

የአማራ ክልል ምክር ቤት
ዜና የአማራ ክልል የማዘጋጃ ቤታዊ ግብርና የአገልግሎት ክፍያዎችን ለነዋሪዎች መሰረዝ የሚያስችለው ረቂቅ ደንብ…
ቀን: March 12, 2025
የአማራ ክልል ምክር ቤት ነዋሪዎች የማዘጋጃ ቤታዊ ግብርና የአገልግሎት ክፍያ ለመፈጸም የማይችሉበት ሁኔታ መኖሩ በጥናት ሲረጋገጥ፣ ክፍያውን በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ መሰረዝ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ አወጣ።
‹‹የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የከተሞች አገልግሎት ገቢ አሰባሰብና ታሪፍ ማሻሻያ፣ የክልል መስተዳድር ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 220/2017 ዓ.ም.›› የሚል ስያሜ የተሰጠው 28 አንቀጾችን የያዘ ረቂቅ ደንብ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የወጣውን የክልሉን ከተማ አስተዳደሮችና ማዘጋጃ ቤቶች የአገልግሎት ገቢ ታሪፍ የተመለከተ ደንብ ለመተካት የቀረበ ነው።
ረቂቅ ደንቡ ድንጋጌውን ማሻሻል ያስፈለገባቸውን አራት ዋና ዋና ጉዳዮች የጠቀሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ‹‹ከተሞች በገቢ ራሳቸውን ባለመቻላቸው ምክንያት በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር ለመወጣት የሚያስችላቸውን ገቢ እያገኙ ባለመሆናቸው፣ እንዲሁም የአገልግሎት ገቢና የገቢ አርዕስት ታሪፍ ማሻሻያ ሲደረግም የከተሞችን ገቢ ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ ፍትሐዊ የሆነ የገቢ አሰባሰብ እንዲኖር ለማድረግ በመሆኑ›› የሚሉ ማብራሪያዎችን ይዟል፡፡
በተጨማሪም አሁን በክልሉ በሥራ ላይ ያለው ደንብ ቁጥር 135/2008 ጊዜው የደረሰበትን ወቅታዊ የከተሞች ልማትን ለማስፈን ያልቻለ በመሆኑ፣ ውስን በሆኑ የአገልግሎት ገቢና የገቢ አርዕስት ላይ ተመሥርቶ የሚሰበሰበውን የገቢ መሠረት ማስፋት በማስፈለጉ ማሻሻያው ተዘጋጅቶ መቅረቡም ተጠቅሷል።
በረቂቅ ደንቡ ከቀረቡ ድንጋጌዎች መካከል በአንቀጽ 23 ላይ ክፍያ የሚቋረጥበት ሁኔታ ተገልጿል።
በዚህ ድንጋጌ በረቂቅ ደንቡ መሠረት የተወሰነው የማዘጋጃ ቤታዊ ግብርና የአገልግሎት ክፍያ በአስገዳጅ ሁኔታ (ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋ፣ እንዲሁም ወረርሽኝ ሲከሰት) መከፈል የማይችልበት ሁኔታ መኖሩን በጥናት ሲረጋገጥ፣ የሚመለከተው ከተማ ወይም ወረዳ አመራር ኮሚቴ ክፍያውን በከፊልም ሆነ በሙሉ ሊሰርዝ እንደሚችልና የዚህም ዝርዝር አፈጻጸም በመመርያ እንደሚወሰን ያስረዳል፡፡
በረቂቅ ደንቡ ክፍል ሦስት ስለከተሞች ገቢ ታሪፍ አወሳሰን፣ አሰባሰብና አጠቃቀምን በተመለከተ ከተዘረዘሩት ድንጋጌዎች መካከል የታሪፍ ምጣኔ አጣጣልን በተመለከተ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ዓይነቶች የታሪፍ ምጣኔ የሚጣለው በቅድሚያ በገቢ ምንጮቹ ላይ ዝርዝር ጥናት ተካሂዶ የገቢው ቀጣይነትና ተገቢነት ሲታመን ብቻ መሆኑን ይገልጻል።
በተጨማሪም የክፍያ ታሪፍ ምጣኔያቸው እንደ የከተሞቹን ደረጃ፣ የወጪ ፍላጎትና የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም በማገናዘብ በቁጥር ወይም በመቶኛ ሊወሰን እንደሚችልና የታሪፍ ምጣኔ ሲዘጋጅ በግብሩ ዓይነት፣ በአገልግሎቱ ዓይነትና መጠን ተለይቶ በገበያ ዋጋ ወይም በሌላ ሥልት እንደሚጣልም ተደንግጓል።
የክልሉ ከተሞች ተነፃፃሪ የሆነ የታሪፍ ምጣኔ አዘገጃጀት ሥርዓት እንዲከተሉ በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ የክልል ከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ከገቢዎች ቢሮ ጋር በመቀናጀት፣ በክልሉ የሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች የታሪፍ ምጣኔ ወይም ተመን አዘገጃጀትና አፈጻጸም ጥናት በማከናወን የተጠቃለለ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀት እንደሚኖርበትና አዲስ የታሪፍ ምጣኔ ሲዘጋጅም ሆነ ነባሩ ሲሻሻል የከተማው ነዋሪ ኅብረተሰብ በሒደቱ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበትም ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል ማንኛውም የከተማ አስተዳደር፣ ማዘጋጃ ቤት ወይም ታዳጊ ከተማ በከተማው ክልል በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራን ወይም የሙያ አገልግሎት የሚሰጥን ማንኛውንም ሰው በተመለከተ ወቅታዊ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመያዝ ለደረጃው የሚመጥን ዓመታዊ የንግድ ሥራና የሙያ አገልግሎት ክፍያ እንደሚወስንና እንደሚሰበስብ፣ ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ ደንብ አንቀጽ ዘጠኝ ተጠቅሷል።
የንግድና የሙያ አገልግሎት ክፍያን ለመወሰንም ዓመታዊ ሽያጭ 60 በመቶ፣ የንግድ ዓይነት ወይም ዘርፍ 20 በመቶና የቦታ ደረጃ 20 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው እንደሚደረግ፣ ዓመታዊ የንግድ ሥራና የሙያ አገልግሎት ክፍያ ገቢ የሚሰበሰበውም የበጀት ዘመኑ ከተጠናቀቀ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡
በአገልግሎት ክፍያዎች አወሳሰን ላይ ስለሚነሳ ቅሬታ አቀራረብና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ በሠፈሩ ድንጋጌዎች መሠረት እያንዳንዱ ከተማ በመመዘኛ መሥፈርቱ ወቅታዊ መረጃዎችን በመያዝ፣ የአገልግሎት ክፍያ ከፋዮችን ደረጃ በሚያወጣበት ጊዜ ወይም በማናቸውም የአገልግሎት ክፍያ አወሳሰን ሒደት ቅሬታ ወይም አቤቱታ የቀረበ እንደሆነ፣ ይህንኑ የሚመረምርና አጣርቶ ውሳኔ የሚሰጥ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ እንደሚያቋቁም ረቂቅ ደንቡ ያስረዳል።
ይሁንና ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው የሚገኝ የገቢዎች ቢሮ በማዘጋጃ ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ በቀረበ ጊዜ፣ የቀረበውን ቅሬታ ወይም አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችልም ተገልጿል።
በአገልግሎት ክፍያ ውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘ ማንኛውም የአገልግሎት ክፍያ ከፋይ ውሳኔው በጽሑፍ በደረሰው በ21 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ለገቢዎች ጽሕፈት ቤት ወይም ለማዘጋጃ ቤት ወይም ለታዳጊ ከተማው እንደገና ይታይልኝ የሚል አቤቱታ ያቀረበ እንደሆነ፣ ለአቤቱታው ገንዘብ ሳያስይዝ ቅሬታው በቀረበበት 10 የሥራ ቀናት ውስጥ የገቢዎች ጽሕፈት ቤት ወይም ማዘጋጃ ቤቱ ወይም የታዳጊ ከተማው አወሳሰኑን በማየት ለቀረበው ቅሬታ በጽሑፍ ምላሽ መስጠት እንደሚኖርበትም ረቅቅ ደንቡ ያስረዳል።
በተሰጠው የቅሬታ የጽሑፍ ምላሽ ያልተስማማ ከፋይ እንዲከፍል ከተወሰነበት ገንዘብ ቅጣትና ወለድን ሳይጨምር የዋናውን ክፍያ 50 በመቶ የሚሆነውን በቅድሚያ አስይዞ፣ በየደረጃው ለተቋቋመው የአገልግሎት ክፍያ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በ30 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ይግባኝ በመጠየቅ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለውም ይላል።
ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አቤቱታው በደረሰው በ30 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ በአገልግሎት ክፍያዎች መጠን ላይ የተሰጠውን ውሳኔ እንደ አስፈላጊነቱ የማፅናት፣ የማሻሻል ወይም የመሻር ሥልጣን እንደሚኖረውና የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑም ተጠቅሷል።
ከዚህ አልፎ ይግባኝ ኮሚቴው በሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ ከፋይ እንዲከፍል ከተወሰነበት ገንዘብ ቅጣትና ወለዱን ሳይጨምር የዋናውን ክፍያ 50 በመቶ የሚሆነውን በቅድሚያ በማስያዝ፣ ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ30 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ይግባኝ የመጠየቅ አቤቱታ የማቅረብ መብት በረቂቅ ደንቡ ተረጋግጧል። ነገር ግን መደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊያይ የሚችለው የሕግ ስህተት ያለበት መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ተመልክቷል።
በረቂቅ ደንቡ እንደተገለጸው ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበ የከተማ አገልግሎት ገቢ ይግባኝ የክርክሩ ተከራካሪ የነበረ ሰው ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ እንደሆነ፤ የፍርድ ቤቱ ወሳኔ በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኙን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል ሲገለጽ፣ ከከተማ አገልግሎት ክፍያ ጋር በተገናኘ በሚደረግ ማንኛውም የክርክር ሒደት የከተማ አገልግሎት ክፍያ ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን የማስረዳት ኃላፊነት ክፍያው የተጣለበት ከፋይ መሆኑም ተደንግጓል።
በሌላ በኩል በረቂቅ ደንቡ መሠረት የተወሰነበትን ማዘጋጃ ቤታዊ ወይም የአገልግሎት ክፍያ በወቅቱ ሳይከፍል የቀረ ማንኛውም ሰው በወቅቱ የባንክ የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ መሠረት ክፍያው በዘገየበት በየወሩ ወይም የወሩ ከፊል ለሆነው ቀን ወለድ እንደሚከፍል የሚደነግግ ሲሆን፣ ነገር ግን በዘገየበት ጊዜ የሚጣል ወለድ ጣሪያ ካልተከፈሉ ዕዳዎች መብለጥ እንደሌለበት ተገልጿል።
የተወሰነበትን ማዘጋጃ ቤታዊ ክፍያ በወቅቱ ሳይከፍል የቀረ ማንኛውም ሰው በዘገየበት ለመጀመሪያው ወር ሦስት በመቶ፣ ከሁለተኛው ወር ጀምሮ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ ወር ወይም ለወሩ ከፊል ጊዜ ደግሞ ሁለት በመቶ ቅጣት እንዲከፍል እንደሚደረግ ሲደነገግ፣ ሆኖም የሚከፈለው ቅጣት ጣሪያ ካልተከፈለው ወይም ከዋናው ዕዳ መብለጥ የለበትም ተብሏል።
የአገልግሎት መሠረቱ ሲለወጥ ወይም ሲቋረጥ በወቅቱ ለማዘጋጃ ቤቱ ያላሳወቀ ሰው ለእያንዳንዱ የክፍያ ዘመን የተመደበውን የማዘጋጃ ቤት ግብርና የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፍል እንደሚደረግ፣ በከተማው ክልል የገበያ ቦታዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ሲባል እንደ ገበያ ከተከለሉ ቦታዎች ውጪ የንግድ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከረቂቅ ደንቡ ጋር በተያያዘ የታሪፍ ምጣኔ ሰንጠረዥ መሠረት መቀጫ እንደሚከፍል ተገልጿል።
በተመሳሳይ ጥፋት ለሁለተኛ ጊዜ ከተገኘ የሚጣልበትን መቀጫ በእጥፍ እንዲከፍል የሚደረግ ሲሆን፣ ከሁለት ጊዜ በላይ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገኝ የከፈለውን ሦስት እጥፍ መቀጫ እንደሚከፍል ተደንግጓል።
የአገልግሎት ክፍያ ውሳኔ ማሳወቂያ በደረሰው በሰላሳ ተከታታይ ቀናት ውስጥ ተፈላጊውን ክፍያ ያልከፈለ ወይም በረቂቅ ደንቡ ውስጥ በተደነገገው መሠረት ያቀረበው ቅሬታ ኖሮ፣ ይኸው ቅሬታ ሥልጣን ባለው አካል ታይቶ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ጉዳዩን ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ማቅረብ ባለበት የጊዜ ገደብ ውስጥ የማቅረብ መብቱን ያልተጠቀመ የአገልግሎት ክፍያ ከፋይ ቢኖር አግባብ ያለው የከተማ አስተዳደር፣ ማዘጋጃ ቤት ወይም ታዳጊ ከተማ ሀብትና ንብረቱን ሊያስከብር ወይም ሊይዝ፣ ሊሸጥና ለዕዳው ማካካሻ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል ሥልጣን በደንቡ ተሰጥቶታል። ይሁንና ይህን የማስፈጸሚያ ዝርዝር ጉዳይ ይህንን ደንብ ተከትሎ በሚወጣው መመርያ እንደሚወሰንም ተገልጿል።
በረቂቁ እንደተጠቀሰው በደንቡ መሠረት የተጣለ አስተዳደራዊ ቅጣት ከፋዩ ፍሬ የማዘጋጃ ቤታዊ ክፍያ የከፈለበት ጊዜ መክፈል ከሚጠበቅበት ጊዜ አንፃር ታይቶ መቀጫው ሊነሳ እንደሚችልና የዚህም አፈጻጸም በመመርያ እንደሚወሰን፣ አስተዳደራዊ ቅጣት የማንሳት ሥልጣን የክልሉ ገቢ ሰብሳቢ አካል መሆኑን፣ እንዲሁም ደንቡን መሠረት በማድረግ የተጣለ ወለድ የማይነሳ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ የሚከፈል መሆኑም ተደንግጓል።