
ከ 9 ሰአት በፊት
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከቁጥጥር የወጣ የሰውነት እንቅስቃሴ ህመም (movement disorders) የገጠማቸው ሴቶች የተሰጣቸው መድኃኒት ያለው የጎንዮሽ ጉዳት እንዳልተነገራቸው ለቢቢሲ ገለጹ።
ሕክምና ከወሰዱ መካከል 20 ሴቶች ለቢቢሲ እንደገለጹት የተሰጣቸው መድኃኒት “አሉታዊ ወሲባዊ ባህሪ” እንዲያዳብሩ የሚያደርግ መሆኑ አልተነገራቸውም።
መድኃኒቱ ሕይወታቸውን እንዳመሳቀለውም ተናግረዋል።
ጂኤስኬ የተባለው መድኃኒት አምራች ድርጅት ባወጣው እና ቢቢሲ በተመለከተው ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው በአውሮፓውያኑ 2023 መድኃኒቱ የሕጻናት የወሲብ ብዝበዛን ጨምሮ “ወጣ ያሉ” ወሲባዊ ባህሪያት ጋር ትስስር አለው።
የመድኃኒቶቹ መግለጫ ላይ እነዚህን የጎንዮሽ ጉዳቶች አልተጠቀሱም። የዩኬ መድኃኒት ተቆጣጣሪ በበኩሉ መድኃኒቱ የወሲብ ፍላጎት እንደሚጨምር እና አሉታዊ የባህሪ ለውጥ እንደሚያስከትል ጠቅለል ያለ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጿል።
ጂኤስኬ እንዳለው የመድኃኒቶቹ መግለጫ ላይ “የተዛባ” የወሲብ ፍላጎት ሊከሰት እንደሚችል ተጠቅሷል።
አሉታዊ ወሲባዊ ባህሪ እንዳስከተለባቸው ከገለጹ ሴቶች መካከል የተወሰኑት ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ለምን ባህሪው እንደገጠማቸው አላወቁም ነበር።
ሌሎቹ ደግሞ ቁማር ውስጥ የመሳተፍ ልማድ ባይኖራቸውም የመቆመር ፍላጎት እና የእቃዎችን የመግዛት (ሸመታ) ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት አንደኛዋ አስተያየት ሰጪ ከ193 ሺህ ዶላር በላይ ዕዳ ውስጥ መግባቷን ገልጻለች።
እንደ ሌሎቹ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ከቁጥጥር የወጣ የሰውነት እንቅስቃሴ የገጠማት ክሌር እንቅልፍ አጥታ እና ከቆዳዋ ሥር በሚሰማት ህመም እየተሰቃየች እንደነበር ተናግራለች።
ከወለደች በኋላም ህመሙ ሲቀጥል ሮፒኒሮል የተባለ መድኃኒት ታዘዘላት። የጎንዮሽ ጉዳቱ በሐኪም አልተነገራትም ነበር። ህመሙ ከቆመ ከዓመት በኋላ የወሲብ ፍላጎቷ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስተዋለች።
ያጋጠማትንም ሁኔታ “በጣም ወጣ ያለ ብዬ ነው ስሜቱን ልገልጸው የምችለው” ትላለች።
ጠዋት ከቤቷ ወጥታ ወሲብ ለመፈጸም ስትሞክር ትውል ነበር። አለባበሷም ሰውነትን የሚያጋልጥ ልብስ ሆኖ ነበር። የትኛውንም ወንድ ስታይ ሰውነቷን አጋልጣ ታሳይ እንደነበር ትናገራለች።
የትዳር አጋር ቢኖራትም ባህሪውን ከማሳየት ራሷን ማስቆም አልቻለችም።
“እያደረግኩ ያለሁት ነገር ትክክል እንዳልሆነ አእምሮዬ ያውቃል። ግን እያደረግኩ ያለሁት ነገር ለራሴ እንግዳ ሆኖብኝም ቀጠልኩበት” ትላለች።
- የሚፆሙ የስኳር ህሙማን ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄ እና ሊመገቧቸው የሚገቡ ምግቦች11 መጋቢት 2025
- “ቲክቶክ በአፍሪካ ሕጻናትን በሚያካትቱ ወሲባዊ ቀጥታ ሥርጭቶች ትርፍ እያገኘ ነው”4 መጋቢት 2025
- በአዲስ አበባ ብዙ ሰዎች ‘የቫይታሚን ዲ’ እጥረት አለባችሁ የሚባሉት በስህተት ነው?13 የካቲት 2025

ያጋጠማትን ያልተለመደ ባህሪ ከመድኃኒቱ ጋር ለማስተሳሰር ዓመታት ወስዶባታል። መድኃኒቱን መውሰድ ስታቆም ባህሪውም ጠፋ።
ራሷን ያስገባችበትን አደጋ ስታስብ “አፍራለሁ እደነግጣለሁም” ትላለች።
“የደስታ ሆርሞን” በመባል የሚታወቀውን ዶፓሚን ሆርሞን የሚያነቃቁ መድኃኒቶች የወሲብ እና የቁማር ሱስ ስሜትን ሊጨምሩ እንደሚችሉ ይነገራል።
ከቁጥጥር የወጣ የሰውነት እንቅስቃሴ ህመም ያለባቸው ሰዎችን ከ6 በመቶ እስከ 17 በመቶ እንደሚጎዱም ይገለጻል።
በአጠቃላይ የመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት የሚገጥማቸው ሰዎች መድኃኒት ከሚወስዱ ሰዎች አንድ በመቶው ናቸው።
የደስታ ስሜትን እጅግ የሚያነሳሱ መድኃኒቶች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ባህሪያት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ጂኤስኬ በሠራው ጥናት ለፓርኪንሰንስ ህመም መድኃኒቱ የተሰጣቸው የ63 ዓመት አዛውንት የሰባት ዓመት ልጅ ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰው ተፈርዶባቸዋል።
መድኃኒቱ የወሲብ ፍላጎታቸውን ከቁጥጥር ውጪ እንዳደረገው እና የመድኃኒቱ መጠን ሲቀነስ ግን ይህ መሻሻል እንዳሳየ በሰጡት ቃል ገልጸዋል።
የ45 ዓመት ጎልማሳ “ከቁጥጥር ውጪ ወሲባዊ ባህሪ እንዳሳዩ እንዲሁም ሰውነታቸውን እንዳጋለጡም” ተመዝግቧል። ይህም በመድኃኒቱ ምክንያት የተባባሰ ነው ተብሏል።
የኒውሮሳይካትሪ ፕሮፌሰር ቫለሪ ቩን እንዳለችው፣ እነዚህ ጠባዮች በማኅበረሰቡ ተቀባይነት የሌላቸው ስለሆኑ ባህሪያቱ የታዩባቸው ሰዎች ሪፖርት ሳያደርጓቸው ሊቀሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው።
የመድኃኒቶቹ የጎንዮሽ ጉዳት በግልጽ መጠቀስ እንዳለበትም ትናገራለች።

ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ 20 ሰዎች እንዳሉት፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ ሳይነገራቸው ከመቅረቱም ባሻገር ለታየባቸውን ለውጥ ሐኪሞች መፍትሔ አልሰጡም።
ሳራ መድኃኒቱን የጀመረችው በ50 ዓመቷ ገደማ ነው።
“ብራድ ፒት እንኳን እርቃኑን ክፍሌ ቢገባ ምንም የማይመስለኝ ሰው ድንገት የወሲብ ፍላጎቴ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ” ስትል ያጋጠማትን አስረድታለች።
በበይነ መረብ አማካኝነትም የወሲብ ቪድዮ እና የውስጥ ሱሪ መሸጥ ጀመረች። የስልክ ወሲብም መጀመሯን ትናገራለች።
ከቁጥጥር የወጣ ግብይት በማድረግ 39 ሺህ ዶላር ዕዳ ውስጥም ተዘፍቃለች።
ሱ የተባለችው ታካሚም ሁለት ዓይነት ዶፓሚን አነቃቂ መድኃኒት ትወስድ ነበር።103 ሺህ ዶላር ዕዳ ውስጥ የገባቸው በመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ነው።
“ያጣሁት ገንዘብ ከፍተኛ ነው። ቤተሰቤን አመሰቃቀለው። ግን ሆነ ብዬ ያደረግኩት አልነበረም” ትላለች።
በአውሮፓውያኑ 2011 ጂኤስኬ በፓርኪንሰን ህሙማን ተከሷል።መድኃኒቱ ቁማር ውስጥ ስለከተታቸው ነበር የከሰሱት።
ጂኤስኬ በ2000 ስለ መድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ጥናት ቢሠራም እስከ 2007 ድረስ ይፋ አላደረገውም።
ኒውሮሎጂስቱ ዶ/ር ጋይ ሌስቸዚር ስለ መድኃኒቶቹ የጎንዮሽ ጉዳት በግልጽ ለታካሚዎች መነገር አለበት ይላል።
ጂኤስኬ ለቢቢሲ በላከው ምላሽ ከ17 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ታካሚዎች ሮፊኒሮል መታዘዙን ገልጾ፣ ይህም “ጥልቅ ምርመራ” ካለፈ እና “ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ” በኋላ መሆኑን ጠቅሷል።
የጤና ባለሙያዎችም ይህንን መድኃኒት ለህሙማን በሚያዙበት ጊዜ ምንም እንኳን በሁሉም ሰዎች ላይ የሚከሰቱ ባይሆኑም ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ የጎንዮሽ ችግሮችን ማስረዳት እንዳሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም የጤና እና ማኅበራዊ እንክብካቤ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
*በዚህ ዘገባ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች መካከል የአንዳንዶቹ ስም ማንነታቸውን ለመጠበቅ ሲባል ተቀይሯል።