
ከ 5 ሰአት በፊት
የኤችአይቪ ቫይረስን ይከላከላል የተባለው እና በየዓመቱ የሚሰጠው ክትባት ከደኅንነት አንጻር አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ወሳኝ የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራ ማሟላቱን ተመራማሪዎች ያወጡት ሪፖርት አመለከተ።
ሌናካፓቪር የተባለው ይህ ፀረ ኤችአይቪ ክትባት ቫይረሱ በሰዎች ህዋሳት ውስጥ እንዳይባዛ የሚያደርግ አቅም እንዳለው ላንሴት በተባለው የሕክምና መጽሔት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
አሁን ወሳኝ የተባለው ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ የደኅንነት ሙከራን በተሳካ ሁኔታ ያለፈው ክትባቱ ወደፊት የሚደረጉ ሙከራዎችን ማለፍ ከቻለ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል የመጀመሪያው የኤችኤይቪ መከላከያ መሆን ይችላል።
በአሁኑ ወቅት ሰዎች ለበሽታው ከመጋለጣቸው በፊት ለመከላከል የሚረዱ በየዕለቱ የሚወሰድ እንክብል እና በየስምንት ሳምንቱ የሚሰጥ ክትባት በአገልግሎት ላይ ይገኛል።
የኤችአይቪ ቅድመ መከላከያ እንክብሎች በሽታውን በመከላከል ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ ቢሆኑም በየቀኑ መወሰድ ስላለባቸው ለተጠቃሚዎች አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ።
በ2023 የወጣ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በመላው ዓለም 39.9 ሚሊዮን ሰዎች የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 65 በመቶዎቹ በአህጉረ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
- በርካታ አፈታሪኮች፣ ምልኪዎች እና ትንግርቶች ያሏት ሙሉ ጨረቃከ 8 ሰአት በፊት
- “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ11 መጋቢት 2025
- የዩኤስኤይድ ሠራተኞች ምስጢር የያዙ ወረቀቶችን እንዲያቃጥሉ ትዕዛዝ ተሰጣቸውከ 8 ሰአት በፊት
የዓለም ጤና ድርጅት፣ ግሎባል ፈንድ እና የተባበሩት መንግሥታት የኤችአይቪ ኤይድስ ፕሮግራም የበሽታውን መከላከያ አቅርቦት ማሻሻልን ጨምሮ ኤችኤቪ በሽታን በአውሮፓውያኑ 2030 ለማጥፋት በጋራ እየሠሩ ነው።
ኤችአይቪ የሌለባቸው 40 ሰዎች ተለይተው ጉልህ ተጓዳኝ ችግር ወይም የደኅንነት ስጋት የለበትም የተባለው ሌናካፓቪር ክትባት በጡንቻቸው ላይ ተሰጥቷቸው ነው የደኅንነት ሙከራው የተደረገው።
የሙከራው ክትባት ለሰዎቹ ከተሰጣቸው ከ56 ሳምንታት በኋላ የመከላከያ መድኃኒቱ በሰውነታቸው ውስጥ እንዳለ ለማወቅ መቻሉ የክትባቱን ጥንካሬ አመላካች ነው ተብሏል።
ለዚህ ዓመት በተዘጋጀው በቫይረስ እና በሌሎች በሽታዎች ዙሪያ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የክትባቱ ተመራማሪዎች ወደፊት የሚደረጉት ሙከራዎች የተለያየ ሁኔታ ላይ ኣሉ በርካታ ሰዎችን ማካተት ይኖርበታል ብለዋል።
አክለውም በየዓመቱ የሚሰጠው ይህ የኤችአይቪ መከላከያ ክትባት (ሌናካፓቪር) አንድ ጊዜ የሚወሰድ በመሆኑ የቅድመ መከላከያውን የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
ቴሬንስ ሂጊንስ የተባለው የኤችአይቪ በጎ አድራጎት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሪቻርድ አንጌል እንዳሉት “በየዕለቱ ይወሰድ የነበረው የበሽታው ቅድመ መከላከያ እንክብል ታላቅ ለውጥ ተብሎ ነበር። በመርፌ የሚሰጥ ዓመታዊ ክትባት ሊመጣ መሆኑ ደግሞ ፍጹም ለውጥ የሚያመጣ ነው” ብለዋል።
ኤኤችአይቪ ፈዋሽ መድኃኒትም ሆነ ዘላቂ የመከላከያ ክትባት ከሌላቸው በሽታዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በየዕለቱ የሚወሰዱ ዕንክብሎች እና የአጭር ጊዜ የቅድመ መከላከያ ክትባት ቢኖሩም ተደራሽነታቸው ውስን ነው።
ነገር ግን በደማቸው የሚገኙ ሰዎች ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና መድኃኒቶች በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየታደጉ ነው።