

ዜና አቶ ጌታቸው ረዳ በሦስት የሠራዊት አመራሮች ላይ ያሳለፉት ዕግድ ከምክትላቸውና ከሕወሓት ክንፍ…
ቀን: March 12, 2025
‹‹የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ያልሾመውን ማውረድ አይችልም››
ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ
- የሌተና ጄኔራል ታደሰ ምላሽ ‹‹የፀጥታ ኃይሉ ለአንድ ቡድን የቆመ ወታደራዊ ክንፍ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው››
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሦስት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችን ከሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ መታገዳቸውን ባሳወቁ በማግሥቱ፣ ምክትላቸው ከሆኑት የክልሉ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደና በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከሚመራው የሕወሓት ቡድን ተቃውሞ ገጠመው።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ሦስት የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችን፣ ከመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነት የታገዱ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር።
አቶ ጌታቸው ከኃላፊነት ያገዷቸው የሠራዊቱ አመራሮች ሜጀር ጄኔራል ዮሐንስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ሜጀር ጄኔራል መዓሾ በየነና ብርጋዴር ጄኔራል ምግበይ ኃይለ ናቸው፡፡
አቶ ጌታቸው ለሦስቱ የሠራዊት አመራሮች በጻፉት የዕግድ ደብዳቤ ላይ የታገዱበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ ‹‹ከክልሉ መንግሥት ዕውቅናና ውሳኔ ውጪ የክልሉን ሕዝብ ወደ ችግር፣ ወጣቱን ወደ አመፅና የፀጥታ ኃይሉን ወደ እርስ በርስ ግጭት የሚያስገቡ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው በጻፉት ደብዳቤ ሦስቱ ወታደራዊ አመራሮች ክልሉ አሁን የሚገኝበት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሕጋዊ መንገድ ዕልባት እስከሚያገኝ ድረስ ታግደው እንደሚቆዩ የሚጠቅስ ሲሆን፣ የዕግድ ደብዳቤውንም ለምክትላቸው ማለትም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሰላምና ፀጥታ ካቢኔ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ታደሰ እንዲያውቁት ግልባጭ ማድረጋቸውን ሪፖርተር ከደብዳቤው ለመረዳት ችሏል፡፡
በሌተና ጄኔራል ታደሰ የሚመራው የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ማለዳ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የዕግድ ውሳኔው ተቋማዊ አሠራርንም ሆነ ሕግን ያልተከተለ ነው፤›› በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ በመግለጫው መግቢያ ላይ፣ ‹‹የወንጀለኞች ጠበቃ መሆን ይብቃ፤›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም ለወንጀለኞች ከለላ ለመሆን የሚደረገው ጥረት መቆም አለበት፤›› በማለትም አሳስቧል።
የዕግድ ዕርምጃው፣ ‹‹በግለሰብ ደረጃ ወይም ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ የተወሰደ ነው፤›› በማለት ወቀሳ ያቀረበው ቢሮው፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ያልሾመውን ማውረድ አይችልም፡፡ አመራሮቹ እንዲታገዱ የተደረገውም በወንጀለኞች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ስለተጀመረ ነው፤›› ሲል ዕግዱን ውድቅ አድርጓል፡፡ የተጀመረው ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ተግባርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓትም በተመሳሳይ፣ ‹‹ሠራዊቱ በከሃዲው ቡድን ሴራ አይፈርስም፤›› በማለት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው የተላለፈውን የዕግድ ውሳኔ ተቃውሟል።
በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓት መጋቢት 1 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ግለሰቦች ፀረ ሕዝብ እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለውበታል፤›› በማለት ከሷል።
በማከልም በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚመራው ቡድን የትግራይ ሠራዊትን ለማፍረስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ወደ አደገኛ ደረጃ መሸጋገሩን ገልጿል፡፡
በአቶ ጌታቸው የተላለፈው የዕግድ ውሳኔ ሕገወጥ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሉ ኃላፊነቱን መወጣቱን እንዲቀጥልና የሕዝቡን ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓትና የፀጥታ ኃይሉን መግለጫ ተከትሎ ማክሰኞ ዕለት በድጋሚ ምላሽ የሰጠው በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፀጥታ ኃይሉ ሦስት የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች መታገዳቸውን መቃወሙ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው በማለት ኮንኗል፡፡
በቢሮው ስም የወጣውና ተቋውሞን የሚገልጸው ምላሽ፣ ‹‹የፀጥታ ኃይሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ሳይሆን ለአንድ ቡድን የቆመ ወታደራዊ ክንፍ መሆኑ በግልጽ ያሳየ ነው፤›› በማለት የወቀሰው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ይህ ድርጊት ውጥረት ውስጥ የገባውን የትግራይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያባብስ እንደሆነም አመልክቷል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ ኃላፊ በሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ በማዕድን ዝውውር፣ በወርቅና ብረታ ብረት ዝርፊያ፣ በኮንትሮባንድ ንግድና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ውስጥ የተሳተፉ አካላት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በክልሉ መንግሥት ትዕዛዝ ቢተላለፍላቸውም፣ ትዕዛዙን ወደ ጎን በማለት በሕግ ማስከበር ስም መንግሥታዊ መዋቅሮችን የማፍረስ እንቅስቃሴ ሲደረግ ዝምታን መምረጣቸው፣ ‹‹ውግንናቸው ለማን እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፤›› ነው በማለትም ከሷል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር በሚል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ‹‹ኋላቀር›› ሲል በጠራው በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራውን ቡድን ተልዕኮ ለማስፈጸም ያለመ እንደሆነ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
የክልሉን ፕሬዚዳንት እንደማይቀበል ከመግለጽ ባለፈ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማፍረስ መወሰኑን በግልጽ አሳይቷል ሲልም ነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የገለጸው፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የሰላምና ፀጥታ ካቢኔ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ በክልሉ ሠራዊት ስም ጉባዔ እያካሄዱ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበው ነበር፡፡
‹‹ሥልጣን ለማግኘት በሕገወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ነው›› በሚል የተወቀሰውን በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓት ድርጊቱን እንዲያቆም ማሳሰቢያ መሰጠቱን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ የሠራዊት አመራሮችም ሆኑ ሌሎች አካላት ጥያቄዎችን የሚያቀርቡበትና የሚያስተናግዱበት ሕጋዊ አግባብ እያለ በወረዳዎችና በቀበሌዎች ሠራዊት በማሰማራት ሥርዓት ለማፍረስ የሚደረግ አካሄድ አግባብነት እንዳልሆነ በደብዳቤው ጠቅሰዋል፡፡
የሠራዊቱ የበላይ አዛዥ መሆናቸውን በደብዳቤው ያሰፈሩት አቶ ጌታቸው፣ ይህ ደብዳቤ ከተላከበት ዕለት አንስቶ በየትኛውም ግንባር ምንም ዓይነት የሠራዊት እንቅስቃሴ እንዳይካሄድና ትዕዛዙን በማይቀበሉ የሠራዊት አመራሮች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡