

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈንታው ከበደ
ዜና የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ ሦስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ
ቀን: March 12, 2025
በሃይማኖት ደስታ
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈንታው ከበደ፣ የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር አዲስ ዘመን ፍሰሐና ይጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ ሾፌር አቶ ከበደ እንድሪስ፣ ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ገለጸ::
ስለተፈጸመው ጥቃት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ መኮንን በሰጡት ምላሽ፣ በጥቃቱ ሁለት የወረዳው ከፍተኛ ኃላፊዎችና ሾፌሩ መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
የሦስቱ ሰዎች ሥርዓተ ቀብርም በወረዳው ቢስቲማ ከተማ ማክሰኞ ዕለት መፈጸሙን አቶ ዓሊ ገልጸዋል።
የወረባቦ ወረዳ አስተዳደር መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ባወጣው የሐዘን መግለጫ፣ ድርጊቱን የፈጸሙት ‹‹የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች›› ናቸው ብሏል።
የዞኑ አስተዳዳሪ በበኩላቸው፣ ‹‹ድርጊቱ እንዴት ተፈጸመ? ማንስ ፈጸመው?›› የሚለው እስካሁን እንዳልታወቀ በመጥቀስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማወቅ በዞን ደረጃ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ ቴክኒካዊ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና የሚደረስበትን ድምዳሜ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
በደረሰው ጥቃት ሐዘኑን የገለጸው የወረባቦ ወረዳ አስተዳደር፣ ‹‹እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በሐሳብ ትግል ማሽነፍ ያልቻሉትን በጠመንጃ ለማስፈጸም፣ ሕዝብን ለማገልገል ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩና አሁንም ሕዝብን ለማገልገል በጉዞ ላይ ያሉ የወረዳ አመራሮችና ባለሙያ መንገድ ላይ እየጠበቁ ጥቃት በማድረስና በመግደል ዓላማቸውን ለማሳካት እየጣሩ ይገኛሉ፤›› ብሏል፡፡
የወረዳ አመራሮችና ባለሙያ የተገደሉበትን ድርጊት ክስተት ነው ሲሉ የገለጹት አቶ ዓሊ፣ ከአንዳንድ የዞን አጎራባች አካባቢዎች አልፎ አልፎ የፈጠረው ከተፈጠሩ ችግሮች ውጪ አብዛኛው የደቡብ ወሎ ዞን አካባቢ ሰላም ነው ሲሉ ተናግረዋል። የአካባቢው ኅብረተሰብ፣ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በጋራ በመሆን የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ እየሠሩ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።