
ከ 8 ሰአት በፊት
የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣነት በሳዑዲ አረቢያ ካደረጉት የአንድ ቀን ወይይት በኋላ ዩክሬን በአሜሪካ የቀረበውን የ30 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሃሳቡን ለሩሲያ እንደሚያቀርቡ እና “ኳሱ በነሱ ሜዳ መሆኑን” ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት አሁን ሩሲያ “በአዎንታዊ” ሐሳብ እንድትስማማ ማሳመን የአሜሪካ ኃላፊነት ነው።
የማክሰኞው የጅዳ ውይይት በዜለንስኪ እና በዶናልድ ትራምፕ መካከል በጽህፈት ቤታቸው (ኦቫል ኦፊስ) ውስጥ ከተፈጠረው ያልተለመደ ግጭት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሄደ የመጀመሪያው ይፋዊ ውይይት ነው።
ሁለቱ አገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዋሽንግተን ከተካሄደው ፍጥጫ በኋላ ያቋረጠችውን የደህንነት መረጃዎች ልውውጥ እና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ እንደምትጀምር ተናግራለች።
የዩናይትድ ስቴትስ እና ዩክሬን መግለጫ “ሁለቱም ልዑካን ተደራዳሪ ቡድኖቻቸውን ለመሰየም ተስማምተው ወዲያውኑ የዩክሬን ዘላቂ ደህንነትን የሚያረጋግጥ ሰላም ለማስፈን ድርድር ይጀምራሉ” ብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ሩሲያ ሐሳቡን እንደምትቀበል ተስፋ አለኝ ሲሉ ማክሰኞ አመሻሽ ከጅዳ በለቀቁት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ዩክሬን “ተኩስ ለማቆም እና ለመነጋገር ዝግጁ ነች” ያሉት ሩብዮ ሩሲያ ሐሳቡን ውድቅ ካደረገች “እንግዲያው በሚያሳዝን ሁኔታ ሰላም ለማምጣት እንቅፋት የሆነው ምን እንደሆነ እናውቃለን” ብለዋል።
“ዛሬ ዩክሬናውያን የተቀበሉትን ሐሳብ አቅርበናል። ይህም የተኩስ ማቆም እና አፋጣኝ ድርድር ለማድረግ ነው።”
“ይህን ሐሳበእ አሁን ለሩሲያውያን እንወስዳለን እንደሚቀበሉትም ተስፋ እናደርጋለን። ኳሱ አሁን በእነሱ ሜዳ ነው” ብለዋል።
- ትግራይ ውስጥ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?11 መጋቢት 2025
- የዩኤስኤይድ ሠራተኞች ምስጢር የያዙ ወረቀቶችን እንዲያቃጥሉ ትዕዛዝ ተሰጣቸውከ 8 ሰአት በፊት
- በህሙማን ላይ የወሲብ እና የቁማር ሱስ ያስከተለው መድኃኒትከ 9 ሰአት በፊት
የ30 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዜሌንስኪ ሩሲያ በባሕር እና በአየር የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም ካቀረቡት ሐሳብ ያለፈ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት፤ በጄዳ ለተካሄደው “ገንቢ ውይይት” ዶናልድ ትራምፕን አመስግነዋል።
ዜሌንስኪ በቪድዮ በለለቁት መግለጫ ሩሲያ “ጦርነቱን ለማስቆም ወይም ጦርነቱን ለመቀጠል ፈቃደኛነቷን ማሳየት አለባት” ብለዋል።
“ጊዜው ሙሉውን እውነት የምናውቅበት ነው” ሲሉም አክለዋል።
ሞስኮ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። ክሬምሊን ቀደም ብሎ በለቀቀው መግለጫ ከጅዳው ውይይት በኋላ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቆ ነበር።
ሩሲያ እ.አ.አ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ከወረረች በኋላ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ተቆጣጥራለች።
ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ እና በሐሳቡም ይስማማመሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ለማጨብጨብ ሁለት እጅ ያስፈልጋል” ያሉት ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚፈረም ተስፋ አድርገዋል።
“ነገ ከሩሲያ ጋር ትልቅ ስብሰባ አለን። እና አንዳንድ ጥሩ ውይይቶች እንደሚመጡ ተስፋ እናደርጋለን።”
ዘሌንስኪን ወደ ዋሽንግተን እንዲመለሱ ለመጋበዝ ፍላጎት እንዳላቸውም አክለዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ፥ ሩሲያ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ ተወካዮች ጋር ለመነጋጋር አሻፈረኝ እንደማትል የሩሲያ የመንግስት የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።
የአሜሪካ እና ዩክሬን ልዑካን የተገናኙት ሞስኮ ውስጥ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ቢያንስ የሶስት ሰዎች ህይወት ካለፈ በኋላ ነው።
ትራምፕ እና ዘሌንስኪም ወሳኝ የሆነ የማዕድን ስምምነትን “በተቻለ ፍጥነት” ለመጨረስ ተስማምተዋል ሲል የጋራ መግለጫው ገልጿል።
ዩክሬን ለአሜሪካ ለደህንነት ዋስትና ስትሰጥ በምላሽ ዩክሬን የከበሩ የምድር ማዕድናትን ለአሜሪካ ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር። ነገር ግን ይህ ሐሳብ በዋይት ሃውስ እሰጣ ገባ ምክንያት ተደናቅፏል።
ስምምነቱ የማክሰኞው ድርድር አካል አለመሆኑን የጠቆሙት ሩቢዮ በዩክሬን እና አሜሪካ ግምጃ ቤቶች ድርድር አድርገውበታል ብለዋል።
የዩኤስ እና የዩክሬን የጋራ መግለጫ ኪየቭ በማንኛውም የሰላም ሂደት ውስጥ አውሮፓ መሳተፍ እንዳለባት “አስረግጣ ተናግራለች” ብሏል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርስላ ፎን ደር ሌየን እንዳሉት ኅብረቱ የማክሰኞን “አዎንታዊ ለውጥ” በደስታ ተቀብሎታል።
ትራምፕ የዩክሬን ፕሬዚደንት የጠየቁትን አፋጣኝ የደህንነት ዋስትና ሳያቀርቡ የተኩስ አቁምን እንዲቀበሉ በዜሌንስኪ ላይ ከፍተኛ ጫና እስከማሳደር ደርሰዋል።
አርብ እለት ትራምፕ ሩስያን ወደ ስምምነቱ ለማምጣት በሞስኮ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል ባልተለመደ መልኩ ዝተዋል። ሩሲያ በጦርነቱ ምክንያት በአሜሪካ ከፍተኛ ማዕቀብ ተጥሎባታል።