
ከ 8 ሰአት በፊት
ዛሬ ማክሰኞ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት በሳዑዲ አረቢያ ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ያደርጋሉ።
አገሪቱ ለዚህ የሰላም ውይይት የተመረጠችው መሪዋ ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባላቸው ጠንካራ ግንኙነት የተነሳ ነው።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በተፋላሚዎቹ ወገኖች መካከል አደራዳሪ በመሆን ከፊት እሰለፋለሁ ብሏል።
የሳዑዲ አረቢያ ትንሿ ጎረቤት፣ ኳታርም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዓለም ታዋቂ የሰላም ባለሟል ሆናለች።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በጋዛ አሁን ያለውን የተኩስ አቁም ስምምነት በማስተባበር የመሪነት ሚና የተጫወተች ሲሆን ከዚያ በፊትም ሌሎች በርካታ እርቆች እንዲፈጠሩ አግዛለች።
ታዲያ እነዚህ ሁለቱ ጎረቤት አገራት ዓለም አቀፍ የሰላም አደራዳሪ እንዲሆኑ የተመረጡት ለምንድን ነው? በመካከላቸው ቁርሾስ ፈጥሮ ይሆን?
ሳውዲ አረቢያ የሰላም ስምምነቶችን ለማሸማገል ለምን ትፈልጋለች?
ሳውዲ አረቢያ የዛሬውን የአስታራቂነት ሚና ከመውሰዷ በፊት ለበርካታ ዓመታት ጠብ አጫሪ የሆነ ባህሪ ነበራት።
እ.ኤ.አ. በ 2015 በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መንግሥትን በመደገፍ ጣልቃ ገብታ የሁቲ አማፅያን ላይ የአየር ድብደባ እና የመድፍ ጥቃቶችን አድርጋለች።
እ.ኤ.አ. በ 2017 የሊባኖስ መንግሥት ሳዑዲ አረቢያ የሊባኖሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሰኢድ አል-ሃሪሪ ስልጣን እንዲለቁ ለማስገደድ በቁጥጥር ስር አውላለች ሲል ወንጅሏት ነበር።
እ.ኤ.አ. በ 2018 የሳዑዲ መንግሥትን በመተቸት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጅጊ በመንግሥት ወኪሎች በኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ውስጥ ተገድሏል።
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የመካከለኛው ምሥራቅ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ፖል ሳሌም “የመሐመድ ቢን ሳልማን ቀደምት አመራር ግጭት ጠማቂ ነበር” ይሉታል።
“ይኹን እንጂ አመራሩ ግጭቶችን ከማባባስ ይልቅ የሰላም ስምምነቶች ላይ በማሸማገል የተሻለ ለመስራት ወሰነ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሻሻል በዋነኛነት የሰላም ድርድሮች ላይ ስትሰራ ቆይታለች የምትለው ደግሞ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው እና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው የዋሽንግተን ኢንስቲትዩት ባልደረባ ኤልዛቤት ዴንት ናት
“ይህ በነዳጅ መላክ ላይ ያለውን ጥገኝነትን ለማቆም እና አዳዲስ የምጣኔ ኃብት ዘርፎችን በማዳበር የውጭ ንግድን ለመሳብ በሚደረገው ስልት ላይ አስፈላጊው አካል ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሳዑዲ አረቢያ የሰላም ስምምነቶችን በማድረግ ምን ስኬት አግኝታለች?
የሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ማስከበር ታሪክ በርካታ አስርት ዓመታትን የተሻገረ ነው።
እ.ኤ.አ. በ1989 በሊባኖስ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ወደ ታኢፍ ስምምነት ያመራው እና በ1990 የተኩስ አቁም የተደረሰበት ውይይት ሽምግልናን መርታለች።
ይህም በአገሪቱ ለ15 ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነት አስቁሟል።
እ.ኤ.አ. በ 2007 በሁለቱ የፍልስጤም ቡድኖች ሃማስ እና ፋታህ መካከል የነበረውን ፍጥጫ ያስቆመ የመካ ስምምነትን አሸማግላለች።
በቅርቡ፣ በልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማንን መሪ በማድረግ፣ ሳዑዲ አረቢያ እንደ ገና የሰላም አደራዳሪነት ሚናዋን ወስዳለች።
እ.ኤ.አ ከ2022 ጀምሮ በየመን ከሚገኙት የሁቲ አማፂያን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሙከራ እያደረገች ነው።
በሱዳን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ በሆኑት የአገሪቱ ወታደራዊ አዛዦች መካከል ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የቆየ ውይይትን እያስተናገደች ነው።
ሳውዲ አረቢያ በ2022 በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተደረገውን እና በሁለቱ ሀገራት ግጭት ተይዘው የነበሩ ከ250 በላይ የጦር ምርኮኞች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ያደረገውን ስምምነት በበላይነት መርታለች።
- ሱዳን ኤምሬትስን ‘በዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪነት’ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ልታቆማት ነው7 መጋቢት 2025
- ዜሌንስኪ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ልታደርገው ያቀደችው ውይይት “ፍሬያማ” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገለጹ7 መጋቢት 2025
- የአሜሪካ ዜግነት ያስገኛል የተባለው “የወርቅ ካርድ” ምንድነው? ለእነማንስ ይሸጣል?26 የካቲት 2025

ኳታር የትኞቹ የሰላም ስምምነቶች ላይ ተሳትፋለች?
ኳታር ከግብጽ እና አሜሪካ ጋር በጋራ በመሆን በጥር 2025 በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በቻለው ድርድር ላይ ቁልፍ አሸማጋይ ነበረች።
እ.ኤ.አ. በ 2020 ኳታር ለ18 ዓመታት የዘለቀውን የአፍጋኒስታን ጦርነት ለማስቆም በታሊባን እና በአሜሪካ መካከል የሰላም ስምምነትን ያሸማገለች ሲሆን፣ አሜሪካ እና አጋሮቿ ጦራቸውን በማውጣት ታሊባን አገሪቱን መቆጣጠር ችሏል።
እ.ኤ.አ. በ 2010 ምንም እንኳ ቢፈርስም በየመን በመንግሥት እና የሁቲ አማፅያን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንደደረስ አድርጋለች።
ኳታር በአፍሪካ በተደረጉ የሰላም ስምምነቶች ላይም ተሳትፋለች።
አንደኛው እ.ኤ.አ. በ2022 በቻድ መንግሥት እና በበርካታ ተቃዋሚዎቹ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አድርጋለች።
ሌላው በ2010 በሱዳን መንግሥት እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል በዳርፉር ምዕራባዊ ግዛት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ነው።
እ.ኤ.አ. በ 2008 በሊባኖስ ተቀናቃኝ አንጃዎች መካከል የነበረው ፍጥጫ ወደ አዲስ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳያመራ የተደረገውን የሰላም ስምምነትን በግንባር ቀደምትነት መርታለች።

ኳታር ለምንድን ነው የሰላም አደራዳሪ መሆን የፈለገችው?
ኳታር እአአ ከ1995 እስከ 2023 በስልጣን ላይ በቆየው ሐማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ዘመን ይህንን የሰላም አደራዳሪነት ሚና ጀምራለች።
ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ኳታር በባሕረ ሰላጤው በ1990 የተገኘውን ኖርዝ ዶም እና ሳውዝ ፓርስ ፊልድ የተባለ የጋዝ ክምችት ለማልማት ስለፈለገች ነው።
የዚህ ነዳጅ መገኛ በኳታር እና በኢራን የውሀ ላይ ግዛቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ኢራን በወቅቱ የሳዑዲ አረቢያ ጠላት የነበረች ቢሆንም ኳታር ይህንን ለማድረግ ከኢራን ጋር መተባበር ነበረባት ሲሉ የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኤችኤ ሄሊየር ያስረዳሉ።
“ኳታር ነዳጅ ስታገኝ የራሷ መንገድ መቀየስ እንዳለባት ተረዳች” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም የሰላም አሸማጋይነት ሚና መጫወትን መረጠች፣ ምክንያቱም “ከበርካታ አገራት ጋር አዎንታዊ ገንኙነት መኖር የደጋፊዎችን ቁጥር ማብዛት መሆኑን ተረድታለች”
የኳታር የሰላም አሸማጋይነት ሚና እ.ኤ.አ. በ2004 ባፀደቀችው ሕገ መንግሥቷ ውስጥ ተካትቷል።
ዶ/ር ሳሌም “ኳታር ዓለምአቀፍ አሸማጋይነትን ከአገራዊ መለያዎቿ መካከል አንዱ አድርጋ መርጣለች እና ራሷንም በዚህ ረገድ ሌሎች ሊጠቀሙባት የሚችሉባት አገር መሆኗን አውቃለች።”
ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር በሰላም አደራዳሪነት ይለያያሉ?
ኳታር ብዙ ጊዜ የሰላም ድርድሮችን ለማካሄድ የምትመረጠው ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች አገራት ግንኙነት ከሌላቸው ቡድኖች ጋር ያላትን ወዳጅነት ጠብቃ በመቆየቷ ነው።
ዶ/ር ሳሌም “ኳታር እንደ ሙስሊም ወንድማማቾች፣ ሃማስ እና ታሊባን የመሳሰሉ እስላማዊ ቡድኖች ላይ እንደ ሳዑዲዎች ጥልቅ ጥላቻ የላትም” ብለዋል ።
ኳታር ከታሊባን ጋር ያላት ግንኙነት በቡድኑ እና በአሜሪካ መካከል አሸማጋይ እንድትሆን እንደረዳት እንዲሁም ከሃማስ እና ከእስራኤል ጋር የፈጠረችው ግንኙነት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ለማድረግ እንደረዳት ይናገራሉ።
“ሳዑዲ አረቢያ ቅቡል የሆኑ ጉዳዮች እና ወገኖች ጋር፣ ኳታር ደግሞ ከተገለሉ አማፂያን ጋር ለድርድር ይቀመጣሉ” ትላለች ዴንት።
ነገር ግን ኳታር የሳዑዲ መንግሥት ለአገዛዙ አስጊ ናቸው ብሎ የሚያያቸው እንደ ሙስሊም ወንድማማች ያሉ ቡድኖችን ስስ ልብ ነው ያላት።
“በአረብ አብዮት (እ.ኤ.አ. በ2010 እና 2011) ኳታር እንደ ሶሪያ እና ሊቢያ ባሉ ቦታዎች ላሉ ተቃዋሚ ቡድኖች ያልተቋረጠ ድጋፍ ሰጥታለች” ትላለች።
” ይህም አቋሟን በጣም ግልጽ አድርጎታል።”
በዚህም የተነሳ በ2017 ሳውዲ አረቢያ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ እና “የባህረ ሰላጤው ፍጥጫ” እንዲቀሰቀስ አድርጓል።
“ፍጥጫውን ተከትሎ ኳታር ከጎረቤቶቿ ጋር ሳትመካከር ከአክራሪ ቡድኖች ጋር የምታደርገው ግንኙነት ወዳጅነትን እንድታቆም አድርጓታል ” ትላለች ዴንት።
“አሁን እንደ አሸማጋይ ይበልጥ ገለልተኛ ሆናለች።”
ዶ/ር ሄይለር ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ የሰላም አሸማጋይ ማን እሁን በሚለው ጉዳይ ላይ አይጋጩም ብለዋል።
“በአሁኑ ጊዜ ኳታር ከሳዑዲ አረቢያ ጋር መወዳደር አትፈልግም፤ ሳዑዲ አረቢያም ማንኛውንም ኳታር የያዘችውን ጉዳይ መውሰድ አትፈልግም” ብለዋል ።
“በሚያሳዝን ሁኔታ አሁንም በዓለም ላይ ሁለቱንም አገራት የሚያባትሉ በቂ ግጭቶች አሉ።”