
11 መጋቢት 2025
ለወራት የቆየው በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። ባለፉት ወራት በደብረፂዮን (ዶ/ር) የሚመራው ወገን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል።
በአቶ ጌታቸው የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ይህ ሙከራ በክልሉ አለመረጋጋት በማስፈን ያለውን ችግር እንደሚያባብስ በመግለጽ ቢያስጠነቅቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረቱ እየተባባሰ ይገኛል።
ባለፉት ቀናት በክልሉ ያሉት ታጣቂ ኃይሎች አመራሮች ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት የደብረፂዮን ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ተቋማትን በኃይል የመቆጣጠር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑ እየተገለጸ ነው።
ይህ ሁኔታም በክልሉ ዳግም ግጭት ሊያስከትል ይችላል በሚል ነዋሪዎች ላይ ከባድ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ አቅም ያላቸው ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያቀኑ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተለይ በአቶ ጌታቸው የሚመራው አስተዳደር የትግራይ ኃይልን ከሚመሩት ወታደራዊ አዛዦች መካከል ዋነኛ የሚባሉትን ሦስት መኮንኖች ማገዱን ካስታወቀ በኋላ ውጥረቱ አይሏል።
ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ በምሥራቃዊ ዞን የጊዜያዊ አስተዳደሩን የተቃወሙ የሠራዊት አመራሮች ከመሩት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የአዲግራት ከንቲባ ጽህፈት ቤት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ታውቋል።
ይህንን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች እና በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወይም የደረሰ ጉዳት እንዳለ አልተገለፀም።
ትናንት ሰኞ የዞኑ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለአራት ሰዓታት በዶ/ር ደብረፂዮን በሚደግፉ የፀጥታ ኃይሎች ታስረው ነበር።
የአዲግራቱን ከንቲባ ጽህፈት ቤት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ህወሓት በፌስ ቡክ ገፁ አረጋግጧል።
“የአዲግራት ከተማ ከንቲባ ሆኖ በምክር ቤት የተሾመው ረዳኢ ገብረ እግዚአብሔር በምስለኔ ግለሰቦች በተሾሙ ሰዎች ምክንያት ጽህፈት ቤቱን ተረክቦ አገልግሎት እንዳይሰጥ አደርጎ ቆይቷል” በማለት ጽህፈት ቤቱን መልሰው መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
- አቶ ጌታቸው ረዳ ሦስት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችን አገዱ11 መጋቢት 2025
- “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ11 መጋቢት 2025
- በትግራይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ 20 ሰዎች መቁሰላቸው ተነገረ21 የካቲት 2025
የትግራይ አመራሮች በወረዳ እና በዞን ደረጃ በሚደረጉ የሹም ሽር ጉዳዮች ፖለቲካዊ እሰጥ አገባ ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይህ በክልሉ አመራሮች መካከል እየተካረረ የመጣው አለመግባባት ያስከተለው የፀጥታ ስጋት ደግሞ ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ አንደሚያስታውሳቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት በሁለት ቡድን ተከፋፍለው በክህደት እና በመንግሥት ግልበጣ የሚወናጀሉት የህወሓት አመራሮች ሁኔታ በሕዝቡ መካከል ስጋት ወደ ፈጠረ አለመግባባት ገብተዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ሰኞ መጋቢት 1/2017 ዓ.ም. አለመረጋጋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው ያሏቸውን ሦስት የትግራይ ኃይሎች አዛዦችን አግዷል።
በደብረፂዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳን “የቀድሞ ፕሬዝዳንት” እንደሆኑ በመግለጽ ይህ ዕግድ ሕጋዊነት የሌለው እና ተግባራዊ የማይሆን ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል።
በተመሳሳይ የክልሉ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ እርምጃው “የተቋሙን አሠራር ያልተከተለ፣ ያልሾመውን የሚያወርድ የግለሰብ እርምጃ ነው በማለት” ቅቡል አይደለም ብሏል።
ይህ መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው ነው ያለው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በበኩሉ መግለጫው የአንጃው መግለጫ ግልባጭ ነው፤ ይህም ሕጋዊ፣ ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ በአስቸኳይ መታረም እንዳለበት አዟል።
ይህ ካልሆነ ግን “ይህንን ተከትሎ ለሚመጡ ነገሮች ሙሉ ኃላፊነት የሚወስደው በቢሮው ስም መግለጫ ያወጣው ከፍተኛ የቢሮ አመራር ነው” በማለት አስጠንቅቋል።
“እየተሸበርን ነው”
የክልሉ ሕዝብ ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ካስከተለው የገንዘብ፣ የሥነ ልቦና፣ ሰብአዊ ቀውስ አላገገመም።
ቢቢሲ ከክልሉ ማዕከላዊ እና ምሥራቃዊ ዞኖች አንዲሁም ከመቀለ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ በማስመልከት ያነጋገራቸው ግለሰቦች መሪዎቹ ወደ ጦርነት እየጎተቱ እንዳያስገቧቸው እንደሚሰጉ ይገልጻሉ።
በአዲግራት፣ በመቀለ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር፣ በገፍ መሸመት እና የመረበሽ ሁኔታ እንደሚታይባቸው ይናገራሉ።
ይህ ስጋት ከክልሉ የሚወጡ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉንም አመልክተዋል።
አብርሃም የተባለ የአዲግራት ከተማ ነዋሪ፣ “አርሚ 15፣ ሚሊሻ እና ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው አካላት የከንቲባውን ጽህፈት ተቆጣጥረዋል” ብሏል።
በከተማዋ ሙሉ በሙሉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳለ በመግለጽም “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ነው የሚመስለው። ከትናንት [ሰኞ] ጀምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለ” ብሏል።
ይህ ሁኔታ ሰላማዊ ዜጎች ላይ መረበሽ እንደፈጠረ በመግለጽ በሁለቱም አካላት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የፕሪቶሪያ ስምምነት በውል የሚያፈርሱ መሆናቸውን እንደሚያምን ይናገራል።
“ይህንን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት የፈለገውን ዓይነት እምርጃ ሊወስድ ይችላል። በትግራይ ድሮኖች ሲያንዣብቡ ሰንብተዋል። ይህ ከኤርትራ ጋር ያለው ነገር ያመጣው ሲመስለን ቆይቷል። ሆኖም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የትግራይ የፀጥታ ሁኔታን መንግሥት እየተከታተለ አንደነበር ነው የሚሰማኝ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በማዕከላዊ ዞን የሚኖረው አርሶ አደር ካህሳይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ “አለመረጋጋት” እንደፈጠረበት ይናገራል።
“ይህም ተመልሰን ወደ ጦርነት እንገባ ይሆን? የሚል ፍርሀት አሳድሮብኛል። ከዚህ በፊት ያለፈው አሰቃቂ ነው። በሰው ዕድሜ ማየት የሚገባንን አይተናል። ይህ አልፎ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ሕብረተሰቡ ተስፋ እንዲኖረው አድርጎ ነበር” ብሏል።
ቢቢሲ ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የከተማዋ እንቅስቃሴ የተለመደው ዓይነት ቢሆንም የስሜት መረበሽ እንዳለ ይገልጻሉ።
ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች አንድ የከተማዋ ነዋሪ “አንድም ደስ የሚል ነገር የለም። ገበያው ዋጋ ጨምሯል። ሰውም ፊቱ ላይ ጭንቅ ብቻ ነው የሚነበበው። ይህ ሁኔታ ዳግም መውጫ እና መግቢያ ወደ ሌለው ከበባ እንዳያስገባን ነው የምሰጋው።”
ሐዱሽ የተባለው ወጣት ደግሞ ፍርሃት እና ጭንቀት በአካባቢው የሚያየው ሁኔታ የሚገለፁበት መንገድ እንደሆነ በመግለጽ “ጦርነት አይቀርም” የሚል ስጋት አለው።
ደም አፋሳሹ የሁለት ዓመት ጦርነት ፍርሃት እንዳልለቀቀው የሚናገረው ወጣቱ “በሰላም እጦት ምክንያት መሥራት አልቻልኩም፤ አሁን ያለውን ሁኔታ ሳይ በጣም አዝናለሁ፣ እበሳጫለሁ። በከበባው ወቅት ብዙ ነገር አሳልፈናል። ረሃብ: ጥማት የካድሬዎች ጉትጎታን አሳልፈናል። ተመልሰን ወደ ዚያ ልንገባ ነው ወይ? በሚል እሰጋለሁ።”
በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ወጥተው ወደ አዲስ አበባ እና አንዳንዶቹም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለስደት ማምራታቸውን ይናገራል።
የክልሉ የፖለቲካ አመራሮች ይህ ሁሉ ስጋት እንዲጨምር አድርገዋል በሚል ይወቀሳሉ።
አስተያየት ሰጪዎቹ በምንም ሁኔታ ክልሉ አሁንም የጦር አውድማ መሆን የለበትም ይላሉ።
የህወሓት አመራሮች አለመግባባት
በትግራይ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በተፈረመ ስምምነት ተቋጭቶ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ ህወሓት ፕሬዝዳንቱን ለመቀየር ለፌደራል መንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል።
ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ፓርቲው በሊቀመንበሩ እና በምክትል ሊቀመንበሩ በሚመራ ቡድኖች ተከፍሎ ሲካሰስ መቆየቱ ይታወሳል።
አወዛጋቢ የነበረው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ እና ጥቂት በማይባሉ የድርጅቱ አመራሮች ዕውቅና ያልተሰጠው ሲሆን፣ በአመራሮች እና በአባላት መካከልም ለተፈጠረ መከፋፈል ምክንያት ሆኗል።
የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ አዛዦች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደውን የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እውቅና በመስጠት በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ጌታቸው እና ዶ/ር ደብረፂዮን የሚመሩት የህወሓት ቡድኖች ግንኙነት ሻክሮ ባለፉት ወራት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የቆዩ ሲሆን የደብረፂዮን ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በድጋሚ እንዲዋቀር በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር።
ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ኅዳር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት ይኸው ጥያቄ ተነስቶ፣ በክልሉ ምርጫ ተካሂዶ መደበኛ አስተዳደር እስኪቋቋም ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሥራ ላይ እንደሚቆይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለጹ ይታወሳል።
የህወሓት ሕጋዊነት ጉዳይ መቋጫ ካለማግኘቱ ባሻገር ባለፈወ የካቲት ወር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በደብረፂዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ማገዱ ይታወሳል።