

በተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጸምበት የኮሬ ዞን ቦርካ ወረዳ ከፊል ገጽታ
ዜና ከምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች በኮሬ ዞን የሚፈጽሙት ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱ ተነገረ
ቀን: March 12, 2025
- በቀጠለው ጥቃት ሳቢያ የሁለት ቀበሌ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ መፈናቀላቸውን ዞኑ ገልጿል
በሃይማኖት ደስታ
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጽሙት ጥቃት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ የፌዴራል መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ሊያበጅለት እንደሚገባ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ታጣቂዎቹ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የሚፈጽሙት ጥቃት ትኩረት ሳይሰጠው ተባብሶ ቀጥሏል ሲሉ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
በዞኑ ጎርካ ወረዳ ጄሎ ቀበሌ የካቲት 29 እና 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የተነሱ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት፣ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ነዋሪነታቸው በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጄሎ ቀበሌ የነበሩት አርሶ አደር ሽኩር የሱፍና ወጣት ቡጥሳ ጉይባ በታጠቁ አካላት መገደላቸውን፣ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደር ሽኩር የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚኖርበት የጄሎ ቀበሌ ከብቶቹን ውኃ በማጠጣት ላይ ሳለ ከምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ዘልቀው የገቡ ታጣቂዎች ጥቃት እንደፈጸሙበት ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ወጣት ቡጥሳ በተመሳሳይ በታጣቂዎች ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ወደ ኬሌ መጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ተወስዶ ለተሻል ሕክምና ወደ አርባ ምንጭ ሪፈራል ሆስፒታል ሪፈር ቢጻፍለትም፣ መንገድ ላይ ሕይወቱ ማለፉን ነዋሪዎቹ አክለዋል። በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት የሚያስቆም ኃይል ባለመኖሩ የአካባቢው ሕዝብ ሥጋት ላይ ወድቋል ሲሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ጥቃት የፈጸመው አካል በደቡብ ክልል መንግሥት ደረጃ ይህ ነው የሚባል ዕርምጃ እየተወሰደበት እንደማይገኝ ጠቅሰዋል። ሆኖም የፌዴራል መንግሥት ለፖለቲካ ሽፋን ብቻ ሳይሆን፣ ትክክለኛና ሕጋዊ መሠረት ያለው ዕርምጃ ወስዶ፣ የሕዝቡን ጩኸት ሊያስቆም ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል።
እንዲሁም በአካባቢው ማኅበረሰብ፣ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታ ማስቻል እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል፡፡
ከምዕራብ ጉጂ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሚፈጸም ጥቃት ምክንያት፣ ከመኖሪያቸውና ከማሳቸው የተፈናቀሉ የጄሎና የዶርባዴ ቀበሌ ነዋሪዎች በአጎራባች ቀበሌዎች ውስጥ ባሉ ከላስቲክ በተሠሩ መጠለያዎች እንዳሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠቅሰዋል። የእርሻ ማሳቸው በታጣቂዎቹ የተቃጠለባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ እንጨት እየለቀሙና መንገድ ላይ አውጥተው እየሸጡ ዕለታዊ ጉርስ ለማግኘት እንዲገደዱ እንዳደረጋቸው አክለዋል። እንዲህም ሆኖ የታጣቂዎች ዒላማ በመሆን እየተገደሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ አልፎ ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የኮሬ ዞን ዋናው የንግድና የሕዝብ ትራንስፖርት መስመር የሆነው የኬሌ-ቶሬ-ጨለለቅቱ-ዲላ መንገድ በአግባቡ አገልግሎት እየሰጠ ስላልሆነ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ተግዳሮት ተፈጥሯል ሲሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር ስለጉዳዩ የጠየቃቸው የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ፣ አርሶ አደሮች ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ሲሉ በጠሯቸው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ዞኑ የተፈጠረውን ጥቃት የሚያጣራ መዋቅር አሰማርቶ ባደረገው ማጣራት፣ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሴት ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማት መረጋገጡን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዳንኤል ኩቴ በበኩላቸው፣ ‹‹ድንበር ላይ ባለ›› ሲሉ በገለጹት የጠላት ኃይል ድርጊቱ ተፈጽሟል ብለዋል።
ይህ የጠላት ኃይል በስም ይገለጽ ይሆን ብሎ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ዳንኤል፣ ‹‹ይህ የጠላት ኃይል ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ፣ የመግሥትን ዓላማ ለማዳከም የሚንቀሳቀስ ሽፍታ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል።
በኮሬና በምዕራብ ጉጂ ዞን አጎራባች አካባቢዎች ታጣቂው ኃይል በሰፊው እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት አቶ ታረቀኝ፣ ዘግናኝ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙ እንደሆነ አስረድተዋል።
የዞኑ ነዋሪዎች የእርሻ ማሳቸውን አረም በሚያርሙበት፣ ከብቶቻቸውን በሚጠብቁበትና ውኃ በሚፈልጉበት ወቅት ትንኮሳዎች እንደሚፈጸምባቸውና እንደሚገደሉም ተናግረዋል። ከዚሁ ባለፈ የእንስሳት ዘረፋ እንደሚፈጸምም አክለዋል። የጄሎና የዶርባዴ ቀበሌ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ መገደዳቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል። ሆኖም ነዋሪዎች ወደ አካባቢው ተመልሰው የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን እንዳይመሩ ታጣቂዎች ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ከዚህ አልፎ የብሔር ግጭት ተነስቶ ዕልቂት እንዲፈጠር የሚሰሩ ፀረ ሰላም ኃይሎች መኖራቸውን ያስረዱት ዋና አስተዳዳሪው፣ ይህን ድርጊት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ከኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን አመራሮች ጋር በጋራ እየተሠራና ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህም እዚያም ኔትወርክ ፈጥሮ ንብረት እየዘረፈ የሚያሸሽ ቡድን አለ የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ በጋራ በመሆን እያሰሱ ተጠያቂነት የማስፈን ሥራና ዕርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹ከኮሬ ዞን ጋር የጋራ ዕቅድ አውጥተን በሰላም ጉዳይ ላይ እየሠራን እንገኛለን፤›› ሲሉም አቶ ዳንኤል ተደምጠዋል፡፡
የሁለቱ አካባቢዎች ሕዝብ ተጋብቶና ተዋልዶ እንደሚኖር የጠቀሱት አቶ ታረቀኝ በበኩላቸው፣ ፀረ ሰላም ኃይል ባሉት ታጣቂ ላይ በጋራ ዕርምጃ መውሰድ ከተቻለ ማኅበረሰቡን ማወያየትና ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለስ ቀላል ነው ብለዋል። ሆኖም ከሐምሌ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እየደረሰ ባለው ጥቃት የደረሰው የሰው ሕይወት ሕልፈትና የሀብት ውድመት ይህ ነው ተብሎ በቀላሉ ሊገለጽ እንደማይችል ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ በክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል ተገምግሞ መቅረብ ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በሚነሱ ታጣቂዎች በየጊዜው ይፈጸማል ባሉት ግድያና የንብረት ውድመት ሳቢያ አስከፊ የሚባል የኑሮ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን፣ የኮሬ ዞን ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል፡፡