ልናገር ዓድዋና አቪዬሽን በባለሙያ ዕይታ

አንባቢ

ቀን: March 12, 2025

በዮናታን መንክር

ከሦስት ዓመታት በፊት ከአንድ ትልቅ የታሪክ ምሁር ጋር ስናወራ፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ከዓድዋ ቀጥሎ ትልቁ ታሪካችን የአቪዬሽን ታሪካችን ነው በሚለው ተስማምተናል፡፡ ብዙ ሰው የኢትዮጵያን አቪዬሽን የሩቅና የቅንጦት ታሪክ አድርጎ ያየዋል፡፡ ነገር ግን በሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ የአቪዬሽን ተፅዕኖ አለ፡፡ ወደ ዓድዋ እንመለስ፡፡

በዘመነ ዓድዋ ቅኝ ገዥ አገሮች የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አልነበራቸውም፣ ለቅኝ አገዛዝ የሚጠቀሙት ሁለት ዋና አቅሞች ነበሯቸው፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ያበለፀጉት የኢንዱስትሪ አብዮት ትሩፋት የሆነው ዘመናዊ የጦር መሣርያና የአፍሪካውያን የበዛና ተከፋፈለ የጎሳ አኗኗር ነው፡፡ በዚህም በቀላሉ አንዱን ጎሳ በሌላኛው እንዲነሳ በጥቅምና በሥልጣን በማጓጓት፣ የአገሩን አንድነት በጣጥሶ በቀላሉ መግባትና መግዛት፡፡

ኢትዮጵያም በበርሊኑ ኮንፈረንስ በኋላ ላልታደለው ጣሊያን ዕጣ ወጥቶለት ሲመጣ ያገኘው ሕዝብ ጥቁር ከመሆኑና በአፍሪካ ከመገኘቱ በቀር፣ ዋጋ የሚያስከፍለው ሕዝብ መሆኑን አልተረዳም ነበር፡፡ ይኼ ሕዝብ በሃይማኖቱ፣ በባህሉ፣ በሥርዓተ መንግሥት ግንባታና በአርበኝነት ስሜቱ የረጅም ዘመናት የቆየ ልማድና ታሪክ የነበረው ነው፡፡ በእርግጥ ጣሊያንን የሚያህል የተደራጀ የጦር መሣርያና በከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሚመራ የሠለጠነ ሠራዊት፣ በመርከብ ስንቅና ትጥቁን በቅርብ ርቀት በገፍ ከሚያገኝ ኃይል ጋር ተዋግቶ ለማሸነፍ የኢትዮጵያውያን የዚያን ጊዜ የጦር አቅምና አርበኝነት የዓድዋን ጦርነት በአንድ ቀን ለማሸነፍ ብቻውን በቂ እንዳልነበር ይታመናል፡፡

ጣሊያን ከሌሎች ቅኝ ገዥ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዕድለ ቢስ ያደረገው ዋናው ነገር፣ በጊዜው በአገር ምሥረታ ላይ የነበሩት አፃ ምኒልክ በመላው የአገሪቱ ክፍል፣ በቅራኔና በጦርነት ጭምር ያኮረፏቸውንም የሚዋጓቸውንም ሁሉ በጋራ፣ በአንድነት እንዲቆሙና ወራሪውን የቅኝ ገዥ ኃይል እንዲዋጉ ያስቻሉበት ጥበብ ነው፡፡ ምናልባት ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ ዓይነት ንጉሥ ቢኖራቸው ኖሮ፣ በአንድነትና በአርበኝነት ተዋግተው ወራሪዎቻቸውን በመለሱ፣ አፍሪካም ከዛሬው የቅኝ አገዛዝ ቅሪት የድንበርና የኢኮኖሚ ዳፋ ተላቃ በኖረች ነበር፡፡

ይህ እንግዲህ አቪዬሽን የሚባል ቴክኖሎጂ ባልነበረበትና ጦርነት በምድር አሠላለፍ በሚወሰንበት ዘመን ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ንጉሡም ዕድለኛ ነበሩ ማለት  ይቻላል፡፡

ጣሊያን ከዓድዋው ሽንፈት በኋላ በአውሮፓውያን አገሮች ዘንድ የደረሰበት ንቀት ለከፍተኛ ቁጭትና እልህ አነሳሳው፡፡ በዚህ ጊዜ የራይት ወንድማማቾች የጀመሩት የአውፕላን ቴክኖሎጂ በብርሃን ፍጥነት በመላው አሜሪካና አውሮፓ እያደገ ቢሄድም፣ የመጀመሪያው የአውሮፕላን ዋና ጥቅም የአየር ኃይል በመገንባት የአየር የበላይነትን መቆጣጠር ሆኖ፣ አገሮች የአየር የበላይነት ፉክክራቸውንና አቅማቸውን መሞከሪያ ያደረጉት በመጀመርያው የዓለም ጦርነት ነበር፡፡ ጣሊያን በአውሮፓ እንደ መገኘቷ የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የመሆን ዕድሏን በሚገባ ተጠቀመችበት፡፡ ኢትዮጵያ ግን ብቻዋን በነፃነት ማግሥት በምትገኝበት አፍሪካ አኅጉር ይህን ቴክኖሎጂ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ማግኘት ሳትችል ቀርታ፣ በሽንፈት በዓለም ያሸማቀቀቻት ጣሊያን ለሁለተኛ ወረራ በላቀ የአየር የበላይነት እየተዘጋጀች ነበር፡፡

ከአፄ ምኒልክ ሕልፈት በኋላ በዋነኝነት በሸዋና በበጌምድር (ጎንደር) መሳፍንትና መኳንንት መካከል በነበረው የሥልጣን ሽኩቻና ባልረጋው ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የባከኑት ዓመታት፣ ለኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ወሳኝ የዕድገት ዕድሎች ያመለጡበትና ለጥቃት ተጋላጭነቷ የጨመረበት ዘመን ነበር፡፡

በዚህ ባልረጋውና በሚናጠው ዘመን ውስጥም ቢሆን፣ በኋላ በንጉሠ ነገሥትነት የዳግም ወረራውን ዳፋ የሚቀበሉት አፄ ኃይለ ሥላሴ በአልጋ ወራሽነት ጊዜያቸው አውሮፓን ሲጎበኙ ካስተዋሏቸው ነገሮች አንዱ፣ የአቪዬሽን ዕድገትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የኃይል ሚዛን መዛባት ነበር፡፡ በአገር ውስጥ የሥልጣን ጉዞአቸውን በከፍተኛ ትግልና ብልኃት እየተጓዙ፣ በውጭ ጉዞአቸው ደግሞ እንደምን ይህን ወሳኝ የሆነ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንደሚችሉ ሲያስቡ ቆዩ፣ ከዚያም በወቅቱ ባየር በሚባል ኩባንያ አማካይነት የመጀመሪያዎቹን የሚገጣጠሙ አውሮፕላኖች በድሬዳዋ በኩል ለማስገባት ያደረጉት ጥረት በጉምሩክ ባለሥልጣናት ጥያቄና ተቃውሞ ቀርቦበት እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ባልተቋረጠ ጥረታቸው ከብዙ ፈተናዎች በኋላና የንጉሥነት ሥልጣናቸው የፈጠረላቸውን አቅም ተጠቅመው የመጀመሪያው አውሮፕላን ገፈርሳ ካረፈበት ነሐሴ 21 ቀን 1921 ዓ.ም. ጊዜ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያን አቪዬሽን በተለይም የአየር ኃይል አቅምን ለማሳደግ የተደረጉት ጥረቶች በታሪክ ወደር የሌላቸውና የኢትዮጵያ አቪዬሽን መሠረት የተጣለባቸው ክስተቶች ነበሩ፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ከምርኮ ከሄደችበት ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰቸው ፀሐይ ኢትዮጵያ 1 አውሮፕላን፣ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዕድገት ጥልቅ ጉጉት፣ ጥረትና ሩጫ ዋና ምልክት ናት፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ የዓለምን ፖለቲካዊ ሁኔታ በጣም በቅርበት በመከታተልና ጣሊያን ኢትዮጵያን ደግማ ለመውረር ያላትን ሐሳብም ጭምር ተረድተው፣ ይህም እንደ ከዚህ ቀደሙ የዓድዋ ጦርነት አርበኝበትና አንድነት ብቻውን የማይመክተው እንደሆነ ተረድተው አውሮፕላኖችን ከስዊድን፣ ከጀርመን፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሣይ አገሮች ለመግዛት ያደረጓቸው ጥረቶች እንዳሰቡት ሳይሳኩ ቀሩ፡፡ ይህም የሆነው በተለይ እንግሊዝና ፈረንሣይ፣ የጣሊያኑ ሙሶሎኒ ከጀርመኑ ሂትለር ጋር የመሠረተው የፋሺዝምና የናዚዝም ጋብቻ መላው አውሮፓን ያሠጋና የ2ኛው የዓለም ጦርነት አይቀሬነት እየተነገረ በነበረበት ጊዜ በመሆኑ፣ ጣሊያንን በመፍራትና ላለማስቀየም በመሥጋት ለኢትዮጵያ አውሮፕላን ለመሸጥ ሳይፈልጉ በመቅረታቸው ነበር፡፡   

ይህም ሆኖ የኢትዮጵያን አቪዬሽን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት በብርቱ ቀጥሎ ገና ከጅምሩ በ1920 ዎቹ መጀመርያና አጋማሽ ከጀርመን፣ ከስዊድን፣ ከፈረንሣይና ከአሜሪካ አብራሪዎችንና ሜካኒኮችን በማስመጣት ኢትዮጵያውያን አብራሪዎችንና ሜካኒኮችን እንዲያሠለጥኑ በማድረግ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳዎችን በመሥራት በሚቻለው አቅም ሁሉ ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆየ፡፡ አብዛኛው ሕዝቧ መኪና እንኳን በቅጡ በማያውቅባት ኢትዮጵያ፣ የዘመኑን የአቪዬሽን ዕድገት ውድድር ወደፊት አሻግሮ በማየት ባለ በሌለ አቅሟ ገባችበት፡፡

አባቶች ‹‹አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም››፣ ‹‹አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ›› አይሆንም እንደሚሉት፣ መላው አፍሪካ በቅኝ አገዛዝና በከፋ ጭቆና ውስጥ ተይዞ በነበረበት አኅጉር ውስጥ ለሥልጣኔና ቴክኖሎጂ የምታደርገው ጉዞ የብቸኝነት ሆነባት፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ሁሉ ከባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ብትገኝም፣ ከአውሮፓዊቷ ጣሊያን ጋር ሊወዳደር የሚችል የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ለመገንባት ባትታደልም፣ ከዳግም ወረራው በኋላ እንደ እርሾ ሆኖ ያገለገላትን የአቪዬሽን መሠረት ግን ለመጣል ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ በወቅቱ ከነበረው ዓለም አቀፍ የጦርነት ሥጋት፣ ውጥረትና በአፍሪካም መላው የአኅጉሩ አገሮች በወደቁበት የቅኝ አገዛዝ ቀንበር የተነሳ፣ የብቸኝነትና የመገለል ዕድሏን ሙሶሎኒ ሊጠቀምበት ተነሳ፡፡ ማንንም ቆሞ የማይጠብቀው ጊዜ በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ የብቸኝነት ጉዞና በአውሮፓ አኅጉር ውስጥ በምትገኘው የጣሊያን የቴክኖሎጂ ግስጋሴ በ1928 ዓ.ም. የዳግም ወረራው ዝግጅት ተጠናቆ፣ ኢትዮጵያን በምድር ጦርነት ሊቋቋማት ያልቻለው የጣሊያን ጦር በአየር መጣባት፡፡ የወቅቱ መዛግብት እንደሚያስረዱት ጣሊያን በዳግም ወረራው፣ በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ወደ 450 የሚሆኑ የተከለከሉ የመርዝ ጋዝና ቦምብ ጣይ፣ የቅኝት፣ መትረየስ ተኳሽና ለተለያዩ የጦርነት ዓላማዎች የሚውሉ አውሮፕላኖችን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አዘነበ፡፡

ለአገሩ ነፃነትና አንድነት ግንባርና ደረቱን ለጥይት ለመስጠት የማይሳሳው የኢትዮጵያ አርበኛ ከላይ የሚዘንብበትን የመርዝ ጋዝ፣ ቦምብና መትረየስ በዓድዋ ጦርነት በማረካቸውና ከዚያ በኋላ በተገዙ መሣሪያዎች ብቻ ሊቋቋም የሚችልበት ተፈጥሯዊ አቅም ስላልነበረው፣ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደረሰ፡፡ የኋላ ኋላም ንጉሠ ነገሥቱ አገር ጥለው እንዲሰደዱ፣ አገርም 40 ዓመት በአውሮፓ የሥልጣኔ ዕድገት ዕድሉን አግኝቶ ለበቀል ሲዘጋጅ በቆየው የጣሊያን ጦር በዋነኝነት የአየር ኃይሉ ውጊያ አማካይነት ኢትዮጵያ ዳግም ተመልሶ ሊገባ ቻለ፡፡

በዓድዋ ጦርነት እንኳንስ ወደ መናገሻዋ ከተማ አዲስ አበባ ሊደርስ ቀርቶ፣ ከኤርትራ ድንበር ወንዝና ተራሮችን መሻገር ያልቻለው የጣሊያን ጦር፣ እንኳንስ ለዓመታት በዘለቀ ጦርነት ብዙ ኪሳራ ለማድረስ ይቅርና 24 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ሙትና ቁስለኛ ምርኮኞቹን በያሉበት በትኖ የተሸነፈው ጣሊያን፣ በአየር የበላይነቱ ምክንያት በአንድ ጊዜ ብዙ የአገሪቱ ክፍሎች እየደረሰ በአጭር ጊዜ መናገሻ ከተማዋንም ተቆጣጥሮ፣ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የማያቋርጥ ግፍና በደሉን በኢትዮጵያውያን ላይ በጭካኔ በትር ማሳረፍ ቻለ፡፡

ዋናው ጉዳያችን አቪዬሽን ገና ከጅምሩ ምን ያህል ከነፃነት ትግላችንና ከሉዓላዊነታችን ጋር እንደ ተቆራኘ ለማሳየት እንጂ፣ አሠርት ባለ ሺሕ ገጾች መጽሐፍት የማይበቁትን የአምስት ዓመት የአርበኞች የነፃነት ተጋድሎና የንጉሠ ነገሥቱን የዲፕሎማሲ ብርቱ ተጋድሎ ማውሳት ባለመሆኑ፣ ሌላኛውን የኢትዮጵያውያን የነፃነት ተጋድሎ በአጭር ጽሑፍ ለመግለጽ ከመሞከር ድፍረት በመቆጠብ በአጭሩ የዛሬውን የኢትዮጵያ አየር ኃይልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያዋለደውን ለሉዓላዊነት፣ ለነፃነትና ራስን ለመቻል የነበረ አገራዊ ቁጭት ውቅያኖስን በጭልፋ በሆነ ልክና መጠን እንመልከት፡፡ 

በዳግም ወረራው ወቅት ከአገር የተሰደዱት ንጉሠ ነገሥት የፋሺስት ጣሊያን ጦር በሕዝባቸው ላይ እያደረሰ ስላለው ግፍና መከራ ጄኔቭ በሚገኘው የመንግሥታቱ ማኅበር አቤቱታቸውን ሊያሰሙ ቢቀርቡም፣ መላው አውሮፓ በሙሶሎኒና በሂትለር ጥምረት መጨረሻው ባልታወቀው የወረራና የጦርነት ሥጋት ውስጥ ስለነበር፣ የአንድ አፍሪካዊ አገር ለዚያውም በዓድዋ የነጭን የቅኝ አገዛዝ ፍላጎት ለሰባበረና ድል ላደረገ አገር ጆሮውን ሊሰጥ የፈለገ አገር አልነበረም፡፡ የንጉሡም ንግግር በፕሮቶኮል ደንቡ መሠረት ቀረበ እንጂ ብዙም ምላሽ ሊሰጠው የፈለገ አገር ተወካይ አልነበረም፡፡ ይሁንና ንጉሡ በታሪክ የነብይ ያህል ያስቆጠራቸውን ንግግር አደረጉ፡፡ ይኸውም የመንግሥታቱ ማኅበር አባል በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የጣሊያን መንግሥት የሚያደርሰውን ግፍና ወረራ ለማቆም ፍላጎት አለመኖሩ ቢያሳዝናቸውም፣ ይህ ሁኔታ ዛሬ በእኛ ነገ ደግሞ በእናንተ ይሆናል የሚል የትንቢት ዓይነት ንግግር አደረጉ፡፡ እንዳሉትም ከሦስት ዓመት በኋላ የበርሊንና የሮም ጥምረት (Berlin-Rome Axis) መላውን አውሮፓ የመውረር እንቅስቃሴያቸውን በመጀመራቸው፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጀምሮ እስያንና አሜሪካን ጨምሮ ውጊያው በአውሮፓ ምድር ለአምስት ዓመታት ያህል ተደርጎ በአሠርት ሚሊዮን የሚቆጠሩ አውሮፓውያን በጦርነቱ አልቀው፣ አውሮፓም ወደ ፍርስራሽነት ተቀየረች፡፡ ኔትፍሊክስ የ22ኛውን የዓለም ጦርነት አስመልክቶ በሠራው ተከታታይ ዶክመንተሪም፣ ንጉሠ ነገሥቱን በመንግሥታቱ ማኅበር ያደረጉት ንግግር በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ውስጥ ጉልህ ክስተት እንደነበረ፣ በተለይም በወቅቱ የአውሮፓ መንግሥታትና የዓለም አገሮች የንጉሡን ማስጠንቀቂያ ሰምተውና ምላሽ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ፣ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ሊያስቀሩ ከሚችሉ ዕድሎች አንዱ አድርጎ በስፋት አቅርቦታል፡፡   

የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በተባበሩት ኃይሎች (Allied Forces) ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ፣ ቀደም ብላ ኢትዮጵያ በንጉሡ በኩል በስደት ከኖሩባት እንግሊዝ ጋር በነበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የእንግሊዝ ንጉሣዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያው ንጉሣዊ ሥርዓት ካለው አክብሮት ይሁን ወገንተኝነት የተነሳ፣ የእንግሊዝ ጦር በአገር ውስጥ በቆራጥነትና በጀብደኝነት የጣሊያንን ሥርዓት ዕረፍት ነስተውና አሾህና አሜኬላ ሆነው፣ ኢትዮጵያን ከዳግም ቅኝ አገዛዝ ሙከራው ያሰናከሉትን አርበኞች በማገዝ፣ ጣሊያን ዳግም ሽንፈቱን ውጦ ከኢትዮጵያ ሲባረር ከወረራው በፊት የኢትዮጵያን አቪዬሽን ለማሳደግ በነበረው ጥረት ፋና ወጊ የነበረችውን ፀሐይ አውሮፕላንም ጭምር ዘርፎ ወደ አገሩ መውሰዱን ልብ ይሏል፡፡

ምንም እንኳን የፋሺስቱ ጣሊያን ጦር በኢትዮጵያውያን አርበኞች መሪ ትግልና በእንግሊዝ ጦር ዕገዛ ተሸንፎ ከአገር ቢወጣም፣ በጦርነቱ ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ሠራዊት ቢገባም፣ ንጉሠ ነገሥቱም ተስፋ አድርገው የነበረውን ሙሉ ነፃነትና አስተዳደራዊ ገለልተኝነት ከእንግሊዞቹ በኩል ባለማግኘታቸው እንኳንስ በአቪዬሽን በኩል የጀመሩትን ጥረት፣ መሠረታዊ የሆኑ የአገር መሪ ኃላፊነቶቻቸውንና ሚናቸውንም ለመወጣት አልቻሉም ነበር፡፡

እንደ ሁልጊዜውም ለፈተናዎቻቸው ሁሉ መላና ብልኃትን የዲፕሎማሲ አቅምን በመጠቀም የሚያምኑት ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በወቅቱ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ፣ መላው አውሮፓ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት በነበረበት ሰዓት፣ በብቸኝነት ልዕለ ኃያል ሆና ከወጣችው አሜሪካን ጋር ግንኙነት በመመሥረት፣ እንግሊዝ ልትጋፋው ከማትችላት አሜሪካ ጋር በአቪዬሽን መስክ ለመሥራት ጥሪ አቀረቡ፡፡ ይህም የዛሬውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መወለድ አበሰረ፡፡ በዚህም የንግድ ስምምነት በወቅቱ የአሜሪካ ትልቁ አየር መንገድ ከነበረው “Trans World Airlines” (TWA) ጋር አየር መንገዱን የመመሥረትና ለጥቂት ጊዜ በአሜሪካውያን እየተዳደረ፣ በኋላ አየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን እንዲመራና የሚያስችለውን  “Ethiopianization” የተባለ ዝነኛና ቁልፍ የሆነ ፕሮግራም ተቀርፆ፣ ሥራው በቅልጥፍና የንጉሠ ነገሥቱም በጣም የቅርብ ክትትል ተደርጎበት ቀጠለ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ. በ1945 ዓ.ም. ተመሥርቶ፣ የመጀመርያ በረራውን ባደረገበት 1946 ዓ.ም. ከመላው አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ነፃነቷን አግኝታ የነበረችው ግብፅ ብቻ በመሆኗ፣ የመጀመርያ የውጭ አገር በረራው ካይሮ ለመሆን  ቻለ፡፡ እንግዲህ፣ ከምሥረታው ጀምሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በአውሮላኖቹ ጭራ ላይ አድርጎ በ1950ዎቹና 1960ዎቹ መዳረሻዎቹን በአፍሪካና አውሮፓ አድርጎ ሲበር፣ ከማንም በላይ የኢትዮጵያን ነፃነትና ታሪክ ለዓለም በማስተዋወቅ በኩል የተጫወተው ሚና እንደ አንድ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ሳይሆን፣ በሚበርባቸው መዳረሻዎች ሁሉ የዲፕሎማሲ ልዑካን ይዞ እንደሚበር የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አምባሳደር ነበር፡፡

እዚህ ላይ በታሪክ ወደኋላ ተጉዞ ማስታወስ የሚገቡና ራስን በዚያ ዘመን ላይ አስቀምጦ በማየት የዚህን አጭር ጽሑፍ ዋና መንፈስ ለመረዳት የሚያስችሉ ጥቂት የታሪክ አንኳሮችን ማየት ገቢ ይሆናል፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋቋመበት ዓመት እ.ኤ.አ. 1945 ማለት፣ በመላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ ከፍተኛ የሰው እልቂትና አገሮችን ወደ ፍርስራሽነት የቀየረው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበትና ዓለም በአሸናፊዎቹ ኃይሎች የርዕዮተ ዓለማት ካምፖች በሁለት ለመከፈል የምትንደረደርበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህም ለየትኛውም አገር ወዳጅን ለመምረጥ፣ የኢኮኖሚ ዕገዛ ለማግኘት እጅግ ፈታኝ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ራሳቸውን በአሜሪካ የማርሻል ፕላን የገንዘብ ድጋፍ ለማዳን የሚሞክሩት አውሮፓውያን እንኳንስ ለሌላ አገር ለራሳቸውም መሆን የማይችሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ወረራ በማድረግ የግፍ ቀንበሯን የጫነችባት ጣሊያንም፣ ከተሸናፊዎቹ ወገን በመሆኗ የደቀቀ አኮኖሚዋንና የፈራረሱ ከተሞቿን ይዛ የምታነክስበት ጊዜ ነበር፡፡

አፍሪካ ቀደም ብለን እንዳነሳነው አየር መንገዱ በተመሠረተበት ጊዜ ከግብፅ በስተቀር በቅኝ አገዛዝ ውስጥ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ በከፋ ጭቆናና ድህነት ውስጥ የነበረችበት ወቅት ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ዓመት ላይ ነው በኢትዮጵያ አሁን በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለውንና በዓለም አቀፍ ስመጥር የሆነውን ግዙፍ አየር መንገድ ለማቋቋም የቻለችው፡፡ ይህ ምሥረታ ዘመናትን ተሻግሮና የአየር መንገድን ጥቅም ተረድቶ፣ በፅኑ መሠረት ላይ የማቆምን የአመራር ጥበብ ብቻ ሳይሆን፣ ከዓድዋ በተወረሰ በራስ የመተማመን ፅኑ መንፈስ የተነሳሳ፣ ኢትዮጵያናይዜሽን የሚባል ፕሮግራም ተቀርፆ ከጅምሩ ኢትዮጵያውያንን ለማብቃት ከፍተኛ ሥራ ለመሥራት በመቻሉ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ አየር መንገዶችን አቋቁመው፣ የውጭ አገሮች ዜጎችን በመሪነት ቀጥረው የሚያሠሩ የአፍሪካ አገሮችና እንደ ኤምሬትስና ኢትሀድ፣ እንዲሁም በቅርቡ የዓለም ትልቁ አየር መንገድ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን የሪያድ አየር መንገድ ጨምሮ ብዙ የዓለም ባለደረጃ አየር መንገዶች መሪዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎቻቸውና የአቪዬሽን ባለሙያዎቻቸው የውጭ አገሮች ዜጎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ሲታሰብ እንችላለን የሚለውና ከአውሮፓውያንና ከአሜሪካውያን በታች አድርጎ ራስን የማሰብ መንፈስ በዓድዋ ባይረጋገጥ ኖሮ፣ ዛሬ አየር መንገዱን በፅኑ መሠረት ላይ የመሠረተውና ለስኬቶቹም ሁሉ ቁልፍ የሆነው በራስ ዜጋ፣ በውስጥ አቅም የመሥራት ጅማሮ የሆነው የኢትዮጵያናይዜሽን ፕሮግራም ባልኖረ ነበር፡፡

ምንም እንኳን በሌሎች ብዙ ጎዳናዎች፣ ጠንክረን በመሥራት፣ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት በመገንባትና ሰላምን በማፅናት፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብዙ አሠርት ዓመታትን በጦርነቶችና ባለመረጋጋት የማሳለፋችን ታሪክ የሚያስቆጭና አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ይሁንና የዚህ ጽሑፍ ርዕስ በሆነው የነፃነትና የድል መንፈስ ዓድዋ በሰጠን አገራዊ ክብርና ማንነት የተነሳ አገሮች እንደ ነፃ፣ ባለድል፣ ባለታሪክና ሉዓላዊ አገር ቆጥረውን በዚያን ዘመን አብረውን በሠሩበት የአቪዬሽን ታሪካችን፣ በተለይም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ምሥረታና ረዥም ጉዞ ያየነውን ዕድገት ብቻ ሳይሆን የታሪክ ግጥምጥሞሽ ብናይ፣ በዳግም ወረራው አገራችንን ብዙ ዋጋ ያስከፈለቻትና የጊዜዋ ኃያል አገር ጣሊያን ብሔራዊ አየር መንገድ የነበረው አሊታልያ የተባለው አየር መንገድ፣ በኪሳራ ተዘግቶ ስሙ ተረስቷል፡፡ ያቺ ለአቤቱታዋ ከመንግሥታት ኅብረት ምላስም፣ ዋስትናም አጥታ በብቸኝነት የታገለችው ኢትዮጵያ ግን፣ ዛሬ ወደ ሮም ብቻ በየቀኑ ወደ ሰባት በረራዎችን የሚያደርግና በየቀኑ ወደ ሚላን የሚበር አየር መንገድ ያላት አገር  ሆናለች፡፡

ጽሐፌን ዓለም በብዙ ያደነቃቸው፣ ያከበራቸውና የአፍሪካ የነፃነት ምሳሌ የሆነችው የደቡብ አፍሪካው የነፃነት ታጋይና የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ‹‹Long Walk To Freedom›› በተባለው ግለ ታሪካቸው ላይ ይኸው የባለ ድልና የነፃነት ምልክት የነበረው አየር መንገድ በራሱ አብራሪ አገልግሎት በሚሰጥበት በአንዱ ቀን፣ በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ ለአፍሪካውያን የነፃነት ታጋዮች ያደትርጉ በነበረው ስብሰባ ለመሳተፍ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲበር የተሰማውን ጽሑፍ በማጋራት ልቋጭ፡፡ ይህ አየር መንገድ ማለት አፍሪካውያን በቅርብ ዘመን ታሪካቸው፣ እንደ ነፃነት ታጋይና የዴሞክራሲ ምልክት አድርገው የሚያዩትንም ሰው፣ በጥቁሮች ችሎታ እንዲያምን ያስቻለውን ልዩ አጋጣሚ፣ መደበኛ ሥራውን በመሥራት ላይ በነበረ ኢትዮጵያዊ አብራሪ ምክንያት ለመፍጠር የቻለ የነፃነት መንፈስ ነው፡፡ የዛሬው የአየር መንገዱም መጠሪያ የአዲሲቷ አፍሪካ መንፈስ ‹‹The New Spirit of Africa›› መባሉ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ሚናውንም የሚያስታውስ ነው፡፡

“We put down briefly in Khartoum, where we changed to an Ethiopian Airways flight to Addis. Here I experienced a rather strange sensation. As I was boarding the plane, I saw that the pilot was black. I had never seen a black pilot before, and the instant I did I had to quell my panic. How could a black man fly an airplane? But a moment later I caught myself: I had fallen into the apartheid mind-set, thinking Africans were inferior and that flying was a white man’s job. I sat back in my seat and chided myself for such thoughts. Once we were in the air, I lost my nervousness and studied the geography of Ethiopia.”

Long Walk to Freedom (Nelson Mandela,1994)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ጸሐፊና አብራሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው yonathan@menkir.com ማግኘት ይቻላል፡፡