ኤክስ

ከ 6 ሰአት በፊት

ኤክስ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ሥራ አቋርጦ እንደነበር ተገለጸ።

ትናንት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ መሥራት አቁሞ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ኤክስን መክፈት አልቻሉም ነበር።

ኢሎን መስክ የሚያስተዳድረው ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) መቋረጡን በአሥር ሺዎች ከሚቆጠሩ የአሜሪካ ተጠቃሚዎች ሪፖርት ማድረጋቸውን ዳውንዲቴክተር የተባለው ድረ ገጽ አስታውቋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ከ8,000 በላይ ሪፖርቶች ተደርገዋል።

ትናንት ከሰዓት አካባቢ የኤክስ ገጽ መቆራረጥ መስተዋሉም ተገልጿል።

ማኅበራዊ ሚዲያውን ለመጠቀም የሞከሩ ሰዎች ገጹ ላይ አዳዲስ መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

ኢሎን መስክ የአገልግሎት መቋረጥ የተከሰተው “ከዩክሬን አካባቢ በተቃጣ ከፍተኛ የበይነ መረብ ጥቃት ምክንያት ነው” ብሏል።

ዩክሬንን እና ፕሬዝዳንቷ ቮሎድሚር ዜሌንስኪን በመተቸት የሚታወቀው መስክ ለክሱ ማስረጃ አላቀረበም።

የውጭ ኃይሎች ስለመሳተፋቸውም ያለው ነገር የለም።

“የተደራጀና ትልቅ ቡድን ወይም አገር እጁ አለበት” ሲል በኤክስ ገጹ ጽፏል።

“ከዩክሬን አካባቢ የተቃጣ ኤክስን ለማስቆም ያለመ ትልቅ የበይነ መረብ ጥቃት ነው” ሲልም አክሏል።

የድረ ገጾችን ትስስር የሚቆጣጠረው ኔትብሎክስ ዳይሬክተር አልፕ ቶከር እንዳለው ኤክስ የተቋረጠው በበይነ መረብ ጥቃት ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ስድስት ሰዓት ገደማ የቆየው የኤክስ አገልግሎት መቋረጥ “በመላው ዓለም” ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተናግሯል።

መስክ ከዚህ ቀደምም ኤክስ አገልግሎት እንዲያቋርጥ የሚያደርግ (ዲዲኦኤስ) ሙከራ እንደተደረገ ጠቁሞ ነበር። ሆኖም ግን አልተረጋገጠም።

ትናንት የተከሰተውን የአገልግሎት መቋረጥ ተከትሎ በሰጠው አስተያየት የአሪዞና የሕዝብ እንደራሴ ማርክ ኬሊን “ከሃዲ” ሲል ከሷል።

የሕዝብ እንደራሴው ወደ ዩክሬን ለጉብኝት በመሄዳቸው ነው “ከሃዲ” ያላቸው።

የሕዝብ እንደራሴው በምላሹ “ነጻነትን መከላከል አሜሪካን ታላቅና ደኅንነቷ የተጠበቀ እንደሚያደርጋት የማትረዳ ከሆነ ሥራውን ለኛ ተውልን” ሲሉ ለመስክ በኤክስ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።