
ኪንና ባህል የሁለገቡ የባህል ሙዚቀኛና መምህር ዓለማየሁ ፋንታ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል
ቀን: March 12, 2025
በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ ያላቸው ከያኒና መምህር ዓለማየሁ ፋንታ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ፒያሳ በሚገኘው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በዘጠኝ ሰዓት ይፈጸማል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ እንዳስታወቀው፣ የማሲንቆና የበገና ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎችን የተካኑት አቶ ዓለማየሁ ፋንታ፣ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለበርካታ ዓመታት በማስተማር ድንቅ ችሎታቸውንና ዕውቀታቸውን ለተማሪዎች አካፍለዋል፡፡
‹‹ማሲንቆን ሲጫወቱ ያሳዩት በነበረው ልዩ የአዘፋፈን ስልት ታዋቂ ነበሩ፤›› ያለው ዩኒቨርሲቲው፣ አቶ ዓለማየሁ በዓለም ዙሪያ በመዞር የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ በማስተዋወቅ ተጠቃሽ ናቸው ብሏል፡፡
ከሥርዓተ ቀብሩ በፊት ነፍስ ኄር ዓለማየሁ፣ ባስተማሩበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት የሽኝት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
በመዲናና በዘለሰኛ ስልት ገናን የነበሩት ዓለማየሁ ፋንታ ከሚጫወቱባቸው መሣሪያዎች መካከል ማሲንቆ፣ ክራር፣ በገና እና ዋሽንት ይጠቀሳሉ፡፡ ሽለላና ፉከራንም መካናቸው ይታወቃል፡፡
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት መጋቢት 1 ቀን ያረፉት አቶ ዓለማየሁ ፋንታ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡