
ከ 7 ሰአት በፊት
ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል “በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” በማለት አስጠነቀቁ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳም “በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በግልጽ የሚታይ መቃቃር አለ። የእኔ ስጋት ይህ ከቃላት አልፎ ወደ ጦርነት እንዳያድግ ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ ለቀጠናውም ዳፋ እንደሚሆንም ጄኔራል ፃድቃን በእንግሊዘኛ ባስነበቡት ጽሑፍ አስታውቀዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረግ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች እንደሚባለው “አጭርና ወሳኝ” እንደማይሆን የገለጹት ጄኔራል ፃድቃን ለቀጠናው አውዳሚ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
“ጦርነቱ ሲያከትም አሁን የምናውቀው የአገራቱ ጂኦግራፊ ይለወጣል። በአፍሪካ ቀንድና ከቀይ ባሕር አሻግሮም ጉልህ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ ያስከትላል” ብለዋል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ የሆኑት ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚቀሰቀሰው ጦርነት “የሱዳንና የቀይ ባሕር ደኅንነት ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብለዋል።
“በጦርነቱ ማዕከላዊ የምትሆነው በደንብ የሠለጠነና ልምድ ያካበተ ከፍተኛ የወታደር ቁጥር ያላት ትግራይ ናት” ሲሉም አክለዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የግጭት ስጋት እንዳለ ከተለያየ አቅጣጫ ሲሰማ ቆይቷል።
በተለይም የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በአልጀዚራ ላይ ያስነበቡት የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቀጠናው ለሚፈጠር ተጠያቂ የሚያደርግ ጽሑፍን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መካረር ተባብሷል።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ለዚህ ጽሑፍ ምላሽ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን እየተነኮሰች እንደሆነ የሚከስ ጽሑፍ በኤክስ ገጻቸው ሰጥተዋል።
ከፕሪቶርያ ስምምነት በኋላ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት እንደሻከረ ጠቋሚ ምልክቶች ቢኖሩም ከሁለቱም አገራት በኩል በይፋ የተባለ ነገር አልነበረም።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጎን መሰለፉ አይዘነጋም።
- አቶ ጌታቸው ረዳ ሦስት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችን አገዱከ 7 ሰአት በፊት
- ማርኮ ሩቢዮ ዮክሬን ያቀረበችው የከፊል ተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ‘ተስፋ ሰጪ’ ነው አሉከ 8 ሰአት በፊት
- ሰሜን ኮሪያውያን በታሪክ ትልቁ የተባለውን የክሪፕቶከረንሲ ማጭበርበር እንዴት ፈፀሙ?ከ 8 ሰአት በፊት
ጄኔራል ፃድቃን “ትግራይ ከዚህ ጦርነት መራቅ” እና “ሰላም እንዲሰፍን” እንደምትሻ በጽሑፋቸው ገልጸዋል።
“ለሰላም ያለው ዕድል እየጠበበ ቢሆንም ወደ ግጭት ላለመግባት ሁሉንም መንገዶች መጠቀም እንደሚያሻ” ተናግረዋል።
ከፕሪቶርያ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠልሸቱን በማስታወስ ጦርነት “አይቀሬ” መሆኑንም ጄኔራሉ ጠቅሰዋል።
“ዝግጅቱ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው። ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት አንዳች ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደኋላ መመለስ ይከብዳል” ብለዋል።
እየመጣ ባለው ጦርነት ምክንያት ትግራይ ከአካባቢያዊ ፖለቲካ፣ታሪክና ባህልም አንጻር ስጋት ውስጥ እንደሆነች የተናገሩት ጄኔራል ፃድቃን “የኔ ምርጫ ትግራይ ለሰላም ጥሪ እንድታደርግ ነው። ብዙ ተሰቃይተናል” ብለዋል።
ሆኖም ግን “መሪዎች ከድርድር ይልቅ ጦርነትን በሚመርጡበት ወቅት” በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለሚኖረው ጦርነት የጦር አውድማ ትግራይ እንደምትሆን ስጋታቸውን በጽሑፋቸው አስተጋብተዋል።
ትግራይ በአፍሪካ ቀንድ ባላት ቦታ እንዲሁም ከአማራና አፋር ክልሎች ጋር አዋሳኝ መሆኗ “ለሌሎች ሰዎች ጦርነት አስፈላጊ ያደርጋታል” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸውም አሁን ያለው ሁኔታ “ወደ ጦርነት እንዳያድግ ማለታችን ብቻ ጦርነትን ስለማያስቀር፣ ትግራይ አስፈላጊ ወዳልሆነ ጦርነት ሳትፈልግ እንዳትገባ ማድረግ” እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
“ለጊዜው አቅሜ፣ አቅማችን የሚፈቅደው ይሄን ነው የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል አቶ ጌታቸው።
ከሁለት ዓመት በፊት ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ተጀምሮ እንደነበር የጠቀሱት የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ እስከ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ድረስ ግንኙነቱ “ጥሩ” እንደነበር ጠቅሰዋል።
“በዚህ ግንኙነት ግን ‘ከእገሌ አንጻር’ የሚል ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት የለኝም። የኤርትራ መንግሥት ከነሙሉ ጥፋቱ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፈጸመው ሁሉንም ዓይነት ጥፋት ጋር ሰላም የመፍጠር ፍላጎት አለን” ብለዋል።
“የኤርትራ መንግሥትን የወራሪነት ባህሪ አስተውያለሁ። እንደ ኢትዮጵያና ሱዳን ያሉ አገራትን እንደ መጠቀሚያ ያደርጋል” ያሉት ጄኔራል ፃድቃን የኤርትራን መንግሥት ፍላጎት “እንደ እስራኤል አይበገሬ፣ እንደ ሲንጋፖር የበለፀገ እንደ ዴንማርክ ጤናማ መሆን” ሲሉ ገልጸውታል።
ይህንን ፍላጎት ኤርትራ ባላት ሃብት ከማሳካት ይልቅ “ከመረብ ወንዝ በስተደቡብ ካሉ ወንድሞች ጋር ግጭት ውስጥ በመግባት” ለማሳካት ይሞክራሉ ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ከስሰዋል።
“ኢሳያስና ተከታዮቹ ለሕልማቸው ዋነኛ መሰናክል ትግራይ ናት። ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት ሞክረዋል. . . ትግራይ አሁንም የህልውና አደጋ ውስጥ ናት” ሲሉም አክለዋል።
በትግራይ አመራሮች መካከል ያለውን ክፍፍል የጠቀሱት ጄኔራል ፃድቃን “ከቀደመና ከአሁንም ወንጀላቸው ተጠያቂነት ለማምለጥ ከኤርትራ ጋር መወገን የሚመርጡ የትግራይ ልጆች አሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ክፍፍል በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ መሰማት የተጀመረው።
ጄኔራል ፃድቃንም ይህንን የህወሓት ክፍፍል በመጥቀስ “ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በመወገን ዐቢይ አሕመድን ከሥልጣን ለመገልበጥ” የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በበኩላቸው “አሁን ያለው ፍላጎት ግን፣ እገሌ እገሌ ማለት አልፈልግም፣ ከኤርትራ ጋር የተገናኙ እንዳሉ አውቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም “በግል ነው በተደራጀ መልኩ የሚለውን ለጊዜው ትተን፣ አሁን ሁሉም የሚፎክርበት ሁኔታ ነው ያለው። ሥርዓት ያለው ነገር እየተፈጠረ ስላለሆነ፣ ከፋኖ ጋር ከእገሌ ጋር ግንኙነት ጀምሬአለው የሚል ብዙ ነው” ብለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት “ተፈናቃዮችን መመለስን የሚመለከት ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው “ኤርትራን ማጥቃት የሚል አጀንዳ ማንሳት አልችልም። ግን የማይቀር ነገር አለ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት ግጭት ውስጥ ከገቡ፣ በጸሎት ብቻ እንደማንድን አውቃለው” ሲሉ አክለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረቱ በዩክሬን፣ በመካለኛው ምሥራቅና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ በሆነበት ወቅት የሚነሳው ጦርነት የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን ጄኔራል ፃድቃን ተናግረዋል።
የጦርነቱን ውጤት የሚወሰነው እንደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ግብፅና ቱርክ ባሉ አገራት እንደሚሆንም በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቋም የፕሪቶርያ ስምምነትን ማስጠበቅ መሆኑን ጄኔራል ፃድቃን ገልጸው፣ ስምምነቱ አደጋ ውስጥ በመውደቁ “የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብቶ ሌላ አውዳሚ ጦርነት ያስቁም” ሲሉ አሳስበዋል።