
March 12, 2025

አቶ ይልማ ደለለኝ የኔቸር ኮንሰርን ፋውንዴን መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆግራፊ ትምህርት የተከታተሉት አቶ ይልማ፣ ከታንዛኒያ አሩሻ ኮሌጅ ኦፍ አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ በማኔጅመንት በአድቫንስ ዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከእንግሊዝ ኬንት ዩኒቨርሲቲ በኮንሰርቬሽን ባዮሎጂ (ብዝኃ ሕይወት አስተዳደር) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ አሁን ላይ በሰዎችና አዕዋፍ (ኢትኖ ባዮሎጂ) መካከል ስፔሻላይዜሽን በማጥናት ላይ ናቸው፡፡ ኬንያ በሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮ ሠርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ተቀጥረው በልዩ ልዩ ኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ የባለሥልጣኑ ቲንክ ታንክ አባል ናቸው፡፡ አቶ ይልማን በዱር እንስሳት ጥበቃና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙትን የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎችን እንዴት ይገመግሟቸዋል?
አቶ ይልማ፡- የዱር እንስሳት ቦታዎችን እንደ ምሽግ ከሕዝብ ለይተንና አጥረን በመሣሪያና በአጥር ስንጠብቃቸው ኖረናል፡፡፡ ይህ ዓይነቱ ሞዴል በኢትዮጵያ አይሠራም፡፡ እየሆነ ያለው ግን ይኼው ነው፡፡ በዘውዳዊው ሥርዓት የዱር እንስሳት ጥበቃ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ታምኖበት ነበር፡፡ ይህም እምነት እውነታ አለው፡፡ ግን ጥበቃው በጠመንጃና በአጥር የተከለለ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡን ጠቃሚ አላደረገም፡፡ ከዚያ አኳያ የጥበቃ ቦታዎች የተፈለገውን ያህል ጥቅም አላስገኙም፡፡ በደርግ ሥርዓትም የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓትና በመንግሥት ብቻ የሚከናወን አካሄድ ስለነበር ጥበቃውን ማሻሻል ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በጥበቃው ዙሪያ የሚኖረው ኅብረተሰብ ‹እርሻችንን እንዳናስፋፋ ትልቅ እክል የፈጠሩብን የዱር እንስሳት ናቸው› የሚል አመለካከት እየፀናበት መጣ፡፡ በ1983 ዓ.ም. የደርግ ሥርዓት ወድቆ ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን እንደተረከበ፣ በዱር እንስሳቱ ላይ ቂም ቋጥሮ የነበረው ኅብረተሰብ በጥበቃ ቦታዎች ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡ በርካታ የዱር እንስሳትም ተገደሉ፡፡ አገሪቱ በክልል ደረጃ ስትዋቀር ደግሞ አንዳንድ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች በክልሎች ሥር እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ክልሎች በዚህ ሁኔታ ለጊዜው ደስ ቢላቸውም፣ የማስተዳደር አቅም ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህሉ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ናቸው በክልሎች ሥር የሚተዳደሩት?
አቶ ይልማ፡- አሁን ለጊዜው ያለኝ መረጃ በፌዴራል ደረጃ የሚተዳደሩ የጥበቃ ቦታዎች 11 ሲሆኑ፣ የቀሩት ግን በየክልሎች ይተዳደራሉ፡፡ የኅብረተሰብ ፓርኮችም እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከእንደነዚህ ዓይነት ፓርኮች መካከል አንደኛው የመንዝ ጓሳ ተጠቃሽ ነው፡፡ በጓሳ ፓርክ ተጠያቂነትና ሥልጣን ያለው የአካባቢው ኅብረተሰብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፓርኮች በአካባቢው ኅብረተሰብ ካልተጠበቁ በስተቀር የሕገወጥ ሠፈራ፣ የእርሻና የግጦሽ ቦታ ይሆናሉ፡፡ ምን መደረግ አለበት?
አቶ ይልማ፡- አንድ ቦታ ለፓርክ አገልግሎት በሚከለልበት ወቅት ብዝኃ ጥቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም ማለት ፓርኩ ውስጥ ሰው ለሰው እንቅስቃሴ ሊገታ ይገባል፡፡ ፓርኩን በሚያዋስኑ አካባቢዎች ለሚኖረው ኅብረተሰብ ግን ከፓርኩ ጥቅም የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ‹ፓርኩ በመኖሩ ህልውናችን እየታደሰ መጥቷል› ብሎ ኅብረተሰቡ በራሱ እንዲያምንና በውስጡም ተነሳሽነትን እንዲፈጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተነሳሸነት በውስጡ እስካልሰረፀ ድረስ የሚሠራው ሥራ ሁሉ የሽንፈት ይሆንበታል፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ እርስዎ አረዳድ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ውጤታማ እንዲሆኑና ማልማትም እንዲቻል በምን መልኩ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል?
አቶ ይልማ፡- ምርታማና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ካስፈለገ በጥበቃው ወሰን ዙሪያ የሚኖረውን ኅብረተሰብ ከገቢው ቀጥተኛ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በማይደርስባቸው ወይም ከአቅሙ በላይ የሆኑትን የጥበቃ ቦታዎች በመንግሥና በግሉ ዘርፍ አጋርነት መርህ መሠረት ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የዱር እንስሳት ጥበቃን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም አሁን የሚታየው መቆራቆዝና አምቧጓሮ ተወግዶ በምትኩ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሕጎች፣ የሕግ ማዕቀፎች ፖሊሲዎችና መመርያዎች ለጥበቃዎቹ የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን ሁኔታ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ፓርኩ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኃላፊዎች፣ እስካውቶችና የዱር እንስሳት ባለሙያዎች ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ፣ የተመረጡና ለዚህም በቂ ዕውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በየወቅቱም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ማግኘት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የዱር እንስሳት ጥበቃ በኅብረተሰቡ እንዲከወን ያደረጉ የአፍሪካ አገሮች አሉ? ከኢትዮጵያ የዱር እንሰስሳት ጥበቃ ከሚገኘው ገቢ የመንግሥትና የኅብረተሰቡ ድርሻ ስንት እንደሆነ ይታወቃል?
አቶ ይልማ፡- አዎ አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ኬንያንና ደቡብ አፍሪካን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለይም የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃን በኅብረተሰቡ ማከናወን እንደ ባህል ተያይዞ የመጣ ሲሆን፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብም የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ የሚገኘው ገቢ ቀደም ሲል ለመንግሥት ነበር፡፡ አሁን ግን ተሻሽሏል፡፡ ምን ያህል እንደሆነ ባላውቅም የተወሰነው ወደ ኅብረተሰቡ ነው የሚሄደው፡፡
ሪፖርተር፡- ከተለያዩ አዕዋፋት መካከል አንደኛው የመስቀል ወፍ ይገኝበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ወፍ በዓመት አንዴ ብቻ ብቅ ይላል፡፡ ለምን እንደሆነ ቢገልጹልን?
አቶ ይልማ፡- ስለ መስቀል ወፍ ስናወራ ከወፊቷ ጋር ተያይዞ የመጣ እስካሁንም ያለ አባባል አለ፡፡ አባባሉም ለብዙ ጊዜ ጠፍቶ ድንገት የሚመጣ ሰው ‹አንተ እኮ የመስቀል ወፍ ሆንክ› ይባላል፡፡ የመስቀል ወፍ የሚመጣው በየዓመቱ መስከረም ሲጠባ ወይም መስከረም ሊጠባ ሲል ነው፡፡ አለበለዚያም ክረምት አልፎ በጋ ሲመጣ ብቅ ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ የመስቀል ወፍ በዓመት አንዴ ብቻ የሚመጣ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ ግን ባካሄድኩት ጥናትና ምርምር ላይ የደረስኩበት ነገር ቢኖር የመስቀል ወፍ ሁልጊዜ ዓመቱን ሙሉ አለ፡፡ ሳያቋርጥ ይኖራል፡፡ የሚሰወረው ግን ቀለሙን በመቀያየር ነው፡፡ ቀለሙንም ሲቀያየር የሄደ ወይም የጠፋ ይመስላል፣ ግን አለ፡፡ ቀለሙን የሚያቀያይረውና ላባውም ረዥም የሚሆነው በእርቢ ወቅትና ሰብል በደረሰ ጊዜ ነው፡፡ ለርቢ ራሱን በሚያዘጋጅበት ሰዓት፣ በተለይ ወንዶቹ በጣም ተልቀውና አምረው የሚታዩ ሲሆን፣ ሴቶቹ ደግሞ ደብዘዝ ብለው ይታያሉ፡፡ ወንዱ ወፍ በጣም አምሮና ደምቆ ሴቷን የሚያማልልበት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ተቀናቃኝ የሆነውን ወንድ ማባረር አለበት፡፡ ለዚህም እጅግ በሚያምር ላባ መልክ ራሱን ያስውባል፡፡ ከዚህ አኳያ የመስቀል ወፍ ዓመቱን ሙሉ አለ፡፡ ዝናብ መኖሩንም ከወር በፊት ያውቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡ ዝናብ በሚመጣበት ወቅት ዕፀዋትም ይበቅላሉ፣ ሰብል በየቦታው በስፋት ይኖራል፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይ ሴቶች የሚወልዱበትን አካባቢ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ሽሚያ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ለሚወልዷቸው ወይም ለሚፈለፍሏቸው ጫጩቶች በቂ ነገር እንዲኖር አካባቢውን ይጠብቃሉ፡፡ የመስቀል ወፍ አምስት ዝርያዎችም አሉት፡፡