

በጦርነቱ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የፈለሱ ሱዳናውያን ስደተኞች
ዜና በየቀኑ 100 ያህል ሱዳናውያን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየገቡ መሆናቸው ተሰማ
ቀን: March 12, 2025
ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የሱዳን ጦርነት ምክንያት በየቀኑ 100 ያህል ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየገቡ መሆናቸውን፣ የአሶሳ ከተማ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የአሶሳ ከተማ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያሲን አሸናፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሱዳን ጦርነት ከመጀመሩ 20 ሺሕ ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ክልሉ ገብተው ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት በጦርነቱ ምክንያት ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ድንበር አቋርጠው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቡ ስደተኞች ቁጥር 108 ሺሕ መድረሱን ጠቅሰው፣ ለስደተኞችም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የምግብ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከሱዳን በየቀኑ ከ40 እስከ 100 የሚጠጉ ሱዳናውያን ስደተኞች ወደ ክልሉ እየገቡ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ክልሉ ከ35 ሺሕ በላይ የሚይዙ አራት የስደተኞች ካምፕ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የሱዳንም ሆኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ድጋፍ የሚያገኙት ከ11 ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሆነ፣ ነገር ግን በቅርቡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በመላው ዓለም ሲሰጥ ቆየውን ተራድኦ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ካቋረጠ ስደተኞች ምንም ዓይነትን አገልግሎት እንዳያገኙ እንደሚያደርጋቸው ሥጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
በክልሉ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች በየቀኑ እየቀነሱ መሆናቸውን፣ ለአብነትም በ2016 ዓ.ም. ለስድስት ወራት ያህል ስደተኞቹ ምንም ዓይነት አገልግሎት ሳያገኙ መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሠረት በእነዚህ ወራት ውስጥ የክልሉ ነዋሪዎች ለስደተኞች ያላቸውን ነገር በማካፈል አብረው እንዲጠቀሙ የተደረገበት አሠራር ተፈጥሯል ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ክልሉ ትልቁን ድርሻ መወጣት መቻሉን አክለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት በክልሉ ለሚገኙ የሱዳንም ሆነ የደቡብ ስደተኞች የበቆሎ፣ የስንዴና የሌሎች ምርቶችን ለአንድ ሰው ይሰጥ የነበረው አሥር ኪሎ ግራም እንደነበር፣ አሁን ላይ ግን ለአንድ ሰው አምስት ኪሎ ግራም እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ ክልሎች ለራሳቸው ፍጆታና ዓላማ ብለው የስደተኞችን ቁጥር እያጋነኑ በማስቸገራቸው፣ በክልሉ ምን ያህል ስደተኞች እንዳሉትና የዕርዳታ ድጋፍ ምን መደረግ እንዳለበት መመለስም ማወቅም አልተቻለም ያሉት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዓለማየሁ ሞንጫቱ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በግዳጅ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን በስደተኞች ላይ የሚያጋጥሙ ሥር የሰደዱ ችግሮችና የገንዘብ እጥረት ለማሟላት ከለጋሾች ጋር በመሆን እንደሚረዳ ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በ2025፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች ለሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ከ300 በላይ መጠለያዎችን መሥራቱን አስታውቋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የውኃ አቅርቦትና መንገድ መሠራታቸውን ገልጿል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ከ27,000 በላይ ስደተኞች በብሔራዊ የፋይን ፕሮግራም ዲጂታል መታወቂያ ያገኙ ሲሆን፣ 700 ስደተኞች ደግሞ በመልሶ ሠፈራ ፕሮግራም ወይም በግል በተገኘ ስፖንሰርሺፕ ከኢትዮጵያ ወጥተዋል፡፡
ድርጅቱ በፈንድ እጥረት ምክንያት ችግሮችን ቀድሞ ከመከላከል ይልቅ ሕይወት አድን ወደ ሆኑ ሥራዎች ትኩረት እንደሚያደርግ ማስገደዱን፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና መሠረተ ልማት ማርጀታቸውን፣ የውኃ አቅርቦት በግለሰብ በቀን 14 ሊትር ላይ መቆሙን፣ የአካባቢ ንፅህና ሽፋን መሆን ከሚጠበቅት 85 በመቶ በታች 33 በመቶ ላይ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡
የአሜሪካ ዕርዳታ መቋረጡ የሕክምና ቅብብሎሽ፣ ማኅረበሰብ አቀፍ የሥነ ተዋልዶ ጤና ፕሮግራሞች፣ የአዕምሮ ጤናና የሥነ ልቦና ድጋፍ፣ የሠራተኞች ሥልጠና፣ ወሳኝ የሆኑ የጤና ግብዓቶች ግዥን ጨምሮ ወሳኝ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡
