የዩኤስኤይድ አርማ

ከ 8 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ሠራተኞች ምስጢራዊ መረጃ የያዙ ወረቀቶችን እንዲያቃጥሉ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ተሰማ።

ይህ ትዕዛዝ መሰጠቱ ሠራተኞችን ግራ ያጋባ ሲሆን ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሊፈርስ ይችላል የሚለውን ግምትም ያጠናከረ ሆኗል።

የድርጅቱ ጊዜያዊ ፀሐፊ የሆኑት ኤሪካ ዋይ ካር ለሠራተኞቻቸው በላኩት ኢሜል ከዋሺንግተን ቢሮ ምስጢራዊ እና ግላዊ መረጃዎችን በማስወገዳቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ሠራተኞቹ አንድ ቀን ለሚወስድ የመረጃ ማፅዳት ሥራ በቢሮው ደጃፍ አቅራቢያ እንዲገኙም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ኢሜላቸው ያሳያል።

“የምትችሉትን ያክል ዶኪዩመንት ቅደዱ። ቀጥሎ አቃጥሉ” ይላል ፀሐፊዋ የላኩት መልዕክት።

ኢሜሉ ሠራተኞች ምስጢራዊ መረጃ የያዙ ከረጢቶች ላይ በማይጠፋ ማርከር “SECRET” እና “USAID (B/IO)” ብለው እንዲፅፉ ያዛል።

ቢቢሲ የኢሜሉን ቅጂ የተመለከተ ሲሆን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስም ጉዳዩን ዘግቦታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

የአሜሪካው የእርዳታ ድርጅት ያቃጠላቸውን መረጃዎች ቅጂ አስቀምጦ እንደሆን እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ዘ አሜሪካን ፎሬይን ሰርቪስ አሶሲየሽን የተባለው የዩኤስኤይድ ሠራተኞች ማኅበር ወረቀቶችን እንዲያቃጥሉ እንደተነገራቸው መረጃው እንዳለው የማኅበሩ ቃል አቀባይ ኒኪ ጋመር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ማኅበሩ ዶኪዩመንቶች እንዲቃጠሉ መደረጋቸው “እንዳሳሰበው” ገልፆ አንዳንድ ወረቀቶች “ከሥራቸው ለተቀነሱ የዩኤስኤይር ሠራተኞች እና ለሌሎች እርዳታዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ” ብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር ዩኤስኤይድን በማፍረሱ ምክንያት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በርካታ ማኅበራት መንግሥት የእርዳታ ድርጅቱን የመዝጋት ሥልጣን የለውም ሲሉ ይከራከራሉ።

ትራምፕ ባለፈው ጥር ወደ ሥልጣን ሲመጡ ነው የእርዳታ ድርጅቱ እንዲፈራርስ ያዘዙት።

የድርጅቱ ሠራተኞች ማኅበር የሀገሪቱ ሕግ “ለግልፅነት እና ተጠያቂነት ሲባል የመንግሥት ሥራዎች በቅጂ እንዲቀመጡ” የሀገሪቱ ሕግ ያዛል በማለት የዩኤስኤይድ ድርጊት “ሕግ የጣሰ ሊሆን ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል።

ምንም እንኳ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ምስጢራዊ የሚሏቸውን ወረቀቶች ቢያቃጥሉም ጥብቅ የሆነ አካሔድ ተከትለው እንደሆነ ይታወቃል።

ቢሊየነሩ ኢላን መስክ የሚመራው ዶጅ የተባለው የመንግሥት ገንዘብ እንዳይባክን የሚሠራ መሥሪያ ቤት ዒላማ ካደረጋቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ ዩኤስኤይድ ነው።

መስክ ድርጅቱ “ሰይጣናዊ ነው” ሲል የገለፀው ሲሆን ዋይት ሐውስ ደግሞ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራቸው ሥራቸው የግብር ከፋዩን ገንዘብ እንደማባከን የሚቆጠሩ ናቸው ብሏል።

በርካታ የድርጅቱ ሠራተኞች ከሥራቸው ሲሰናበቱ ቁጥራቸው ላቅ ያለ ደግሞ ላልተወሰነ ጊዜ እረፈት እንዲወጡ ተደርጓል።

በዩኤስኤይድ ከሚረዱ በርካታ ሀገራት መካከል ኢትዮኢጵያ እና ዩክሬን ይገኙበታል።