በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኤመስበርገር (መሀል) ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 መግለጫ ሲሰጡ

ዜና የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ በጣለው የቪዛ ገደብ በግንቦት ወር እንደሚመከርበት አስታወቀ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: March 12, 2025

የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የቪዛ ገደብ በተመለከተ በመጪው ግንቦት 2017 ዓ.ም. እንደሚመክርበት ተገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ የኅብረቱ አምባሳደርና የአባል አገሮች ዲፕሎማቶች በተገኙበት ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያና አውሮፓ ኅብረት ግንኙነት የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ 

የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኤመስበርገር  በሰጡት መግለጫ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሻክሮ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነት ገንቢ ውይይት በማድረግ ወደ መስመር ለማስገባት መተማመን ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ወደ ኅብረቱ አገሮች ከገቡ በኋላ የጥገኝነት ጥያቄዎቻቸው ውደቅ ሲደረግ ወደ አገራቸው መመለስ የነበረባቸው ኢትዮጵያውን ስደተኞችን ለመቀበል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት አላሳየም በሚል በኢትዮጵያውያን ላይ የቪዛ ገደብ የጣለው እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 2024 ጀምሮ ነበር፡፡

 በገደቡ መሠረት የዲፕሎማትና የአገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቪዛ በክፍያ እንዲሰጣቸው፣ ቪዛ ለማግኘት የሚጠብቁት ጊዜ ከ15 የሥራ ቀናት ወደ 45 የሥራ ቀናት ከፍ እንዲል ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡

ጉዳዩን በትኩረት እየሠራንበትና በቅርበት የምንከተለው ነው ያሉት አምባሳደሯ፣ ‹‹በአጀንዳችን የተቀመጠ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በአውሮፓ ካሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ትልቅ ለውጥ አሳይቷል፤›› ብለዋል፡፡ ይህን በተመለከተ በመጪው ግንቦት ወር ኅብረቱ መክሮ ውሳኔ ያሳልፋል ብለዋል፡፡

የአሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያደርግ የነበረውን የበጀትና በሰሜን ኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንደገና መጀመርን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚደረገውን የበጀት ድጋፍ በተመለከተ ምንም እንኳ አሁን መናገር ባይቻልም፣ ከኅብረቱ በኩል ፍላጎት መኖሩንና እንዴት መቀጠል እንደሚቻል ውይይት እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት መቆም ያለበት መሆኑን በተለያዩ መንገዶች እየገለጽን ነው፤›› ያሉት አምባሳደሯ፣ ግጭት ተገቢ ባለመሆኑ ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ድርድር ለማምጣት የሚቻልበት መንገድ እንዲገኝ ይሠራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ባለው የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ያሳስበኛል የሚል መግለጫ ያወጣው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ይህን መግለጫ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደሯ፣ ‹‹የሚዲያ ነፃነትና የተሻለ ምኅዳር እንዲፈጠርና በአገሪቱ የተለያዩ አመለካከቶች እንዲደመጡ በማድረግ የሰላም መልህቅ እንድትሆን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ አሜሪካ ስትሰጥ የነበረው ዕርዳታ በመቋረጡ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የአውሮፓ ኅብረት ብቻውን ሊሸፍነው የማይቻለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ወደ አንድ በማምጣት ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡