ማኅበራዊ
ለከት ያጣ የኑሮ ውድነት

አበበ ፍቅር

ቀን: March 12, 2025

ወ/ሮ መሠረት ሲሳይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሁለት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሯሯጡ አዲስ በሚሠሩ ሕንፃዎችና ከአውራ ጎዳና ራቅ ባሉ አካባቢዎች ቡናና ሻይ በማዞር እየሸጡ ነው፡፡ ‹‹ከሚባለው በላይ ኑሮ ከብዶኛል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ ብቻ ለጊዜው ከዚያም ከዚህም እየተሯሯጥኩ ልጆቼን እያሳደኩ ነው፡፡ በየዕለቱ የማይጨምር ነገር የለም፤›› በማለት እየገጠማቸው ያለውን ለሪፖርተር አጋርተዋል፡፡

ዛሬ ላይ ያሉበት አካባቢ በኮሪደር ልማት ባለመፍረሱ እዚህም እዚያም እያሉ እንዳሚሠሩ የሚናገሩት ወ/ሮ መሠረት፣ እንደ ሌሎች አካባቢዎች በልማት ተነስተው ቢሆን፣ ኑሮው የበለጠ ሊከፋባቸው ይችል እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

የበኩር ልጃቸው 12ኛ ክፍል ተፈትኖ ባለማለፉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለ ምንም ሥራ አብሯቸው ይኖራል፡፡ ሴት ልጃቸው 10ኛ ክፍል ናት፡፡ ለልጃቸው የሚያስፈልጋትን ነገር አሟልቶ ለማስተማር መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እንደምታየኝ ይቺን ቡናና ሻይ ከብስኩት ጋር በየመንገዱ በመሸጥ ነው የቤት ኪራይ የምከፍለው፣ ልጅ የማስተምረው፣ የዕለት ተለት ኑራችንን የምመራው ከዚህች ከማገኛት ገንዘብ ነው፡፡ ይህንንም በስንት ትግል መሰለህ ብዙ ቀን በጊዜያዊነት ተይዤ ተፈትቼያለሁ፡፡ በየቀኑ ቦታ እለዋውጣለሁ፡፡ ይህ በመሆኑም ቋሚ ደንበኛ አፍርቼ ለመሥራት አልታደልኩም፤›› ሲሉ እንባ በቀረው መከፋት ብሶታቸውን ይናገራሉ፡፡

በዘጠናዎቹ አካባቢ ከባለቤታቸው ጋር ቦሌ አካባቢ ቤት ሠርተው ከመኖር ባሻገር  አከራይተው የወር ገቢ ያገኙ እንደነበር የሚያስታውሱት ወ/ሮ መሠረት፣ ነገር ግን የጨረቃ ቤት በመሆኑ ብዙም ሳይኖሩበት እንደፈረሰባቸውና ከዚያን ጊዜ ጀምረው ተከራይተው  እየከፈሉ እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡

ዛሬ ላይ እየተዳደሩበት ያለውን ቡናና ሻይ አፍልቶ የመሸጥ ሥራ ከጀመሩት እንደቆዩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁሉም ነገር እንደተቀያየረባቸው፣ የሥራ ቦታ ማጣት፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ የሰዎች ገቢ መቀነስና ሌሎችም ችግሮች በሚሠሩት  ሥራ ወጪያቸውን በአግባቡ ለመሸፈን እንዳላስቻላቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ልጆች ባሉበት ቤት ማታ የሆነ ነገር ይዤ ካልገባሁ እንኳን ልጆቼን እኔንም ቅር ይለኛል፡፡ ስላስለመድኳቸው ስገባ እጅ እጄን ነው የሚያዩት ፡፡ የምሠራው ሥራ ያው  የቀን ሥራ በለው፡፡ ደንቦች መጡ አልመጡ መሳቀቅ፣ ሲመጡ ዕቃ  ሸክፎ መሮጥ ነው፡፡ ሕይወቴ በብዙ ውጣ ውረድ የተሞላች ናት፡፡ ቢሆንም ግን ተመስገን ማለቱ የተሻለ ነው፡፡ ማታ ለልጆቼ የሆነች ነገር ይዤ እገባለሁ፡፡ ሰው ጤና ከሆነ ፈጣሪን ማመስገን የተሻለ ነው፤›› በማለት ስለሆነውም ስላልሆነውም ያመሰግናሉ፡፡

በተለይ ደግሞ በዚህ ሁለትና ሦስት ሳምንት በምግብ ፍጆታዎችና በአቅርቦት ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስደነግጥ፣ ቡና የሚያፈሉት ከመቀመጥ በሚል እንጂ አዋጪነቱ የሚታይ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በቅርብ ቀን አምስት መቶ አካባቢ ይገዛ የበረው አንድ ኪሎ ቡና ዛሬ ላይ ስምንት መቶ ብር ገብቷል፡፡ አንድ ሲኒ ቡና አሁን ከሚሸጥበት 25 ብር በላይ ብጨምር የሚገዛኝ አይኖርም፡፡ እንዳልተወው ከሰው ቤት ተቀምጬ  ነገ ጎዳና ላይ እወድቃለሁ፡፡ እንዳልሠራም እንደምታየው ቀን በቀን ማባሪያ የሌለው የዋጋ ንረት ያለበት አገር ላይ ነው ያለነው›› ይላሉ፡፡ ሥራቸው ልፋት ብቻ እንደሆነም በምሬት ይናገራሉ፡፡

የዘይት ነገርም እንዳስገረማቸው፣ ከሦስት ሳምንት በፊት 1,200 ብር አካባቢ የነበረው አምስት ሌትር ዘይት በአሁኑ ወቅት ከ1,600 እስከ 1,800 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ያክላሉ፡፡

ክፍለ አገር ያሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ ስለ ኑሮ ውድነቱ በየቀኑ እንደሚያወሩ የሚናገሩት ወ/ሮ መሠረት፣ በዚህም የኑሮ ውድነቱ ከከተማ እስከ ገጠር መሆኑን መታዘባቸውን ይገልጻሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ መሠረት ሁሉ፣ ብዙ ሰዎች ስለዘይት መወደድ፣ ስለ እንቁላልና ስለቡና ዋጋ መጨመር፣ ስለ ትራንስፖርት፣ ስለ መብራትና የውኃ ፍጆታ ማሻቀብ፣ ስለ ቤት ኪራይ ፣ስለ ጣሪያ ግድግዳ ግብር ከዓምናው መጨመርና ስለሌሎችም በርካታ የዋጋ ንረቶች ቆመውም ተቀምጠውም በሚገናኙበት ሁሉ ያወራሉ፡፡ በትራንስፖርት፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ ሥፍራዎች፣ በሠርግ፣ በሐዘን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁሉ  የሚያወሩት አንድ ዓይነት ርዕስ ነው፡፡ እሱም ስለኑሮ ውድነት፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም ማነስና የፍጆታ እቃዎች ዋጋ  ከዕለት ወደ ዕለት መናር ነው፡፡ ችግሩ ግን ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ›› እንደሚባለው ጠብ የሚል መፍትሔ መታጣቱ ነው፡፡

አንድ የሸቀጣሸቀጥ ነጋዴ እንደተናገረው፣ በሁለት ወር ውስጥ በአንድ ኩንታል የአገር ውስጥ ምስር ላይ ዘጠኝ ሺሕ ብር ጨምሯል፡፡ እንደ ነጋዴው ትዝብት፣ በሌሎች ሸቀጦች ላይ ጭማሪ ቢታይም፣ በተለይ በዚህ ወር እንደ ቡና፣ ዘይትና የወጥ ቤት እህሎች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ስለተለመደ እንጂ በጣም አስደንጋጭ የሚባል ነው፡፡

በሁሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ ዘይትና ቡና እንዲሁም የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ የማይቀመስ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በወፍ በረር ያናገርናቸው ነዋሪዎችም፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች የሸቀጦች ዋጋ ጣሪያ መንካቱን ነግረውናል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኦማር የሚባለው ዘይት አምስት ሊትር እስከ 1,700 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ሌላ ስያሜ ያላቸው ዘይቶችም እንዲሁ 1,530 እስከ 1,600 ብር ድረስ እየተሸጡ ነው፡፡ ቡና በኪሎ ከ700 መቶ ብር እስከ 800 ብር ድረስ ሲሸጥ፣ የአገር ውስጥ ምስር በኪሎ እከከ 290 እንዲሁም ከውጭ የሚገባው 260 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ በዱቄትና በሌሎች ሸቀጦች ላይም የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡

አቶ ሁሴን (ስማቸው ተቀይሯል) የተባሉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ የዋጋ  ግሽበቱን አሳሳቢነት እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዓብይ ፆም፣ እንዲሁም ‹‹በእኛ በእስልምና እምነት ደግሞ የረመዳን ፆም የሚከናወንበት›› ወቅት ቢሆንም፣ የዋጋ ንረቱ አፅዋማቱን አስታከው የመጡ ናቸው እንዳይሉ አድርጓቸዋል፡፡ ምክንያቱም  የክርስቲያኖች ፆም ሲገባ መቀነስ የነበረበት የእንቁላል ዋጋ በነበረበት ቀጥሎ ከ14 ብር  እስከ 18 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በሌሎች ሸቀጦችም በተመሳሳይ እንደ ድንችና ቲማቲም ያሉ ቀላል የሚመስሉ ምግቦችም ቢሆኑ ዋጋቸው እየጨመረ እንደሚገኝ  ሪፖርተር  መታዘብ ችሏል፡፡

 አበባ ጎመን 250 ብር በኪሎ፣ ዝንጅብል 190 ብር በኪሎ፣ ፎሶሊያ 250 ብር በኪሎ፣ ቴምር እርጥቡ በኪሎ 400 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሽማቾች ተናግረዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ ኑሮን ተቋቁሞ ለመኖር እጅግ አዳጋች እየሆነ የመጣበት ጊዜ ላይ እንደሚገኙም በምሬት ነግረውናል፡፡ ለልጆች ዕድገት አስፈላጊ ናቸው ያሏቸው እንደ ወተት፣ ሥጋ፣ እንቁላል፣ አሳ እንዲሁም በየማስታወቂያው ‹‹ልጆች እንዳይቀነጭሩ አረንጓዴ ተክሎች አብሉ›› ብሎ በቀላሉና በተደጋጋሚ እንደሚነገረው ሳይሆን፣ አሥር እግር የማይሞላ ጎመን እንኳን ለመግዛት ከ40 እስከ 50 ብር እንደሚጠየቅ፣ ቆስጣም ቢሆን እፍኝ የማይሞላው 30 ብር፣ ጥቅል ጎመን በኪሎ 45 ብር፣ ዝኩኒ ካሮትና የሌሎችም ዋጋ ሰዎችን በልተው የማደር አቅም እንደሚፈታተን አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን ላይ ለልጆች መሠረታዊ ጤንነትና ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችን ገዝቶ ማብላት አለመቻል ያማል፤›› የሚሉት እኚሁ ተቀጣሪ፣ ከሁሉም በላይ የኑሮ ውድነነቱ ብስጩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ የልጆች የንፅህና መጠበቂያ፣ ሳሙናና ዳይፐር እንዲሁም የወር አበባ መጠበቂያ የመሳሰሉ መሠረታዊ መገልገያዎች ከአቅም በላይ እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ፡፡

ከሳምንት በፊት ለአስቤዛ ያወጡት ወጪ ከሳምንት በኋላ ሲሄዱ እንደሚጨምር፣ በወር ለምግብ ብቻ የሚያወጡት ወጪ በየጊዜው የሚጨምርና ከአቅም በላይ በመሆኑ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ሁሉ ትተው ለልጆቻቸው ብቻ እንዲያስቡ እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራሁ ነው የሚለው ምን እንደሆነም አልገባኝም፤›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡