ዜና
ኢዜማ ገዥው ፓርቲ ዜጎች በውድም ሆነ በግድ የማጠናከሪያ ገንዘብ እንዲያዋጡለት እያደረገ ነው…

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: March 12, 2025

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚሄዱ ዜጎችን የፓርቲ ማጠናከሪያ እንዲያዋጡ እያደረገ ነው ሲል አስታወቀ፡፡

ኢዜማ ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ብልፅግና ባለፈው ጥር ወር ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች አንዱ በሆነው ‹‹ፓርቲውን ማጠናከር›› የሚል ውሳኔ መሠረት በማድረግ፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ‹‹በውድም ሆነ በግድ›› የፓርቲ ማጠናከሪያ ገንዘብ እንዲያዋጡ እየተደረገ እንደሆነ ካሰባሰብኩት ማስረጃዎች ማወቅ ችያለሁ ብሏል።

‹‹ከፓርቲ አባላት ውጪ ያሉ ዜጎች ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ለየትኛውም ድርጅት በፈቃደኝነት የፈለጉትን ድጋፍ ማድረግ መብታቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እንዲሁም ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ዜጎች ሐሳባችንን ይወክሉልናል ለሚሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ ምንም ፍርኃት መደገፍ እንዳለባቸውም እምነታችን ነው፤›› ያለው ኢዜማ፣ ‹‹ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱባቸው የመንግሥታዊ ተቋማት ይህን ድርጊት መፈጸም በፍፁም ሕገወጥ ተግባር ነው፤›› በማለት ማስረጃ አለኝ ያለውን የብልፅግና ድርጊት ተቃውሟል።

ኢዜማ ብልፅግና ስለአባላቱ ብዛት በአደባባይ ይፋ አድርጎታል ያለውን አኃዝ በመጥቀስ፣ በዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው ሕገወጥ ድርጊት ከመዋቅሩ ጋር በማያያዝም ተችቷል።

‹‹በመሠረቱ ብልፅግና ፓርቲ 17 ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ ሲል በአደባባይ ቢሰማም፣ ለፓርቲው ማጠናከሪያ አሉኝ ከሚላቸው አባላት ማሰባሰብ ሲገባው አባል ካልሆኑ ዜጎች ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ጋር አያይዞ መዋጮ ማሰባሰብ ምንም ዓይነት የሕግም ሆነ የሞራል መሠረት የለውም፤›› በማለት ኢዜማ ተችቷል።

‹‹ብልፅግና ይህንን ዓይነት አሳፋሪ ተግባር የሚፈጽሙ አባላቱንም ቆጥሮ ከሆነ ‹በአባላት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ ሆኛለሁ› የሚለው መዋቅሩን በድጋሚ ሊያጤነው ይገባል፤›› ሲል ኢዜማ ገልጿል፡፡

ኢዜማ ከዚህም ባሻገር የብልፅግና ከፍተኛ አመራር አባላትን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ካላቸው ሚናና ጥቅማ ጥቅም ጋር በማያያዝም ወቀሳ አቅርቧል።

‹‹ዋና ዋና የሚባሉት የፓርቲው አባላት በመንግሥት መዋቅር በሹመት፣ ግፋ ሲል ደግሞ የዴሞክራሲ ተቋማት ማስተባበሪያ በሚል የሙሉ ጊዜ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ሥራ የሚሠሩት ሁሉ ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ግብር ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚተዳደሩ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፤›› ብሏል።

ከዚህም ጋር አያይዞ አሁን ብልፅግና አባል ያልሆኑ ዜጎችን ጭምር ለአገልግሎት ወደ ማንኛውም መንግሥታዊ ተቋማት ሲሄዱ የፓርቲ መዋጮ እየተሰበሰበ ነው በማለት የወቀሰ ሲሆን ድርጊቱንም፣ ‹‹የመንግሥት መዋቅርን ለአንድ ፓርቲ አገልግሎት መጠቀም መሆኑን አለመረዳት ሳይሆን፣ የማናለብኝነት ስሜቱ የት እንደ ደረሰ እንደ ማሳያ የምንወስደው ነው፤›› ብሏል፡፡

ብልፅግና በኢትዮጵያ ‹የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ይኑር› የሚል ቁርጠኛ አቋም አለኝ ቢልም፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ውስጥ መገኘቱ ዓይን ያወጣ አድልኦ እየሠራ መሆኑ ሊያወቀው ይገባል፤›› ሲልም ገልጿል፡፡

ኢዜማ ተፈጥሯል ያለውን ሕገወጥ ድርጊት በተመለከተም፣ ‹‹ገዥው ፓርቲ አሁን አለኝ ከሚለው ግዝፈት በላይ ለመለጠጥ የሚሄድበት መንገድ ቅጥ ያጣ ራስ ወዳድነትና አልጠግብ ባይነትን የሚያሳይ እንደሆነ ማስገንዘብ እንወዳለን፤›› ብሏል፡፡

አገሪቱ በዚህ መንገድ የምትጓዝ ከሆነ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ ‹‹ዘበት ይሆናል፤›› በማለት ኢዜማ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ይፋ ያደረገው፣ ‹‹የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር›› ረቂቅ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የገንዘብ ምንጮች የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አስፍሯል።

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 118(4) ላይ እንደተገለጸው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የገንዘብ ምንጩ ከአባላቱ የሚሰበሰብ የአባልነት መዋጮ ከሆነ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አባል የሚሰበሰብ የአባልነት መዋጮ መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ ከሠራተኛው ደመወዝ በመቁረጥ አባል ወደ ሆነበት የፖለቲካ ፓርቲ የባንክ ሒሳብ ማስገባት እንደማይችል ተገልጿል።

ረቂቅ አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲ የገንዘብ ምንጭን በተመለከተ የተዘረዘሩ ጉዳዮችን በሚመለከት ምርጫ ቦርድ ዝርዝር መመርያ እንደሚያወጣ የተገለጸ ሲሆን፣ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል ዕጩ ከየትኞቹ አካላት የሚቀርብለትን ስጦታ ወይም ዕርዳታ መቀበል እንደማይችል በተከታዩ አንቀጽ በዝርዝር አስቀምጧል።

ከእነዚህም መካከል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመንግሥት ከሆኑ የልማት ድርጅቶች፣ እንዲሁም ካልታወቀ ምንጭ የሚቀርብ ስጦታን ወይም ዕርዳታን መቀበል እንደማይችል የሚገልጹ ድንጋጌዎች ይገኙበታል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማንኛውም ፓርቲ ወይም የግል ዕጩ በረቂቅ አዋጁ በተጠቀሰው መሠረት የተከለከለ ስጦታ ወይም ዕርዳታ በማንኛውም መንገድ የተቀበለ እንደሆነ፣ ስጦታውን ወይም ዕርዳታውን በተቀበለ በ21 ቀናት ውስጥ ከተያያዥ መረጃዎች ጋር ለቦርዱ ገቢ ማድረግ እንዳለበትም ተደንግጓል።

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል ዕጩ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ከተፈቀደለት ውጪ ገንዘብ ወይም ንብረት በስጦታ፣ በዳረጎት፣ በውርስ፣ በንግድና ኢንዱስትሪ ሥራ ወይም በማናቸውም መንገድ ተቀብሎ ቢገኝ ላገኘው የገዘብ ጥቅም ቦርዱ እንደሚቀጣው፣ በተጨማሪም አግባብ ባለው ሕግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቅሷል።

ኢዜማ በማክሰኞ ዕለት መግለጫው፣ ‹‹በፍጹም ሕገወጥ›› ሲል የጠቀሰውን ‹‹የብልፅግና በመንግሥት ተቋማት መዋጮ ማሰባሰብ›› በተመለከተ መግለጫው ማጠቃለያም ጥሪ አቅርቧል።

‹‹ዜጎች በኑሮ ውድነት፣ በሙስናና በመልካም አስተደዳደር ዕጦት መንገላታታቸው ሳያንስ ይህን ዓይነት በጠራራ ፀሐይ በፓርቲ መዋጮ ስም የሚፈጸም ዝርፊያ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም፣ ዜጎችም በግልጽ እምቢ እንዲሉ ጥሪ እናስተላልፋለን፤›› ብሏል።

መንግሥት በማንኛውም ደረጃና ተቋም ተፈጽሟል የተባለውን ድርጊት እንዳይፈጸም አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግና ሥርዓት እንዲያስከብር የጠየቀው ኢዜማ፣ ‹‹ድርጊቱን የሚፈጽሙ›› ያላቸው ማንነታቸው ያልተገለጸ የብልፅግና ፓርቲ አባላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲል አሳስቧል።

‹‹ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህን ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ በማጣራት፣ በመንግሥት ተቋማት ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚሰበሰብ የብልፅግና ፓርቲ ማጠናከሪያ ገንዘብ ማሰባሰብ በአስቸኳይ እንዲያስቆምና በፓርቲው ላይ የወሰደውን የዕርምት ዕርምጃ ለሕዝብ በግልጽ እንዲያሳውቅ፤›› ሲል ኢዜማ በመግለጫው ጠይቋል።