ቀነኒ አዱኛ

11 መጋቢት 2025

ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት

የአዲስ አበባ ፖሊስ ታዋቂው ድምጻዊ አንዷለም ጎሳን ከዕጮኛው ቀነኒ አዱኛ ሞት ጋር በተያያዝ በቁጥጥር ስር አውሎት ምርመራ እያደረገበት መሆኑን አስታወቀ።

ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ እጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ለህልፈቷ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በርካታ ተከታዮች ያሏት ቀነኒ ሞትን ተከትሎ በርካቶች ሐዘናቸውን ከመግለፅ ባሻገር የሞቷ ምክንያት እንዲጣራ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ክስተቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፤ ሟች ቀነኒ አዱኛ “ከበረንዳ ላይ በወደቀችበት ወቅት በቤቱ ውስጥ የነበረውን ባለቤቷን ድምፃዊ አንዷለም ጎሳን በቁጥጥር ስር በማዋል” ምርመራ እያደረገ መሆኑን አሳውቋል።

ፖሊስ የሟች አስከሬን ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል መወሰዱን የገለጸ ሲሆን፣ የአርቲስት አንዷለም ማኔጀር ሌሊሳ ኢንድሪስም ይህንን አረጋግጦ የቀብር ሥነ-ሥርዓቷ ዛሬ ረቡዕ እንደሚከናወን ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግሯል።

ቀነኒ ከሚኖሩበት ሕንጻ መውደቋን እና “ንጋት 11 ሰዓት አካባቢ መሞቷን” ሌሊሳ ተናግሮ አንዷለም እና ቤተሰቦቹ ወድቃ እንዳገኟት አስታውቋል።

ሌሊሳ ንጋት 11 ሰዓት ሰዓት ስልክ ተደውሎ “ቀነኒ ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል እንደገባች” እንደተነገረው ገልጾ፣ “እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ከአምስተኛ ፎቅ ወድቃ ነው የሞተችው። ሁኔታውን ለማጣራት ምርመራ ተጀምሯል” ብሏል።

ማኔጀሩ አክሎም መኖሪያ ቤቱ አዲስ አበባ አራብሳ ሰንሻይን ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ መሆኑን ጠቅሶ፣ ጥንዶቹ በሥፍራው ከአንድ ዓመት በላይ መኖራቸውን ተናግሯል።

አርቲስት አንዱአለም እና ቀነኒ

ከክስተቱ በኋላ አስከሬኗ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ያኔት ወደተባለ ሆስፒታል መወሰዱን ገልጿል።

“እስከ ምሽት ድረስ ከቆየን በኋላ ፖሊስ መጥቶ አስከሬኑን ለምርመራ ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ወሰደው። ቀጥሎ ሱሉልታ ወደሚገኙት ቤተሰቦቿ ተወስዷል። የቀብር ሥነ-ሥርዓቷ በአዲስ አበባ ይፈፀማል።”

ሌሊሳ አርቲስት አንዱአለም በአሁኑ ወቅት ለምርመራ በፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ ማክሰኞ ዕለት ለቢቢሲ አረጋግጦ ነበር።

“አንዷለም ነው ወደ ሆስፒታል የወሰዳት። ፖሊስ መጥቶ ለምርመራ እሱን ይዞት ሄዷል። ከዚህ ውጪ በማኅበራዊ ሚድያ የሚሰራጩ ወሬዎች አሉባልታ ናቸው። አንዷለምን ወደ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዱት ቃሉን ለመቀበል ነው” ሲል አብራርቷል።

ማኔጀሩ በማኅበራዊ ሚድያ የሚሠራጩ የተለያዩ መረጃዎችን የተሳሳቱ ናቸው በማለት ወቅሰው ጉዳዩን እስኪጣራ ድረስ ሰዎች በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጠይቋል።

ጥንዶቹ “በቅርቡ ትዳር የመመሥረት ዕቅድ እንደነበራቸው” ማኔጀሩ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በኢንጂነሪንግ ድግሪ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀችው ቀነኒ በሞዴሊንግ እና በማስታወቂያ ሥራዎች በማኅበራዊ ሚድያ ዝናን አትርፋለች።

በሚቀጥለው ቅዳሜ ልደቷን ለማክበር በሚል ፎቶዎች እየተነሳች እንደነበር ቢቢሲ ከቅርብ ሰዎቿ ለመረዳት ችሏል።

ታዋቂው የኦሮምኛ ቋንቋ ድምጻዊው አንዷለማ ጎሳ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን፣ የቀነኒ ሞትን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ የሚያካሂደው ምርመራ ሲጠናቀቅ ውጤቱን ለሕዝብ እንሚያሳውቅ ገልጿል።