የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች

ከ 8 ሰአት በፊት

ምግብ የሕይወት ትልቁ ድጋፍ ነው።

የምግብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ያለ ምግብ’ማ ባዶ ጆንያ ነን፤ ልንሰባበር እንችላለን ይላሉ።

ለዚህም ነው ምግብ ላይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት እያሉ የሚያስጠነቅቁት።

ለስኳር ህሙማን ሲሆን ደግሞ ጥንቃቄውን ያገዝፈዋል።

ባለፈው የካቲት ወር በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁለት ታላላቅ እምነቶች ምዕመናን ፆም የጀመሩበት ነው።

የክርስትና እና የእስልምና አማኞች በአሁኑ ወቅት የዐቢይ ፆም (ሁዳዴ) እና የረመዳን ፆምን እየፆሙ ናቸው።

የስኳር ህሙማን ፆም የሚፆሙ ከሆነ ምን ዓይነት ምግብ መመገብ አለባቸው? ምን ዓይነትስ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው?

ዶ/ር ይሁኔ አየለ በዲላ ዩኒቨርስቲ የምግብ ሳይንስ እና ኒውትሪሽን ተመራማሪ ናቸው።

ከስኳር በሽታ ምንነት ጀምሮ ታማሚዎች በፆም ወቅት ምን ዓይነት የአመጋገብ ሥርዓት መከተል እና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ይለግሳሉ።

የስኳር በሽታ ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የስኳር በሽታ የዚህ ዘመን አደገኛ በሽታ ተብሎ የሚጠራ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ነው።

የሰውነት ክብደትን ወይም ስባትን ተከትሎ የሚመጣ እና ብዙ ሰዎችን እያሰቃየ ያለ በሽታ ነው።

የበሽታው መንስኤም በሰውነታችን ውስጥ ያለው የምግብ ልመት (ዳይጀሽን) ሥርዓት መታወክ ነው።

ምግብ ደግሞ ሕይወትን የሚያሽከረክር የኃይል ምንጭ ነው።

የስኳር በሽታ ይህን የኃይል ምንጭ የሚያስተጓጉል ነው። ምግብ በምንመገብበት ጊዜ በተለይም ኃይል ሰጪ (ካርቦሃይድሬት) ምግቦች በሰውነት በማላሚያ ስርዓት ውስጥ ገብተው ወደ ጉልኮስ ይቀየራሉ።

ይህ ጉሉኮስ ወደ ህዋስ (ሴል) በመግባት ተቃጥሎ ኃይል ሰጥቶ ዕድገት እንዲኖረን፣ እንድንቀሳቀስ አልያም ማንኛውንም የሕይወት እንቅስቃሴዎች እንድናደርግ ያደርጋል።

የስኳር ህመም ሲከሰት በምግብ ልሞ እና ደቅቆ ወደ ህዋስ ገብቶ ተቃጥሎ ኃይል በመስጠት ሕይወትን ማንቀሳቀስ አልተቻለም ማለት ነው።

የስኳር በሽታ አንደኛው ምልክት ድካም የሆነውም ለዚህ ነው።

በአጭሩ የስኳር በሽታ ማለት በሰውነታችን ውስጥ ኃይል ሰጪ ምግቦች ወይም የስኳር ምግቦች ልመት ሥርዓት ውስጥ ወደ ህዋስ እንዲገባ የሚያደርጉ ሆርሞን (ኢንሱሊን) አለመመረት ወይም አለመሥራት ነው።

የስኳር በሽታ በሁለት መንገድ ሊመጣ ይችላል።

ህዋሳት ለኢንሱሊን መታዘዝ ሳይችሉ ሲቀሩ አንደኛው መንስኤ ነው። ለምሳሌ ሕጻናት አፋቸውን ከገጠሙ መመገብ እንደማይችሉ ሁሉ ህዋሳትም በተለያየ ምክንያት አፋቸውን ገጥመው ግሉኮስ አላስገባም ሊሉ ይችላሉ።

ሁለተኛው መነሻ ምክንያት ደግሞ የኢንሱሊን አለመመረት ነው። ህዋሳት ግሉኮስን ወይም ስኳርን ማስገባት ቢፈልጉ እንኳ ተቀባዩ ኢንሱሊን በጣፊያ አማካኝነት ሳይመረት ሲቀር ነው።

ሦስት ዓይነት የስኳር በሽታዎች ያሉ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ 90 በመቶው የማኅበረሰብ ክፍልን እያጠቃ ያለው “ዓይነት ሁለት” (ታይፕ-2) ተባለው ነው።

ረመዳን እና የስኳር በሽታ

የረመዳን ፆም ከፀሐይ መውጣት እስከ መጥለቅ ድረስ ሰውነትን ከመጠጥ እና ከምግብ በመገደብ ይፆማል።

ታዲያ የስኳር ህሙማን በረመዳን ፆም ወቅት ምን ዓይነት አመጋገብ መከተል አለባቸው?

የስኳር በሽታ በአጭር አገላለፅ የኃይል መራብ ማለት ሲሆን፣ ፆም ደግሞ ከኃይል መራቅ ማለት ነው።

ይህ መራቅ ደግሞ ለተዳከመው ሰውነት ኃይል እንዲያስፈልግ ያደርገዋል።

በሌላ አገላለፅ የሚፆሙ ሰዎች ስኳር ወደ ደማቸው እየገባ አይደለም ማለት ነው።

ረጅም ሰዓት (12 ሰዓት) የሚፆሙ ሰዎች ደግሞ ስኳር ከደማቸው እየጠፋ ይሄዳል።

“ወረደ ስኳር” ብለው የሚጠሩት ዶ/ር ይሁኑ፤ በዚህ ወቅት አዙሮ ሊጥላቸው ወይም በሰውነት ውስጥ የውሃ መድረቅ (ዲሃይድሬሽን) ሊደርስባቸው እንደሚችል ይናገራሉ።

ይህም “በጣም አደገኛ ነው” ይላሉ።

የስኳር ህሙማን በፆም ወቅት ለሰውነት ስኳርን ቀስ እያሉ የሚለቁ፤ በጣም ያልላሙ እና ያልጣፈጡ ምግቦችን መመገብ አለባቸው።

ለምሳሌ ቤታችን ለሻይ እና ለሌሎች መጠጦች የምንጠቀመው ስኳር፣ ፉርኖ ዳቦ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ . . . ምግቦች ረሃብ ላይ ለቆየው ሰውነት ስንመገባቸው ስኳርን ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ።

በረመዳን ፆም የሚዘወተረው ቴምርም በዚህ መልኩ ሊገለፅ ይችላል።

ቴምር፣ ስኳር ላለባቸው ሰዎች የስኳር መጠናቸውን ከፍ ሊያደርግ ስለሚችል እንዲመገቡት አይመከርም።

በመሆኑም የስኳር ህሙማን ቀስ እያሉ ስኳርን የሚለቁ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጭማቂ (ጁስ)፣ ውሃ ወዘተ በመውሰድ አመጋገባቸውን እንዲያስተካክሉ ይመከራል።

የቅባት እና የፕሮቲን ምግቦችም የደምን የስኳር መጠን ስለማይጨምሩት ምድባቸው ከእነዚህ የሆኑ ምግቦችን መመገብ ይቻላል።

ከተለያዩ ያልተፈተጉ ጥራጥሬዎች እና እህሎች የሚዘጋጀው ሾርባን መመገብም ይመከራል።

በሌላ አገላለፅ ቁልፉ ነገር በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍም ዝቅም ሳይል እንዳይዋዥቅ ማስተካከል በመሆኑ፤ ይህን ሚዛን የሚጠብቁ ምግቦች ከአትክልት ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ኩከምበር፣ ዱባ . . . ከጥራጥሬ ደግሞ ኦቾሎኒ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ምስር . . .መመገብ ጠቃሚ ነው።

ዐቢይ ፆም እና የስኳር በሽታ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ለሁለት ወራት የሚፆመው ዐቢይ ፆም ከእንስሳት ተዋፅኦዎች በመገደብ እስከ ቀኑ 9፡00 እና ከዚያም በላይ የሚፆም ነው።

ባለሞያዎች ምግብ ከሁለት ምንጮች ከእንስሳት እና ከእጽዋት ይገኛል ይላሉ።

ከእንስሳት ንጥረ ነገሮች (ኒውትሬሽን) በቀላሉ ይገኛሉ። በአጭሩ የእንስሳት ተዋፅኦ የሆኑ ምግቦች ንጥረ ነገሮችን በቀላሉ የሚለቁ ናቸው።

ለማሳያ ያህል ከሥጋ እና ከዕጽዋት የሚገኝ አይረን (ብረት) የተባለው ንጥረ ነገር፤ እጽዋት በከፍተኛ ደረጃ ሊሰጡ የሚችሉት 15 በመቶ ብቻ ነው።

ይህም ማለት 85 በመቶው ጥቅም ላይ አይውልም ማለት ነው።

በሌላ በኩል የእንስሳት ተዋፅኦዎች ከ30 እስከ 40 በመቶ አይረንን ይሰጣሉ። ይህም እነዚህ የእንስሳት ምርቶች ታኝከው ወይም ተዋህደው በቀላሉ የሚፈለገውን ንጥረ ነገር ይሰጣሉ።

ለዚህም ነው ዶ/ር ይኹኔ እጽዋትን ንጥረ ነገሮች በቀላሉ ባለመስጠት “ንፉግ” ሲሉ የሚጠሯቸው።

የኢትዮጵያውያን አመጋገብ ስብጥር ሲታይ የተለመዱ እና አንድ ዓይነት ምግቦችን በመመገብ የሚታወቅ ነው።

በዚህ የአመጋገብ ሥርዓት ፆም ሲጨመርበት በቀን የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት ከባድ እንደሚያደርገው ባለሞያዎች ያነሳሉ።

በመሆኑም የሚሉት ተመራማሪው ጿሚዎች የምግብ ስብጥራቸውን ሰፋ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

እንደ ተልባ፣ ለውዝ፣ ሰሊጥ ያሉ የቅባት እህሎችን መመገብ ይመከራሉ።

ገንቢ (ፕሮቲን) ምግቦችም የሚመከሩ ሲሆን ከባቄላ የሚዘጋጀው ስልጆን የመሳሰሉ ምግቦችን በመመገብ የምግብን ስብጥር ሰፋ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ስኳርን ቀስ አድርገው የሚሰጡ እንደ አትክልት ካሉ ምግቦች በተጨማሪም በፆም የተከለከሉ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን ሊተኩ የሚችሉ እንደ ምስር፣ አተር፣ ባቄላ፣ አኩሪ አተር እና የመሳሰሉ ምግቦችን በተለያየ መንገዶች በማዘጋጀት መመገብ ያስፈልጋል።

ይህም ለስኳር በሽታ የተስማማ ብቻ ሳይሆን “የእጥረት በሽታ” ለመከላከል ይረዳል።

በፆም ወቅት በሽታ የመከላከል ሥርዓትም ስለሚወርድ ሁኔታውን ተጠቅመው የሚከሰቱ በሽታዎች እንዳይጠቁም ጥንቃቄ ይሻል።