስኪ በዋይት ሐውስ ያደረጉት ጉብኝት በአለመግባባት ከተጠናቀቀ በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው ይፋዊ ስብሰባ ነው።
ከዜሌንስኪ ጉብኝት በኋላ አሜሪካ ዜሌንስኪን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት በሚል ለኪዬቭ የምታደርገውን ወታደራዊ ዕርዳታን እንዲሁም የደህንንት መረጃ ልውውጥ ለጊዜው አቁማለች።
ሩቢዮ የዕርዳታ መቋረጡ ጉዳይ ከውይይቱ በኋላ “ሊፈታ ይችላል” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ ማክሰኞ የሚደረገው ድርድር ግን “ለዚያ ቁልፍ ይሆናል” ብለዋል።
እገዳው የተደረገው “እነሱ [ዩክሬን] ለማንኛውም ዓይነት የሰላም ሂደት ቁርጠኛ እንዳልሆኑ ስለተሰማን ነው” ያሉት ሩቢዮ “ይህ ከተለወጠ፣ የእኛ አቋምም ሊለወጥ ይችላል” ብለዋል።
“ፕሬዚዳንቱ በእጃቸው ያሉትን አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ሁለቱንም ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት ይሞክራሉ፤ ያኔም ይህ ጦርነት ያበቃል” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በድርድሩ “ትልቅ መሻሻል” እንደሚጠብቁ ተናግረው ነበር።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዜሌንስኪ የማዕድን ስምምነቱን ለመፈረም ወደ አሜሪካ ይመጡ ይሆን ተብለው በፎክስ ኒውስ ለቀረበላቸው ጥያቄም “በእርግጥ ተስፋ አለኝ። እስካሁን የሚታየው ነገር በጣም እና በጣም አዎንታዊ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም ዜሌንስኪ ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ዊትኮፍ በሳዑዲ አረቢያ በሚኖረው ውይይት ላይ ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል የዩክሬናውያን የደህንነት እና የግዛት ጉዳዮች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
አሜሪካ ዩክሬን የሚያስፈልጋትን ማንኛውም የመከላከያ የስለላ መረጃን ለማጋራት መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ዝግ አድርጋ አታውቅም ያሉ ሲሆን፣ ትራምፕ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ለዩክሬን የተቋረጠው የስለላ መረጃዎችን ማጋራትን “ሊነሳ” እንደሆነ ተናግረው ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመርም ከውይይቱ በፊት ትራምፕን ማነጋገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩናይትድ ስቴትስ ዕርዳታ እና የመረጃ ልውውጥ እንደገና እንዲጀመር የሚያስችል አወንታዊ ውጤት እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል” ብለዋል ቃል አቀባዩ ።
እኤአ በ2022 የካቲት ወር ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን የወረረች ሲሆን በአሁኑ ወቅትም አምስት ግዛቶች፣ ክሬሚያን ጨምሮ፣ በእጇ ይገኛሉ።