የሽግግር መንግሥት በተናጠል በክልል ደረጃ ሊመሠረት አይችልም!

*በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመኢአድ፤ ኢሕአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ*

አገራችን የገባችበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ወደ አገራዊ ቀውስ እያደነ ባለበትና ከዚህም ለመውጣት አገር አድን ርብርብ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት ከሰሞኑ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የደረሱበት ስምምነት በአመዛኙ እሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ የሚቆጠርና ቀን አይቶ የመጣል አዝማሚያ ያለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ስምምነት ተደርሶባቸዋል ተብለው ከተነሱትና በአቋም መግለጫ መልክ ከወጡት ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግሥት ማቋቋም፡ አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ ማጠቃለል፡ መተከል፣ ወሎ፡ ድሬደዋ፡ ሞያለና ሐረርን የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ ከልሎች ወደ አሮሚያ ማካተት፡ በክልሉ ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በገዳ ሥርዓት እንደሚተገበሩ፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሽግግር መንግሥቱ ሠራዊት ማድረግና የኦሮሚያን ዳር ድንበር እንዲያስከብርና በክልሉ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማስቻል የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው:: እኛ የትብብር ፓርቲዎች በኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም በመላ እገራችን ሰላም እንዲሰፍን ለዚህም ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት መንግሥትን ያለመታከት ስንወተውት ቆይተናል። አሁንም ሰላም በአገራችን እንዲሰፍን ሁላችንም በጋራ መታገል ያለብን ወቅት ነው እንላለን። ላለፉት ስድስት ዓመታት የመከራ ሕይወት እየገፋ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ በጋራ ታግለን የሚናፍቀውን ሰላም እውን ማድረግ ይጠበቅብናል እንጂ በተናጠል ያውም በክልል ደረጃ ወርድን የሚመጣ ሰላም አይኖርም፤ የአገራችንን እንድነትም ማስጠበቅ አይቻልም። በአንድ ክልል ሊቋቋም የታሰበው “የሽግግር መንግሥት” አገራችን አሁን ከምትገኝበት ሁኔታ የበለጠ ያመሰቃቅላል፡ ችግሮችንም ያባብሳል እንጂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል። በሁሉም አካባቢ ሰላም ካልሰፈነ፣ ማንም ወገን ብቻውን ነፃ አይወጣም፣ የትኛውም ክልል ውስጥ በተናጠል ሰላም አይሰፍንም። ስለሆንም በተናጠል በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግሥት ማቋቋም የሚለውን አስተሳሰብ አጥበቀን እንቃወማለን።

በአንድ በኩል ጦርነት ይቁም እያሉ በሌላ በኩል ከአጎራባች ክልሎች ጋር ጦርነት እንግጠም የሚሉ ከግጭት ጠመቃ የሚመነጩና እርስ በእርስ የሚጣረሱ፣ ከልሉን ጥቂት ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሞኖፖል የያዙት ደሴት በማድረግና ራስን ብቸኛ ወኪል አድርጎ በማስቀመጥ አሁንም የተጠቂ ፖለቲካና የመጡብህ ዓይነት ቅስቀሳ የማራመድ፣ የስልጣን ጠበኛ የዓላማ ተጋሪ መንፈስ ያዘለ፣ አገር የገባችበትን ቀውስና ትልቁን አገራዊ ሥዕል ያልተመለከተ ወይም መመልከት ያልፈለገ አካሄድ መሆኑን ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ይህ አካሄድ በአገር ፍርስራሽ ላይ የራስን ጎጆ ለመቀለስ ያለመ፡ ቅርብ አዳሪ፣ ፍትሕ አልባ፣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና ኢ-ሞራላዊ ሆኖ አግኝተነዋል።

በታሪክም በሕገ መንግሥቱም አዲስ አበባ የሁሉም ኢትጵያዊ ከተማ፣ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫና ራሷን የቻለች የከተማ አስተዳደር የተዋቀረላት እንዲያውም በሽግግሩ ቻርተር ከልል የነበረችን፣ ከዚያም አልፎ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችን ከተማ የአንድ አጎራባች ክልል አካል አድርጎ ማሰብና መጠየቅ ከቀን ቅዠትና ከፀብ ያለሽ በዳቦ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ በተጨማሪም መተከል፣ ወሎ፡ ድሬደዋ፣ ሐረርንና ሞያሌን ወደ ኦሮሚያ ለማጠቃለል መሻት ምናልባት በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ከልሎች በኢኮኖሚ፣ በጦርነትና የውስጥ ቁርቁስ የተዳከሙ በመሆናቸው ጎዶሎ ቀናቸውን ጠብቆ ወረራ ከመፈጸም ተለይቶ የማይታይና የስብስቡም ፍላጎት የመጨረሻ ግቡ የት ድረስ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። እርግጥ አገራችን ውስጥ ጠያቂና ተጠያቂነት ስለጠፋ ዛሬ እንዳሻው መሆን መቻሉ ጠቅሞ ይሆናል፡፡ ምናልባት በኮሪደር ልማት ስም በከተማው ተፈናቃይና እረፍት አልባ የሆነውን የአዲስ አበባ ሕዝብ ለጥቅለለው እያዘጋጁት ይሆን እንድንልም አስገድዶናል፡፡

በአጠቃላይ በቅርቡ በአነግና በአፌኮ የተደረሰው ስምምነት አገራችንን በበርካታ አሥርት ዓመታት ወድኋላ የሚመልሳት ስለሆነ በዚህ ጊዜ ቀልብ ገዝቶ አገር አድን ርብርብ ማድረግ እንጂ ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው መንፈስና በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ጥቃቅን ጎጆዎችን ለማቆም ከመሯሯጥ በአንድነት ተጋግዘን በአገራችን ውስጥ ሰላም አስፍነን ዜጎች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ወኪሎቻቸውን በመምረጥ የዜጎች መብቶች ሳይሸራረፉ የሚከበሩባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጋራ ጠንከረን እንድንታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲ

የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ