

የአቃቂ አካባቢ የወንዝ ዳርቻ
ማኅበራዊ የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻን ደንብ አራት ተቋማት ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ሥልጣን ተሰጣቸው
ቀን: March 12, 2025
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዝ ዳርቻ ልማትና ብክነትን በተመለከተ ያወጣውን ደንብ፣ አራት የመንግሥት ተቋማት ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ሥልጣን መስጠቱ ታወቀ፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማትና ብክነትን በተመለከተ የወጣውን አዲሱን ደንብ ለማስፈጸም ሥልጣን የተሰጣቸው የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንና የመንገዶች ባለሥልጣን መሆኑናቸውን ሪፖርተር ያገኘው ሰነድ ያስረዳል፡፡
በዚህ መሠረት በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ልማት ይዞታና ጥበቃ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም በወንዞች ላይ ደረቅ ቆሻሻና ፍሳሽ ሲጣል፣ ሲደፋ፣ ሲለቀቅ፣ ወይም እንዲለቀቅ ሲደረግ በድርጊቱ ፈጻሚ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥልጣን ያለው የከተማው ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ እንደሆነ አዲሱ ደንብ ያሳያል፡፡
ቢሮው አግባብነት ያላቸውን አካላት በማስተባበርና አስፈላጊውን የሙያ ድጋፍ በመስጠት ይህንን ደንቡን እንደሚያስፈጽም፣ በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ልማት ይዞታ ላይ ሕገወጥ ድርጊት መፈጸሙ ከነዋሪዎች ጥቆማ ሲቀርብ ተቀብሎ ማጣራትና መፍትሔም እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
በወንዝ ዳርቻ ውስጥ ለልማት የሚፈቀዱና የማይፈቀዱ ተግባራትን እንደሚወስን፣ በውኔው መሠረትም የማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ በተለይም በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ልማት ክብካቤና ጥበቃ ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት በትብብር እንደሚሠራ ደንቡ ያብራራል፡፡
በሌላ በኩል በሕግ መሠረት የተመዘገቡና ፈቃድ ያገኙ አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ደንብና በዚህ ደንብ መሠረት አክብረው መሥራታቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡
ባለሥልጣኑ ከወንዝና ከወንዝ ዳርቻ የፍሳሽ ወይም የቁሶችን ናሙና በመውሰድ በላቦራቶሪ እንዲመረመር እንደሚያደርግ፣ የምርመራውን ውጤት መሠረት አድርጎ ዕርምጃ እንደሚወስድ በደንቡ ላይ ተብራርቷል፡፡
የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ መዋላቸውን የመቆጣጠር ሥልጣን ባለሥልጣኑ የተሰጠው ሲሆን፣ በወንዝ ብክለት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት በካዩ ወደ ቀድሞ ሁኔታ የሚመልስበት የአሠራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ደንቡ ያስረዳል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ያወጣውን ደንብ ዓላማዎችና ድንጋጌዎች ለማስፈጸምና ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን የማከናወን ተግባር የባለሥልጣኑ ሲሆኑ፣ ማንኛውም ሰው ወደ ወንዝና ወደ ወንዝ ዳርቻ የሚለቀው ፍሳሽ ብክለት የማያስከትል መሆኑን አለመሆኑን ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን እንደተሰጠው ሰነዱ ያመለክታል፡፡
በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ልማትና ይዞታ ላይ ለሚደርስ ጉዳት፣ ደረቅ ቆሻሻ ወይም ፍሳሽ ሲጣልም ሆነ ሲደፋ በድርጊት ፈጻሚው ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ለደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የተሰጠ መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል፡፡
ከማንኛወም መኖሪያ፣ አምራች ሆነ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ጎርፍ ማስወገጃ መስመር እንዳይገባ የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰው ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን፣ ጥፋት ፈጽሞ የተገኘን ማስረጃ በማደራጀት ለደንብ ማስከበር ባለሥልጣን መረጃውን የማስተላለፍ ሥራ እንደሚያከናውን በደንቡ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ወደ ጎርፍ ማስወገጃ መስመር የተለቀቀ ፍሳሽ የበካይነትና አደገኛነት ደረጃ እንዲጣራ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጥቆማ የማቅረብ ሥልጣን ለባለሥልጣኑ እንደተሰጠው ደንቡ ያብራራል፡፡
የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ብክለትን አስመልክቶ የተቀመጠው አስተዳዳራዊ የገንዘብ ቅጣት እንደሚያሳየው፣ በባህሪው አደገኛነት ያለው ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መጣል ወይም እንዲጣል በማድረግ መበከል ለድርጅት አንድ ሚሊዮን ብር የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ 500 ሺሕ ብር እንዲቀጣ በደንቡ መሥፈሩን በሰነድ ተመልክቷል፡፡
ከጤና ተቋማት፣ ከትምህርት ተቋማት፣ ከነዳጅ ማደያዎች፣ ከጋራዦች፣ ከመኪና ጣቢያዎች የሚወጡ የተለያዩ በካይ ኬሚካል ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ላይ ማከማቸት ወይም መጣል፣ እንዲሁም መልቀቅ 400 ሺሕ ብር የሚያስቀጣ መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል፡፡
ከመኖሪያ ቤት፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ከአምራች ድርጅቶች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች፣ የጠርሙስ ስብርባሪ፣ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ጣሳዎች፣ ፕላስቲክና የፕላስቲክ ከረጢቶች፣ ደረቅ ቆሻሻና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸው በካዮች በወንዝና በወንዝ ዳርቻ መድፋት ወይም መጣል ግለሰብን 20 ሺሕ ብር ሲያስቀጣ፣ ለድርጅት 100 ሺሕ ብር ቅጣት የሚጥል መሆኑን በደንቡ ተካቷል፡፡
ከመኖሪያ ቤት የሽንት ቤት ወይም ማንኛውም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ የለቀቀ ወይም መስመሩን አገናኝቶ ወንዙን የበከለ ግለሰብ 150 ሺሕ ብር ቅጣት እንደሚጣልበት ሰነዱ ያሳያል፡፡
በወንዝና በወንዝ ዳርቻ ውስጥ ከተፈቀደው የወንዝ፣ የመናፈሻ ፓርክና ሌሎች ለወንዝ ዳርቻው ልማት አስፈላጊ ከሆነ ግንባታ ውጪ የፕላስቲክ ቤት ወይም ማንኛውም ዓይነት ግንባታ መገንባት 200 ሺሕ ብር እንደሚያስቀጣ በደንቡ ተደንግጓል፡፡
በወንዝ ዳርቻ ክልል ውስጥ እንስሳት ማሰማራት ወይም እንዲገቡ ማድረግም ሆነ ከተፈቀደ መግቢያና መውጫ ተሽከርካሪ ማሽከርከር 30 ሺሕ ብር እንደሚያስቀጣ በደንቡ ተቀመጠ ሲሆን፣ 21 ያህል የቅጣት ዓይነቶች በደንቡ መካተታቸውን ሰነዱ ያብራራል፡፡
