
March 12, 2025

የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደ ሰንበት (ዶ/ር)
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በተለያዩ መንገዶች ለአገሮች ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ በማቋረጡ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሆቴሎች ይካሄዱ የነበሩ ሥልጠናዎች፣ ስብሰባዎችና አጫጭር ዓውደ ጥናቶች መቀነሳቸውን የሆቴል ዘርፍ ተዋናዮች ተናገሩ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2024 ብቻ ወደ 38 ቢሊዮን ዶላር በጀት በመላው ዓለም ወጪ ማድረጉ የሚነገርለት ዩኤስኤአይዲ ለኢትዮጵያ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገ ግዙፍ የተራድኦ ድርጅት መሆኑ ይነገርለታል፡፡
በከተማው ውስጥ ከሚገኙ ሆቴሎች ይህ ድጋፍ በመቋረጡ የገጠማቸውን ችግር በተመለከለተ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የማርኬቲንግ ባለሙያ፣ እ.ኤ.አ. በመጋቢትና በሚያዝያ 2025 ብቻ ለሆቴላቸው ይገባ የነበረ 25,000 ዶላር በፕሮግራሙ መታጠፍ ምክንያት መሰረዙን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የማይገኘውን ገንዘብ ለማካካስ ከዚህ ቀደም ከነበረው የሆቴሉ ዋጋ ባነሰ ገንዘብ የሚመጡ ፕሮግራሞችንና እንግዶችን የመቀበል፣ እንዲሁም በማርኬቲንግ ባለሙያዎች አማካይነት ወደ ድርጅቶችና ተቋማት በመሄድ የማካካሻ እንግዳና የመሳብ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በካዛንቺስ አካባቢ የሚገኝ አንድ የሆቴል አዳራሽ ባለሙያ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ የሆቴሉ አዳራሽ በሳምንት ሦስቴ አንዳንዴም ለአምስት ቀናት በሙሉ ተይዘው የነበረበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን የሚደረጉ ስብሰባዎች ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
አንድ የሆቴልና ማርኬቲንግ ባለሙያ ከዚህ ቀደም በሚደረጉ ስብሰባዎች ምንም እንኳ ሁሉም ስብሰባዎች በቀጥታ በዩኤስኤአይዲ የሚደገፉ ባይሆኑም፣ በተዘዋዋሪ በራሱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃው እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
ሪፖርተር በአዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ሆቴሎችን ለመጠየቅ ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ድጋፉ በመቋረጡ ብዙ ስምምነቶች መሰረዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደ ሰንበት (ዶ/ር)፣ በዩኤስኤአይዲ በሚደገፉ ፕሮግራሞች በተለይ የተለያዩ ሥልጠናዎች፣ ኮንፈረንሶችና ዓውደ ጥናቶች ሲካሄዱ እንግዶችም የመኝታ ክፍሎች ይይዙ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
ከሆቴሎች ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች በመሰረዛቸውና ፕሮግራሞች በመታጠፋቸው፣ እንዲሁም እንግዶች በመቅረታቸው የደረሰውን ጫና በተመለከተ ፌደሬሽኑ በቀጣይ ግምገማ እንደሚያደርገበት ገልጸው፣ ሆቴሎች አማራጭ ስትራቴጂ እንዲቀይሱ አሳስበዋል፡፡
የረድኤት ድርጅቶች ሠራተኞች በተለያዩ ጊዜያት ለእረፍትና ለሥራ ወደ ሆቴሎች ለመምጣት ዕቅድ ይዘው የነበሩ ቢሆንም ዓመታዊ ስምምነቶችና ወቅታዊ ግዥዎች ተሰርዘዋል፡፡ ያሉት ፍትሕ (ዶ/ር)፣ በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ ላይ ትልቅ ጫና መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
‹‹የሆቴሎች ገቢም እንደሚቀንስ እንጠብቃለን፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ በዩኤስኤአይዲ ይደገፉ የነበሩ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት የነበራቸውን ውል ሙሉ በሙሉ በማቋረጣቸው ወደፊት ሊደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች መታጠፋቸውን ከሆቴሎች መስማታቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህ ክስተት ዘርፉ በአገር ውስጥ ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ማጠናከር፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ የገበያ አቅም መፍጠር እንደሚስፈልግ የሚያሳይ ከኮቪድ-19 ክስተት ቀጥሎ የመጣ ትልቅ ክፍተት ፈጣሪ ነው ብለዋል፡፡
