
ከ 9 ሰአት በፊት
ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ወቅት አስገራሚ ክስተቶች እንደሚፈጠሩ ለዘመናት በርካታ አፈ ታሪኮች ተነግረዋል።
አማልክት የሚገለጡበት፣ ከሰው ወደ ተኩላነት መቀየር፣ አዕምሯቸው የሚሰወር. . . ሌላም ሌላም ሙሉ ጨረቃ ስትታይ የሚካሄዱ ፌስቲቫሎች፣ ምልኪዎች ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ባለው ዘመን ቀጥለዋል።
ሙሉ ጨረቃ በየወሩ በ29ኛው ቀን ትከሰታለች።
መሬት በፀሐይ እና በጨረቃ መካከል ስትሆን ጨረቃዋ ሙሉ ሆና፣ ደምቃ እና ፍንትው ብላ ትታያለች።
ባለፈው ኅዳር 6/2017 ዓ.ም. ታላቋ ጨረቃ የምትባለው ታይታለች።
ጨረቃዋ ከመደበኛዋ በ14 በመቶ በልጣ እንዲሁም 30 በመቶ ደምቃ ታይታለች።
ታላላቆቹ ጨረቃዎች በዓመት ውስጥ ሦስት ወይም አራት ጊዜ የሚከሰቱ ሲሆን፣ በተከታታይ ወራትም ይታያሉ።
ሙሉ ጨረቃ በዓለም ዙሪያ ባሉ ባህሎች፣ አፈ ታሪኮች፣ ምልኪዎች እና ወጎችን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች።
በሙሉ ጨረቃ ዙሪያ የሚባሉ አንዳንድ አፈ ታሪኮችን፣ ምልኪዎች እና ፌስቲቫሎችን እንዳስሳለን።

ሙሉ ጨረቃ ለጥንታውያን ሕዝቦች
ጨረቃ በምህዋሯ የምታደርገው ዑደት፣ መደብዘዝ እና መድመቅ ከጥንት ጀምሮ ጊዜን ለመቁጠር ጥቅም ላይ ውሏል።
በአሁኗ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአውሮፓውያኑ 1957 የተገኘው የኢሻንጎ አጥንት አንዱ ማሳያ ነው።
ከጭላዳ እግር እንደተወሰደ የሚታሰበው ይህ አጥንት ከ20 ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ቀደምት የቀን መቁጠሪያ ነው ተብሎ ይታመናል።
በቤልጂየማዊ ተመራማሪ የተገኙት አጥንቶች ደማቅ ክቦችን፣ ጠቆር ያሉ ክቦችን እና ከፊል ክቦችን የያዙ ቅርጾች የሰፈሩባቸው ናቸው።
እነዚህ ክቦች የጨረቃን ድምቀት እና ቅርጽን ሊወክሉ እንደሚችሉ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ አርኪኦሎጂስት አሌክሳንደር ይናገራሉ።
ይህም አጥንቶቹ የስድስት ወር የጨረቃ ቀን መቁጠሪያነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን እንደሚገምቱ ጥናታቸውን ጠቅሰው ያስረዳሉ።
መስከረም አጋማሽ ወይም መጨረሻ ላይ የምትከሰተው ደግሞ የመኸር ጨረቃ ትሰኛለች።
በየዓመቱ በዚህ ወቅት ፀሐይ ስትጠልቅ ወዲያውኑ የምትወጣ ሙሉ ጨረቃ ናት።
በዚህ ወቅት አርሶ አደሮች የጨረቃ ብርሃንን በመጠቀም እስከ ምሽት ድረስ ሰብላቸውን ይሰበስቡ ነበር።
- ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልገው ዶ/ር ብርሃኑ ቡልቻ ማን ነው? ጨረቃስ ‘ሁለተኛ ቤታችን’ ትሆናለች?19 መስከረም 2022
- በሰሀራ በረሀ ለ50 ዓመታት ያልታየ ዶፍ ዝናብ መውረዱን የሳተላይት ምስሎች አሳዩ15 ጥቅምት 2024
- ትራምፕ ጨረቃ ላይ ማዕድን ቁፋሮ እንዲጀመር ለምን ፈለጉ?12 ሚያዚያ 2020

በሙሉ ጨረቃ የሚደረጉ ፌስቲቫሎች
ቻይና፦ በቻይና በበልግ አጋማሽ ወቅት የሚደረገው ፌስቲቫል ዞንግኩዊ ጂዬ (የጨረቃ ፌስቲቫል) ይሰኛል። በመኽር ጨረቃ ዕለት የሚከናወነው ይህ ፌስቲቫል በአገሪቱ የሕዝብ በዓል ነው። ፌስቲቫሉ 3 ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ይህም የተትረፈረፈ ምርት እንዲገኝ ለማደረግ የሚካሄድ ክብረ በዓል ነው።
በተመሳሳይም በኮሪያ የቹሴክ ፌስቲቫል በመኽር ጨረቃ ወቅት የሚካሄድ ሲሆን፣ ለሦስት ቀናት ያህል ይቆያል። ቤተሰብ፣ ወዳጅ እና ዘመድ ተሰባስቦ የመኽር ጨረቃ ዕለትን ያከብራሉ። እንዲሁም የቀደሙ አያቶቻቸውንም የሚያስቡበት የበዓል ወቅት ነው።
ሕንድ፡ በሂንዱባህል የሙሉ ጨረቃ ቀናት ፑርኒማ ይሰኛሉ። በእነዚህ ዕለቶች ጾም ይጾማል እንዲሁም ጸሎቶች ይከናወናሉ። በኅዳር ወር ውስጥ የሚካሄደው ካርቲክ ፑርቢማ በሂንዱ የቀን መቁጠሪያ መሠረት ቅዱስ ወር ነው። ሺቫ የተሰኘው ከሦስቱ የሂንዱ አማልክት አንዱ ትሪፑዋርሱራ የተሰኘውን ሰይጣን ያሸነፈበት እንዲሁም ሌላኛው አምላክ ቪሽኑ የሰውን ልጅ ከጥፋት ለመታደግ በዓሳ መልክ የተገለጠበት ነው።
በርካቶችም ይህንኑ ቅዱስ ወር በወንዞች ውስጥ በመታጠብ እና በሸክላ የተሠሩ ኩራዞችን በወንዞቹ ላይ በማብራት ያከብሩታል።
ቡድሂስቶች ደግሞ የእምነቱ መሠረት የሆነው ቡድሃ ከ2500 ዓመታት በፊት በሙሉ ጨረቃ እንደተወለደ ያምናሉ። በተጨማሪም ቡድሃ በሙሉ ጨረቃ ወቅት የልህቀት ደረጃ ላይ እንደረሰ እና በዚህም ወቅት እንደሞተ ያምናሉ። እነዚህ የቡድሃ ፑሪኒማ የተሰኙት ወቅቶች በሚያዝያ ወይም በግንቦት ወራቶች በሙሉ ጨረቃ ወቅት ይታሰባሉ።
በሲሪላንካ በየወሩ በሙሉ ጨረቃ ወቅት ፖያ ተብሎ በሚጠራው የሕዝብ በዓል የአልኮል እና የሥጋ ሽያጭ የተከለከለበት ነው።
በባሊ ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ወቅት አማልክቶች ወደ መሬት ወርደው በረከታቸውን እንዲሁም ምርቃታቸውን የሚሰጡበት ዕለት ናት ተብሎ ይታመናል። በእዚህም ወቅት ጸሎት ማድረግ፣ መስዋዕትን ማቅረብ እንዲሁም አትክልት እና ፍራፍሬ የሚተከሉበት ነው።

በሙስሊሞች ዘንድ በሙሉ ጨረቃ ወቅት ለሦስት ቀናት እንዲጾሙ ይመከራል። እነዚህ ዕለቶች አል አያም አል ቢድ በመባል ይታወቃሉ። ነቢዩ መሐመድ የጨለማዎቹን ሌሊቶች አላህ ብርሃን ስላበራላቸው ምስጋናቸውን ለመግለጽ ሦስቱን ቀናት መጾማቸው ይነገራል።
በክርስቲያኖች ዘንድም ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳበት ዕለት የትንሳኤ (ፋሲካ) ዕለት የሚከበረው በፀደይ ወቅት ምሽቱ እና ቀኑ እኩል በሚሆንበት (ስፕሪንግ ኢኩኖክስ) ተከትላ ከምትወጣው ሙሉ ጨረቃ በኋላ ባለው ዕሁድ ነው።
በሜክሲኮ እና በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገራት የጨረቃ ዳንስ የቀድምት አሜሪካውያን ባህል እንደገና እያንሰራራ ይገኛል። ለሦስት ቀናት በሚቆየው ፌስቲቫል በሙሉ ጨረቃ ምሽት ሴቶች ተሰባስበው የሚደንሱበት እና የሚያመልኩበት ነው።

ከሙሉ ጨረቃ ጀርባ ያሉ አፈ ታሪኮች እና ንግርቶች
በአውሮፓ ከጥንት ጀምሮ ሙሉ ጨረቃ በአንዳንድ ሰዎች ላይ እብደት ያስከትላል ተብሎ ይታሰብ ነበር። ሉናሲ (እብደት) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃልም ሉና (ጨረቃ) ከሚለው የላቲን ቃል የተገኘ ነው።
ሙሉ ጨረቃ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ባህርይን ያመጣል የሚለው እሳቤ ከሰው ወደ ተኩላነት የሚቀየሩ አፈ ታሪኮች እንዲነገሩ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሰዎች ያለፈቃዳቸው ወደ ተኩላነት ተቀይረው ሙሉ ጨረቃ በሚወጡባቸው ምሽቶች ማኅበረሰባቸውን እንደሚያሸብሩ ይነገራል።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግሪካዊው የታሪክ ፀሐፊ ሄሮዶተስ በአሁኑ ዘመን ሩሲያ ውስጥ በምትገኘው ስኪትያ ውስጥ የሚኖሩ ኒዩሪ የተባሉ ጎሳዎች በየዓመቱ ለበርካታ ቀናት ወደ ተኩላነት እንደሚለወጡ ጽፏል።
በአውሮፓ በ15ኛው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን ወቅት ወደ ተኩላነት ይቀየራሉ የተባሉ ሰዎች ለፍርድ ቀርበዋል።
ከእነዚህም ውስጥ በአውሮፓውያኑ 1589 በጀርመን ለፍርድ የቀረበው ፒተር ስቱብ የተባለ የመሬት ባላባት አሳፋሪ ሂደት ይጠቀሳል።
የአካባቢው አዳኞች ከሰው ወደ ተኩላነት ሲቀየር አይተነዋል በማለት ምስክርነት በመስጠታቸው ነበር ግለሰቡ የቀረበው። በዚህም ሂደት ፒተር ስቃይ እና እንግልት ከተፈጸመበት በኋላ ሰዎችን አድኖ ለመብላት ወደ ተኩላነት የሚቀይር አስማታዊ ቀበቶ እንዳለው ተናዘዘ።

ሙሉ ጨረቃ በሕይወታችን ላይ ያላት ተጽእኖ
አንዳንዶች ሙሉ ጨረቃ ስትታይ እንቅልፋቸው እንደሚረበሽ ያምናሉ።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሙሉ ጨረቃ ልትወጣ አካባቢ ወይም በምትወጣበት ዕለት ሰዎች ለመተኛት ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳሉ።
በተጨማሪም በጥልቅ እንቅልፍ የሚያሳልፉት ጊዜ ውስን ሲሆን፣ የእንቅልፍ ሰዓታቸው ያጥራል እንዲሁም በሰውነታችን ውስጥ ለመተኛት የሚያግዘው ሜላቶኒን የተሰኘው ሆርሞን መጠን ዝቅተኛ ይሆናል።
በጥናቱ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ብርሃን በማይገባባቸው ክፍሎች ውስጥ ቢተኙም በቂ እንቅልፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
በርካታ አትክልተኞች ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ወቅት የአፈርን ምርታማነት እንደሚያሻሽል በማመን ዘር ይዘራሉ አትክልትንም ይተክላሉ።
ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ወቅት የጨረቃ የስበት ኃይል በአንድ በኩል ወደ ምድር ሲስባት በሌላው በኩል ደግሞ የፀሐይ የስበት ኃይል ሌላኛውን ወገን በሚስበት ወቅት በመሬት ላይ ተጨማሪ እርጥበት የሚያመጣበት ወቅት እንደሆነ ይታሰባል።
ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ወቅት እንስሳት የመናከስ ሁኔታቸው እንደሚጨምር በአውሮፓውያኑ 2000 በዩናይትድ ኪንግደም የተደረገ አንድ ጥናት አሳይቷል።
ጥናቱ በአውሮፓውያኑ 1997 እስከ 1999 ባለው ወቅት በእንስሳት ተነክሰው ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የገቡ ታካሚዎችን በመረመረበት ወቅት ክስተቱ ሙሉ ጨረቃ በምትወጣበት ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አረጋግጧል።
ሆኖም በአፈ ታሪኩ መሠረት ከሰው ወደ ተኩላነት በተቀየሩ የተነከሱ ሰዎች እስካሁን የተመዘገበ የለም።