ማኅበራዊ
በተለያዩ ተግዳሮቶች የሚፈተነው የትምህርት ጥራት

የማነ ብርሃኑ

ቀን: March 12, 2025

የትምህርት ጥራት በትውልዱ ላይ የተደቀነ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ የተማረ፣ የሠለጠነና በክህሎት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገው ጥረት በከፍተኛ ተግዳሮት ውስጥ በማለፍ ላይ ይገኛል፡፡ በየጊዜው በመለዋወጥ ላይ በሚገኘው ዓለም የትምህርት ዘርፍ ከዘመኑና ከቴክኖሎጂ ጋር እየተቃኘ ስላልመጣ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ የሚናገሩት ነው፡፡

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥራት ያለው ትምህርት የምዝገባ ቁጥሮችን መጨመር ብቻ ሳይሆን መማርን፣ ፈጠራንና ችግር መፍታትን የሚያበረታታ የትምህርት ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በደንብ የሠለጠኑና ተነሳሽነት ያላቸው መምህራን ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ሥርዓተ ትምህርት፣ በቂ የትምህርት ግብዓቶች ለትምህርት ቅድሚያ የሚሰጥ የአስተዳደር መዋቅር ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲና የትምህርት ፍኖተ ካርታ የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ዋና ቁልፍ ነው፡፡ በመሆኑም የመምህራን ልማት፣ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ፣ የትምህርት ፋይናንስና ቴክኖሎጂ ውህደት የመሳሰሉ ወሳኝ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባልም ብለዋል፡፡

እንደ ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፣ እነዚህ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ቢኖሩም፣ የመምህራን ብቃት ክፍተቶች፣ የሀብት ክፍፍል ልዩነቶች፣ በቂ ያልሆነ የግምገማ ዘዴዎችና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኛነት ዛሬም የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

‹‹ጥራት ያለው ትምህርት በተናጠል ሊገኝ የሚችል አይደለም፤›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በመሆኑም የመንግሥት አካላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፎችና ከኅብረተሰቡ ከፍ ያለ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማጠናከር ትብብር፣ ቁርጠኝነትና በሁሉም ደረጃ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ አዳዲስ መፍትሔዎችን በመተግበርና የትምህርት ሥርዓቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን የሚያሟላ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ሲሉም አክለዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ እንደሚገልጹት፣ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ችግሮችም የክልሉ የፀጥታ ችግር የወለዳቸው ናቸው፡፡

በመሆኑም በፀጥታ ችግር ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መጠገን፣ ከትምህርት ገበታ የራቁ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት መመለስ፣ የትምህርት ግብዓት ቁሳቁሶችን ማሟላትና መምህራንን ወደ መማር ማስተማር ሒደት የመመለስ ሥራ በማከናወን የትምህርት ዘርፉን መታደግ እንዲቻል የባለድርሻ አካላት ትብብር ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ላይ በክልሉ ከሚገኙ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ወደ 3,700 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት አይሰጡም፤›› ያሉት አቶ መኳንንት፣ እናስተምራለን ካልነው ሰባት ሚሊዮን ተማሪ አካባቢ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኘው 2.8 ሚሊዮን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ ትምህርት ገበታ ያልመጡት 4.2 ሚሊዮን ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ እንዲገኙ ለማድረግ በትምህርት ቢሮ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ትምህርቱ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰጥ በባለሙያዎች የታገዘ የድጋፍን የክትትል ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ግዑሽ (ዶ/ር) አገላለጽ፣ በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ጦርነቱ የወለዳቸው በርካታ ችግሮች ዛሬም አልተፈቱም፡፡ በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን የመጠገን፣ በሞትና በመሳሰሉ ምክንያቶች የሌሉ መምህራንን በአዲስ የመተካት፣ ትምህርት ቤቶችን በቁሳቁስ የማደራጀትና ሕፃናቱን ወደ ትምህርት ቤት ገበታ እንዲመለሱ ማድረግ ከፍተኛ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ ውዝፍ የመምህራን ደመወዝ ክፍያ ሌላው ተጨማሪ ፈተናም ነው፡፡

በክልሉ በትምህርት ዘርፉ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታትና የትምህርት ሥርዓቱ ጤናማና ጥራቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲቀጥል የፌዴራል መንግሥት፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ዕገዛና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ኪሮስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ እንዳመለከቱት፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡

‹‹የትምህርት ጥራት በዋነኛነት በመምህራን ብቃትና ጥራት ላይ የተመሠረተ ነው፤›› የሚሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ከዚህ አንፃር የመምህራን ምልመላ፣ ዝግጅት እንዲሁም የሥራ ላይ ተከታታይ ሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ዘመኑን የዋጀ ሆኖ እንዲቃኝ በርካታ ጥረቶች በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ዓምና ክረምት ከ50 ሺሕ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማስገባት ሰፋ ያለ የአቅም ግንባታ ሥራ የተሠራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡   

ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቷ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተኑ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ሲነገር ከርሟል፡፡ የትምህርት ለሁሉም ተደራሽነት፣ ዝቅተኛ ትምህርት ጥራት፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የመምህራን እጥረት፣ የልዩ ፍላጎት መምህራን አለመኖር፣ የአካል ጉዳት (የመስማትና የማየት ችግር) ያለባቸውን ልጆች ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ለማስተማር የሚያስችል የሰው ኃይልም ሆነ አመቺ ትምህርት ቤት አለመኖር ዘርፉን ከሚፈትኑ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡