ዳዊት ታዬ

March 12, 2025

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሚሰጠውን ዕርዳታ ማቋረጡ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቢዝነሶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡ የዕርዳታው መቋረጥ ዩኤስኤአይዲ በቀጥታ ድጋፍ ሲያደርግላቸው የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኩል ሲሰጡ የነበረውን ዕርዳታ ከማስተጓጎል ባለፈ፣ ከእነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የግዥ ስምምነቶችን የፈጸሙ የቢዝነስ ተቋማት ሥራም እየተስተጓጎለ ነው፡፡

ዩኤስኤአይዲ በሚሰጠው ዕርዳታ ከተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር ውል ገብተው ሲሠሩ ከነበሩ አምራች ዘርፎች መካከል አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ለተረጂዎች የሚሆኑ የተለያዩ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን የሚያመርቱ ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍም በተመሳሳይ ቢዝነሶቻቸው ላይ እክል እየገጠማቸው ነው፡፡

አምራቾች አልሚ ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ለተረጂዎች የሚያቀርቡ ምግብ ነክ ምርቶችን አምርተው ለማቅረብ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመዋዋል በቋሚነት ሲያቀርቡ የነበሩ ሲሆን፣ ዩኤስኤአይዲ የሚሰጠውን ዕርዳታ በማቋረጡ ምርቶችን በማቅረብ ያገኙት የነበረውን ገቢ የሚያሳጣቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል እንደ ዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ፣ ሴፍ ዘ ችልድረን (ዩኤስኤአይዲ) ወርልድ ቪዥንና ካቶሊክሪሊፍ አገልግሎትና የመሳሰሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለዕርዳታ የሚያቀርቡትን ምግብ ነክ ምርቶች ከአገር በቀል አምራቾች በመግዛት ለተረጂዎች ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የዩኤስኤአይዲ መቋረጥ የተነሳ መንግሥታዊ ያልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶች ከተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት ጋር የነበራቸውን ውል ወዲያውኑ እንዲቋረጡ አስገድዷቸዋል፡፡

በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መንግሥታዊ ላልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶች ምርቶችን በማምረት ከሚጠቀሱት መካከል ደግሞ ፋፋ የምግብ ኮምፕሌክስ፣ ፎረስ ፋብሪካ፣ ቋሪት፣ አስታኮ፣ ብሌስ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኮምፕሌክስና የመሳሰሉ ፋብሪካዎች ይገኙበታል፡፡

 አንዳንዶቹ አምራቾች ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የገቡት ስምምነት ለአገር ውስጥ ተረጂዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት አገሮች ተረጂዎች የሚቀርቡ ምርቶችን ለማምረት ጭምር ነው፡፡ አሁን ግን በውላቸው መሠረት ማምረት የነበረባቸውን ምርት ከማምረት ተቆጥበዋል፡፡

መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር ለዕርዳታ የሚሆኑ ምግብ ነክ ምርቶችን ለማምረት ውለታ ከገቡ አምራቾች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ውላቸው እንዲቋረጥ የተደረገው የዩኤስኤአይዲ ዕርዳታ እንዳይሰጥ የሚለው የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ በተላለፈ ማግሥት ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የአንድ አልሚ ምግቦች አምራቾች ተወካይ  ሁኔታው ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ነበር ይላሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ተለዋጭ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ምርት አቁሙ መባላቸውንም ገልጸዋል፡፡

ምርት ማቆም ብቻ ሳይሆን ተመርተው ወደ ተለያዩ መጋዘኖችና ተረጂዎች ወዳሉበት አካባቢ እንዲደርሱ በተሽከርካሪ ተጭነው የነበሩ ምግብ ነክ ምርቶች በሙሉ እንዳይንቀሳቀሱ በመባሉ ምርቱ ተራግፎ ወደ አምራቾች መጋዘን መልሶ እንዲገባ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ይህ ዕገዳ ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል ያሉት እኚሁ ተወካይ የዩኤስኤአይዲ ዕገዳ ሦስት ወራት የሚል በመሆኑ ጊዜያዊ ችግር ሊሆን እንደሚችል የተገለጸላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ ግን ዕግዱ የሚነሳ ከሆነ ሊቀጥሉ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከትናንት በስቲያ ከአሜሪካ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ሲተገበሩ የነበሩ ከአምስት ሺሕ በላይ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ የወሰነ በመሆኑ ከሦስት ወራት በኋላም ድጋፉ ሊቀጥል ይችላል የሚለውን ግምት አጨልሞታል፡፡ ይህም አልሚ ምግቦችና ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶችን ለመግዛት የተፈጸሙ ውሎች እንዳይቀጥሉ ያደርጋል የሚል ሥጋት አሳድሮባቸዋል፡፡  

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍም ተመሳሳይ ችግር መፈጠሩ ታውቋል፡፡ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሆቴሎች ገብተው የነበረው ውል እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ መልደሰንበት (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መቋረጥ የተነሳ ሆቴሎች ሲያገኙ የነበረውን ጥቅም አሳጥቷቸዋል፡፡ የዩኤስኤአይዲ አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገው በመላው ዓለም ቢሆንም ይህ ሁኔታ ከአገራችን አንፃር ሲታይ ጉዳቱ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በተለይ በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ሥራ እንዲያቆሙ የሚያደርግ መሆኑ አንድ ጉዳት ነው፡፡ የእነዚህ ሠራተኞች ሥራ ማቆም ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሆቴል ሥራ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ የሆቴል ዘርፉ ሊጎዳ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡

ዩኤስኤአይዲ ዕርዳታ ከፍተኛና ብዙ ፕሮዳክቶች የሚንቀሳቅስ መሆኑን የጠቀሱት ፍትሕ (ዶ/ር)፣ በዓይነት ብቻ ሳይሆን በፋይናንስም ድጋፍ የሚሰጡ በመሆናቸው እንዲሁም በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ ከመሆናቸው አንፃር ኢኮኖሚው ላይ የራሳቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የፕሮጀክቶቹ እንቅስቃሴ በአንዴ እንዲቆም መደረጉ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ዩኤስኤአይዲ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ በቀጥታ ድጋፍ ያደርግ እንደነበር፣ ይህ ድጋፍም የተለያዩ የሥልጠና መርሐ ግብሮችን ያካተተ ሲሆን፣ በዘርፉ ብዙዎችን ማብቃት የተቻለበት እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ይህ በዩኤስኤአይዲ አማካይነት ይሰጥ ስለነበር የዕርዳታው መቋረጥ እንዲህ ያሉ ጠቀሜታ የነበራቸው የሥልጠና ፕሮግራሞችን እንዲቋረጡ አድርጓል ብለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዩኤስኤአይዲ የሚደገፉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሆቴል ዘርፍ አገልግሎቶችን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀሙ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር የዩኤስኤአይዲ ሥራ መቆም በቀጥታ የሆቴሎች ገቢ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ የተለያዩ ሥልጠናዎችንና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ያካተቱ ስለሆኑ፣ የእነዚህ ኮንፈረንሶች መስተጓጉል በቀጥታ የሆቴል ዘርፉን የሚነካ ይሆናል ብለዋል፡፡ የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶቹን ተከታትለው የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችም ቁጥር ቀላል ባለመሆኑ የዕርዳታው መቋረጥ በሆቴሎች ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በየፕሮጀክቶቹ የሚሠሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም የሆቴል ተጠቃሚዎች መሆናቸውን፣ የሥራቸው ባህሪም ቢሆን መስክ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የሆቴሎች ዋነኛ ተጠቃሚዎች ከመሆናቸው አንፃር፣ የሆቴል ቢዝነስ ላይ ከዚህም በኋላ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከእነዚህ የመንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶና ሠራተኞች ጋር ቋሚ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩ ሆቴሎች ኮንትራታቸውን በማቋረጥ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ በእነዚሁ ድርጅቶች የተያዙ የስብሰባና የሥልጠና ፕሮግራሞችም መሰረዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ የሆቴሎች ገበያ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የፍተሕ (ዶ/ር) ማብራሪያ ያመለክታል፡፡  

እንደ አልሚ ምግቦች አምራች ተወካዩ ገለጻ ደግሞ እነዚህ አምራቾች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ገቢ በማሳጣት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን ነው፡፡ አምራቾችቹ ውለታ የገቡበት ምርት ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከአገር ውስጥና ከውጭ በግዥ ያስገቡ ያሉ በመሆኑ እነዚህን ግብዓቶችን መጠቀም ካልቻሉ ኪሳራ ሊያስመዘግቡ የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖር ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ ሊኖር ይችል የነበረውን ምርት ታሳቢ በማድረግም ቀድሞ ግብዓቶችን ለመግዛት ያደረጓቸው ስምምነቶች ለመሰረዝ የሚገደዱበት ሁኔታም ስለሚኖር የአምራቾች ጉዳት በተለያየ መልኩ ሊገለጽ የሚችል መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በኢትየጵያም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ባሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አማካይነት ሊሰጥ የቆየው ድጋፍ ከፍተኛ መጠን ያለው በመሆኑ፣ የድጋፉ መቋረጥ በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ላይም ተፅፅኖው የጎላ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ከዕርዳታ ጋር የተያያዙ ድርጅቶች ተጠቃሚነታቸው መቀዛቀዝ ሆቴሎች ያገኙት የነበረው የውጭ ምንዛሪ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡ ብዙዎቹ ድርጅቶች የአገልግሎት ክፍያዎቻቸውን በውጭ ምንዛሪ የሚከፍሉ መሆኑም፣ ከዚህ ይገኝ የነበረውን ጥቅም ሊያስተጓጉል ይችላል ተብሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደ አገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ ባለሙያዎችና ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ድርጅቶች ግለሰቦች በዕርዳታው መስተጓጉል ያገኙ የነበረው ገቢ እንዳሳጣቸው አክለዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መቋረጥ አገልግሎት የሚያቀርቡ ቢዝነሶች ላይ ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን አክለዋል፡፡

በመሆኑም የብዙ ሆቴሎች ትልቅ ገበያ ሆኖ የቆየው የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መቋረጥ ኢንዱስትሪው ላይ ሊኖረው የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለው መሆኑን ፍትሕ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡