
ከ 3 ሰአት በፊት
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የፌደራል መንግሥት በክልሉ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ “የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ” በቂ ምክንያት እንዳለው ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው። ግማሽ ሰዓት ገደማ በፈጀው ቃለ መጠይቅ በቅርቡ ስላገዷቸው የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች እና በክልሉ ስለነገሰው ውጥረት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ጌታቸው በእንግሊዝኛ በሰጡት በቂህ ቃለምልልስ የፕሪቶሪያው ስምምነት አካል የሆኑት የፌደራል መንግሥት እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “በትግራይ ያለው ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን እና የፕሪቶሪያ ስምምነት መፍረስ የሚያስከትለውን ትልቅ ችግር ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው” ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ ትናንት ማክሰኞ አመሻሽ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም ይህ ድፍረት የሞላበት እርምጃ “በትግራይ ሕዝብ ላይ ወደሚካሄድ አውዳሚ ጦርነት ከማምራቱ በፊት” የፕሪቶሪያ ስምምነት ባለድርሻ አካላት እንዲቃወሙት ጠይቅዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ መጋቢት 1/2017 ዓ.ም. ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጄነራል ማሾ በየነ፣ ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ ኃይለ እንዲሁም ማከሰኞ ዕለት ጄነራል ፍሰሐ ኪዳኑ ላይ ጊዜያዊ ዕግድ እንደተጣለባቸው ይታወቃል።
የአቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማ ያረፈበት የዕግድ ደብዳቤ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች የታገዱት “ከመንግሥት ውሳኔ ውጪ መላ ሕዝባችንን እና ወጣቱን ወደ ግርግር፤ የፀጥታ ኃይላችንን ወደ እርስ በርስ ግጭት ብሎም ሕዝባችንን ወደማይወጣበት አዘቅት የሚያስገባ አደገኛ እንቅስቃሴ አልቆመም” በሚል ነው።
አቶ ጌታቸው ከሠራዊት አመራሮች መታገድ ማግስት በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ “ውሳኔ” ያሉትን ተግባራዊ ለማድረግ “ሁሉንም እርምጃዎች” መውሰድ በመጀመራቸው እንደታገዱ ገልጸዋል።
“የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ሰብረው እየገቡ ነው፣ ጊዜያዊ የአስተዳደር ኃላፊዎችን እያነሱ ነው፣ ይህ ደግሞ በሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በራሱ በሠራዊቱ ውስጥ ውዥንብር ፈጥሯል” ብለዋል።
“ጥያቄው ፕሬዝዳንቱን ወይም የካቢኔ አባላትን [ከሥልጣን] የማንሳት እና አለማንሳት አይደለም፤ ከሁሉም በላይ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘውን ትንሽ ሰላም የማስጠበቅ ነው” ሲሉ አክለዋል።
“የውጭ ኃይሎች በዚህ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ብለን የምናምንበት ምክንያት አለን” ያሉት ጌታቸው፤ “አሁንም ይህ ውሳኔ ይቆማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
- ትግራይ ውስጥ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?11 መጋቢት 2025
- በአዲስ አበባ የንግድ ባንክ ጥበቃ ሠራተኛ ሁለት ሰዎችን ገድሎ ራሱን አጠፋከ 4 ሰአት በፊት
- የአዲስ አበባ ፖሊስ አርቲስት አንዷለም ጎሳን ከዕጮኛው ሞት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ገለጸከ 5 ሰአት በፊት
የአዲግራት ከንቲባ ቢሮ በዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን መያዙን ያረጋገጡት አቶ ጌታቸው፤ “ይህን ለማድረግ ያቀዱትን ብቻ ሳይሆን አዲግራት ላይ ብቻ ሳይሆን መቀሌ ላይ ማድረግ ይፈልጋሉ” ብለዋል።
“የትግራይን ሕዝብ ኃይል በመጠቀም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በሕገወጡ የህወሓት አንጃ ስም መያዝ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው እና ወደ ተጨማሪ ጥፋት የሚያመራ ነው” ሲሉ አክለዋል።
“ለዚህም ነው ያንን እብደት ለማስቆም የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግ እየሞከርኩ ያለሁት” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ “ያንን እብደት የማስቆም አቅም አለኝ ወይ የሚለው የተለየ ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብቶ እነዚህ ሰዎች አብደት ላይ መሆናቸውን ሊነገራቸው ይገባል” ብለዋል።
የወረዳ ምክር ቤቶች እንደገና ሊዋቀሩ ይገባቸዋል የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሕግ እና በመመሪያ መፍታት እንደምንችል በግልፅ ተናግሯል ብለዋል።
አቶ ጌታቸው “የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ከተናገራቸው እጅግ በጣም አስቂኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ [ጊዜያዊ አስተዳደሩ] ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር በሚያደርገው ውሳኔ ላይ እንቅፋት ሆኗል” የሚል መሆኑን ጠቁመዋል።
“ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በሕገወጥ የወርቅ እና የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ማስገባት የሚለውን ሃሳብ ሲቃወሙ ቆይተዋል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም “በትግራይ ሕዝብ ላይ ለተፈፀመው ዘግናኝ ወንጀል ምንም መፍትሔ ሳያበጁ እና አሁን በየመንደሩ ማህተብ መንጠቅ ሕግ እና ሥርዓትን እንደማስከበር ተደርጎ መወሰዱ ከንቱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በቃለ መጠይቃቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ውጥረት ነው።
“በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ግጭት እንዲፈጠር አልፈልግም” ያሉት ጌታቸው “የሚፈጠር ከሆነም የትግራይ ሕዝብ የገፈቱ ቀማሽ እንዲሆን አልፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “የትግራይ ሕዝብ በዚህ ዓይነት ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ አልፈልግም፣ አንዳንድ ባልደረቦቼ ይህንን ሀሳብ ውስጥ ያስገቡ አይመስሉም፣ ወይም የትኛውንም ክፍተት ለመጠቀም ያሰቡ ይመስላሉ፣ እና እኔ ልለው የምችለው ማንም ሊገምተው ከሚችለው በላይ አስከፊ ነው” ብለዋል።
ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል “በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” በማለት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ መናገራቸው ይታወሳል።
ጦርነቱ ለቀጠናውም ዳፋ እንደሚሆንም ጄነራል ፃድቃን በእንግሊዝኛ ባስነበቡት ጽሑፍ አስታውቀዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረግ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች እንደሚባለው “አጭርና ወሳኝ” እንደማይሆን የገለጹት ጄነራሉ ለቀጠናው አውዳሚ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
“ግን ይህ እንዳይሆን ተስፋ ማድረግ ብቻ ነው አሁን የምችለው። ለዚህም ነው የፕሪቶሪያ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ በመቀለ እና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ዓይነት እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ግልጽ ጥሰቶች ሳይኖሩበት እንዲተገበር እየሞከርን ያለነው” ሲሉ አክለዋል።