

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ
March 12, 2025
ኤርትራና ኢትዮጵያ በጦርነት ሥጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ጦርነቱ በማንኛውም ሰዓትና ቦታ ሊጀመር እንደሚችል ግምቶች ከየአቅጣጫው እየተሰጡ ነው፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የአልጄዚራ ጽሑፍ ኤርትራን ክፉኛ መወንጀሉ ሁኔታውን ግልጽ ያወጣ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለትግራይ ልሂቃን መልዕክት፣ እንዲሁም ለየካቲት 11 በዓል ብለው የላኳቸው ሁለት ደብዳቤዎች ኢትዮጵያ በውጭ ብቻ ሳይሆን በውስጥም የግጭት ሥጋት ያየለባት መሆኗን አመልካች ጉዳይ ተደርገው ሲቀርቡ ሰንብተዋል፡፡ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሩ የአብረሃም በላይ (ዶ/ር) መግለጫ ደግሞ ይህን በሰሜን ኢትዮጵያ ቀጣና የተፈጠረ ትኩሳት ምንነት የበለጠ ግልጽ ሲያወጣው ተስተውሏል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ለቀይ ባህር በር ባለቤትነት መከላከያው እንደሚተጋ መናገራቸውም ምን እየተደገሰ ነው ያሰኘ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከተለዋዋጩ ቀጣናዊ ጂኦ ፖለቲካ ጋር አብሮ የሚሄድ የጦር ዝግጅት የማድረግ አስፈላጊነት ንግግር የበለጠ ጉዳዩን አጠነከረው፡፡ ከእነዚህ እኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት ሚዲያዎች የሚወጡ ዘገባዎች አንድምታ በቀይ ባህር፣ በባህር በር፣ በሰሜን ኢትዮጵያና በኤርትራ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ደግሞ የነገሩን አዝማሚያ አመልካች ተደርገው ነው የተወሰዱት፡፡ በመጀመሪያ የባህር በር ቀጥሎ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ የመግባቢያ ስምምነት ጉዳዮች ነበሩ ዋናዎቹ አጀንዳዎች፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ከሶማሊያ ጋር የፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ አጀንዳ ቀጥሎ ዋና ማጠንጠኛ ሆነ፡፡ በሒደት የአንካራ ስምምነት ቦታውን ቢረከብም አሁን ደግሞ የባህር በር፣ የቀይ ባህር፣ የአሰብ ወደብና ኤርትራ የሚሉ ጉዳዮች የአጀንዳ ዝርዝሩ ላይ ጎላ ብለው የሠፈሩ ይመስላል፡፡
ይህ ሁሉ በፍጥነት እየተለዋወጠ ሲከሰት የታየ ሁነት ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት መደረጉ አይቀሬ ነው የሚለውን መላምት በጉልህ አጠናክሮታል፡፡ ይህን ደግሞ በርቀት ያሉ ታዛቢዎች ወይም የፖለቲካ ተንታኞች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖችም በተለያዩ መንገዶች እያረጋገጡት ይገኛል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና ያልተማከለ አስተዳደርና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል በማንኛውም ሰዓት ጦርነት ሊፈነዳ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዋና አዋጊና የዚያን ጊዜው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩት የጦር መኮንኑ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ “Tigray Cannot be the Battleground for Ethiopia and Eritrea” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ሰፊ ሀተታ፣ በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ እንደሚችልና ትግራይም የጦርነቱ ዓውድማ ልትሆን እንደምትችል አመላክተዋል፡፡
በትግራይ ጠንካራ የሆነ የሠለጠነና ልምድ ያለው ሠራዊት መኖሩን ጠቁመው፣ ይህን ኃይል አጋር ለማድረግ ሁለቱ መንግሥታት እንደሚመክሩ ገልጸዋል፡፡ ሕወሓትና የትግራይ ሠራዊት ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለማበር እንደሚፈልጉም በመጠቆም ትግራይን ከጨፈጨፈ ወገን ጋር ማበሩ እንደማያዋጣ ነው የተናገሩት፡፡
ትግራይን ጦር ሜዳ ሊያደርግ ይችላል ያሉት የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ ቀጣናዊ ግጭት ወደ መሆን በአንዴ እንደሚሸጋገር አመልክተው፣ መቼና እንዴት የሚያቆም እንደሆነ ግን እንደማይታወቅና ማባሪያ ላይኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ጦርነቱ የአገሮቹን ጂኦግራፊ ሊለውጥ ይችላል። ከአፍሪካ ቀንድና ከቀይ ባህር ባሻገርም ዓለም አቀፋዊ የጂኦ ፖለቲካ አሠላለፍ ለውጥ ይፈጥራል፤›› ሲሉም ነው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በጽሑፋቸው ያሠፈሩት፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ1990 ዓ.ም. ሊጀምር ሲል በዋዜማው ባድመን በመሳሰሉ የትግራይ መሬቶች ላይ ሊፈጸም የተቃረበው የሻዕቢያ ወረራ በቶሎ እንደሚጀምር፣ ግንባር ባሉ የጦር መኮንኖች የቀረበውን ምክርና ወረራውን ለመመከት ዝግጅት ይደረግ የሚል ውትወታ ቸል በማለት በቀድሞ ጓዶቻቸው ይወቀሳሉ፡፡ ራሳቸውም በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ባድመ ከመወረሩ አንድ ቀን ቀድሞ ከኤርትራ የጊዜው ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ስብሃት ኤፍሬም፣ ከደኅንነት ኃላፊው አብረሃ ካሳ፣ እንዲሁም ከደኅንነት አማካሪው የማነ ገብረ አብ ጋር የድንበር ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ እያደረጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህን እሳቸውም መዘናጋት እንደሆነ ቢገልጹትም፣ አንዳንዶች ግን ኤርትራ ኢትዮጵያን ስትወር ጎልፍ ክለብ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር ውስኪ እየተጎነጩ ነበር በሚል ሲተቿቸው ቆይተዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት በፆረና ግንባር በተከፈለው ውድ ዋጋ የሚተቿቸው ቢኖሩም፣ በሒደት ግን ኢትዮጵያ የባህር በር እስክታገኝ ጦርነቱን መቀጠል አለባት የሚል አቋም አንፀባርቀዋል ተብሎ ከአንዳንዶች ድጋፍ ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ይኸው አቋማቸውም ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር እንዳጋጫቸውና ከኃላፊነት እንዲለቁ መነሻ እንደሆነ ራሳቸውም ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ከብዙ ዓመታት የጡረታ ቆይታ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የትግራይ ኃይሎችን ከሚመሩ የጦር አዛዦች አንዱ ሆነው ራሳቸውን የከሰቱት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ አሁን ደግሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር በመሆን እየሠሩ ናቸው፡፡ የጦር መኮንኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ከተፈጠረው የጦርነት ሥጋት በተጨማሪ፣ በሱዳን ከባድ የሚባል ትኩስ ግጭት መቀጠሉ ትግራይን ብሎም ኢትዮጵያን በእሳት የተከበቡ እንዳደረጋቸው ነው ሰፊ ትንተና የሰጡት፡፡
ሌተና ጄኔራሉ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት መግባት አደጋው ከባድ ነው እያሉ ባሉበት ወቅት ደግሞ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ አቶ ጌታቸው ረዳም ይህንኑ ሥጋት የሚያጎላ መግለጫ አሰምተዋል፡፡ ‹‹ሁለቱ መንግሥታት የፈጠሩት ውጥረት ያሳስበናል፣ ያለ ፍላጎታችን ወደ ጦርነት እንዳንገባ ያሠጋኛል፡፡ በትግራይ በኩል እስካለፈው ነሐሴ ከኤርትራ ጋር እንገናኝ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ይኸው ግንኙነት ነበረ፡፡ ከእነ ወንጀሉም ቢሆን ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም እንዲፈጠር ፍላጎት አለኝ፣ ሆኖም በሁሉም አቅጣጫ የጦርነት ሥጋት ውስጥ ነን፤›› በማለት ነበር አቶ ጌታቸው የተናገሩት፡፡ ትግራይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ባለው ውጥረት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ክልሎች ጋር ያልተፈቱ ችግሮች ያላት መሆኑ ክልሉ ከቀውስ ገና ካለመላቀቁ አንፃር ሥጋት እንደሚያጭርባቸው ነው ያስረዱት፡፡
አቶ ጌታቸው ከክልሉ ውጪ ባለ ተፅዕኖ ጦርነት ሊከሰት የመቻሉን ዕድል ቢናገሩም በወቅቱ ግን በትግራይ ክልል ውስጥ ከሕወሓት ክንፍ፣ እንዲሁም ከጦሩ አመራሮች ጋር ከረር ያለ ውጥረት ውስጥ መውደቃቸው የቆየና የተባባሰ ጉዳይ ሲሆን ነው የታየው፡፡ ከሰሞኑ ለምሳሌ የትግራይ ጦር የደቡብ ግንባር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዮሐንስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የምሥራቅ ግንባር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል መዓሾ በየነን፣ እንዲሁም ብርጋዴር ጄኔራል ምግበ ኃይለ አግደዋል፡፡ የትግራይ ጦር ኃይል ውስጥ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የማይታዘዙ መኮንኖች እንዳሉ በመጠቆም የጦሩ ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ዕርምጃ እንዲወስዱ አዘው ነበር፡፡ ሦስቱን የጦር መኮንኖች ከመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በጊዜያዊነት ከኃላፊነት ማገዳቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ መግባባት እስኪፈጠር ድረስ ውሳኔያቸው እንደሚፀናም ነው ሰኞ ዕለት ይፋ ያደረጉት፡፡
የፀጥታ ቢሮ ኃላፊው ጄኔራል ታደሰ ወረደም ቢሆኑ ከአቶ ጌታቸው ውሳኔ በተቃራኒ የቆሙ ሲሆን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችን መሾምና መሻሩን እንዲያቆም በይፋ ጠይቀዋል፡፡ በትግራይ ክልል አንዳንድ ሰዎች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ሌሎችን ከኃላፊነት ለማሰናበት እንደሚንቀሳቀሱ የጠቀሱት ጄኔራሉ፣ ይህ ነገር ቆሞ ችግሮች በሰላማዊ መፍትሕ በንግግር እንዲፈቱ ፍላጎታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ግን ከሰሞኑ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ቀውስ የሚፈታውና በጊዜያዊ አስተዳደሩና በሕወሓት መካከል ያለው ክልሉን የናጠ ክፍፍልና ፍትጊያ የሚቆመው፣ ሕወሓት ዳግም ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ ሕጋዊ አሠራሮችን በተከተለ መንገድ ምርጫ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
ልጃቸውንና የልጃቸውን አባት በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ማጣታቸውን፣ ‹‹ማንም የማያገኘው ሰማዕትነት ነው፡፡ በእኔ ላይ ብቻ የመጣ ሳይሆን በመላው ትግራይ ላይ የወረደ የጭካኔ በትር የጠየቀው መስዋዕትነት ነው፤›› በማለት ከሰሞኑ ሲናገሩ የተደመጡት የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)፣ በትግራይ ላይ ጦርነት ለማድረግ አንዳችም ምክንያት እንዳልነበረ ሲሞግቱ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹የፕሪቶሪያ ስምምነትን አንዳንድ ያልጠበቅናቸውና ያልገመትናቸው ጉዳዮችን ይዞ የተፈረመ ሰነድ ነው፤›› ያሉት ፈትለወርቅ፣ ካለው ጠቀሜታ አንፃር በሒደት እየታረመ ይሄዳል በሚል ወደ መቀበል እንደገቡ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ስምምነቱ በውስጣችን የተፈጠረውን ክፍፍል አልፈጠረውም፤›› ሲሉ የተደመጡት ፖለቲከኛዋ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስምምነቱን በትክክል ባለማስፈጸሙና የትግራይን ጥቅም ባለማስጠበቁ ነው ችግሩ የተፈጠረው ብለዋል፡፡ የእነሱ ተወካይ ከኤርትራ ተወካዮች ጋር መነጋገሩን የጠቆሙት ፈትለወርቅ፣ ይህም የሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በፌደራል መንግሥቱ ይሁንታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ያለፈ አልፏል ወደ ጦርነት ዳግም መግባት አንፈልግም የሚል አቋም በሕወሓትን በኤርትራም መካከል መንፀባረቁን ነው ያከሉት፡፡ የሕወሓት መሪ ደብረ ጽዮንም ቢሆን ይህንኑ የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራ አስፈላጊነት ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ አጠናክረውታል፡፡ በትግራይ ውስጥ ለተፈጠረው ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻ መፍትሔው የፕሪቶሪያ ስምምነትን ቃል በቃል መተግበር ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ሕወሓት ሰሜን ኢትዮጵያን ላካለለው ለትግራይ ጦርነት መፈንዳት መንስዔ ነው የሚለውን ጉዳይ የሕወሓት አመራሮች ሲቀበሉት አይሰማም፡፡ ኤርትራ በጦርነቱ እንድትገባ የጋበዘው ራሱ ሕወሓት ነው የሚለውንም አይቀበሉትም፡፡ ይህ ጦርነት በሚሊዮን ሰዎችን ማስፈጀቱን በማስታወስ ለዚህ ምን ያህል ኃላፊነት እንደሚወስዱ የተጠየቁት ወ/ሮ ፈትለወርቅ፣ ይህ ጥያቄ የሚነሳው አጥፊዎቹንና በትግራይ ላይ የዘመቱትን ነፃ ለማውጣት ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡
የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በትግራይ ለተፈጠሩ ቀውሶችና ችግሮች ራሱ ሕወሓትን ተጠያቂ ሲያደርጉት ይሰማል፡፡ ከሰሞኑ የጋራ መግለጫ ያወጡት ባይቶና፣ ውናት፣ እንዲሁም አረና ትግራይ ፓርቲዎች ሕወሓት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ለቀጠለው ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ ጭምር ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የፀጥታ ኃይሉ ለክልሉ መንግሥትና ሕዝብ የሰላም ዋስትና እንጂ አንዱን ቡድን ለሥልጣን ለማብቃት መሥራት የለበትም፤›› ሲሉ የገለጹት ፓርቲዎቹ፣ ሕወሓት ግን በፀጥታ ኃይሉ ታዝሎ የትግራይን ሥልጣን እንደለመደው ብቻውን ለመጠቅለል ይሞክራል ብለዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዕርምጃ ይውሰድ ዝምታውን ያቁም በማለት የጠየቁት ፓርቲዎቹ፣ የትግራይ ሕዝብ ከቀውስ እንዳይወጣና ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዳይመለስ ሕወሓትና የሚደግፉት የጦር መኮንኖች እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የትግራይ ውስጣዊ ቀውስና የፖለቲካ ሽኩቻ ባልሻረበት በዚህ ወቅት ደግሞ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ፍጥጫ ማየሉ ትግራይን ለከፋ የፀጥታ ሥጋት መዳረጉ ጎልቶ መደመጥ ጀምሯል፡፡ ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆነ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምትዋሰንባቸው ሁለቱ የአፋርና የትግራይ ክልሎች የጦር ዓውድማ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ ለአፋር ቡሬ ቅርብ በሆነው በአሰብ ወደብ በኩል ጦርነት ይቀሰቀሳል መባሉ ከሰሜን ኢትዮጵያው የጦርነት ተፅዕኖ ገና ያልተላቀቀውን የአፋር ክልል ተመልሶ የጦር ቀጣና ሊያደርገው እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሰብ ግንባር ውጊያ አይቀሬ ነው የሚል ግምት እየተሰማ ነው፡፡
የኤርትራ ባለሥልጣናት ለሳዑዲ ዓረቢያ ደብዳቤ መጻፋቸው፣ እንዲሁም አሰብን ባማከለ ጉዳይ ከሳዑዲ ጋር የቅርርብ ፍላጎት አላቸው ከመባሉ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያም በኤርትራም ያለው የጦር ዝግጅት ተጠናክሯል መባሉ አሰብ የሁለቱ አገሮች ጦርነት መነሻ መሆኑ አይቀሬ ነው የሚለውን ግምት አጠናክሮታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በትግራይ በኩልም ከኤርትራ ጋር ዳግም ወደ ጦርነት የሚገባበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እየተገመተ ነው፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሸመ (ዶ/ር) በአልጄዚራ ያስነበቡት ጽሑፍ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት መልክ የቀየረ ነበር፡፡ ኤርትራ የቀጣናው በጥባጭ ነች የሚለውን ውንጀላቸውን ሙላቱ (ዶ/ር) ለማጠናከር ኤርትራ እንደ ፋኖ ያሉ የአማራ ተቃዋሚ ቡድኖችን፣ እንዲሁም የሕወሓት ክፋዮችን በመደገፍና በማስታጠቅ ትንቀሳቀሳለች ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ሰላም ያመጣውን የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት እያደናቀፈችና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች ነው የሚል ክስም አሰምተዋል፡፡ ኤርትራ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች የተሟላ ሰላምና መረጋጋት እንዳይመጣ እያደረገች ነው ከማለት ጎን ለጎንም፣ ሌላ ዙር ጦርነት ሳይፈጠር ዓለም ሊያስታግሳት ይገባል ማለታቸው በኢትዮጵያ በኩል በኤርትራ ላይ የተያዘውን አቋም መክረር ያመላከተ ነው የሚሉ አሉ፡፡ መንግሥት ግን ጽሑፉ የእሳቸውን አቋም ያራምዳል ማለቱ አይዘነጋም፡፡ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀልም አፀፋ የሰጡ ሲሆን፣ ኤርትራ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጀምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ኢትዮጵያን መውቀስና መተቸት ከጀማመረች ሰንበትበት ማለቷም ይታወሳል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) መግለጫም ቢሆን፣ ኤርትራ የትግራይን መሬት ይዛለች ከያዘችው ቦታ ካልወጣችም ማስታገስ እንችላለን የሚል ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፋቸው፣ የሁለቱን አገሮች ግጭት አይቀሬነት አመልካች ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡ በትግራይ ውስጥም ቢሆን ከኤርትራ ጋር ለመወዳጀት የሚታይ ሽር ጉድ መኖሩን የጠቀሱት አብረሃም (ዶ/ር)፣ ለሚመጣው ነገር ኢትዮጵያ አፀፋ ለመስጠት እንደምትችል ጠጠር ያለ መግለጫ ነው የሰጡት፡፡
በትግራይ አቅጣጫም ይሁን በአፋር ቡሬ መስመር የሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት መግባት አንዴ ከፈነዳ በቀላሉ እንደማይገታ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡ አንጋፋው የሕወሓት መሥራችና የአረና ፓርቲ አመራር አቶ ገብሩ አሥራት ከቀናት በፊት ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ የሁለቱ አገሮች ግጭት በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ዘርፈ ብዙ ችግር፣ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ቀጣና ከተለወጠው የኃይል አሠላለፍ አንፃር በአንዴ እንደማያባራ ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩ ከአማራ ክልል ጦርነትና ከኦሮሚያ ክልሉ ግጭት ጋር ሁሉ የመያያዝ ዕድሉ የሰፋ መሆኑን ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡
ይሁን እንጂ ሌሎች ወገኖች ከዚህ በተቃራኒው ኤርትራን ማስተንፈስና ማስታገስ ያስፈልጋል የሚለውን ሐሳብ ሲጋሩ ነው የሚታየው፡፡ ለሪፖርተር ከዚህ ቀደም አስተያየታቸውን የሰጡት የኦነግ ከፍተኛ አመራርና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተካፈሉት ኮሎኔል ገመቹ አያና ከእነዚህ አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ደካማ ባይሆን ኖሮ ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት በሆነው በትግራይ ክልል ላይ ለፈጸማቸው ወንጀሎች አፍንጫውን ተመቶ ልኩን ማየት ነበረበት፤›› በማለት በቁጭት ተናግረው ነበር፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት ጌታቸው አሰፋ (ፕሮፌሰር) ጦርነትን በመሠረታዊነት እንደሚጠሉ ጠቅሰው፣ ሆኖም ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ከገቡ የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው እንዲዋጉ ነበር ያሳሰቡት፡፡ ‹‹ጥቂት የሕወሓት ሰዎች ከአስመራው ኃይል ጋር አንድነት ለመፍጠር አይሞክሩም ብዬ አላስብም፡፡ ከዚያ ሁሉ ዕልቂት በኋላ ማንም ይሁን ማንም ከአስመራ ኃይል ጋር የሚያብር የትግራይ ፖለቲካ ኃይል መጠየቅ አለበት፡፡ ይህን የሚያደርግ ኃይል በቃ ለሆነው ሁሉ ነገር ምንም ግድ አይሰጠኝም የሚልና ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ ነው፡፡ ሻዕቢያ እኮ አንዴ ከኳታር፣ ሌላ ጊዜ ከሳዑዲ፣ አንዴ ከኢራን፣ ከዓረብ ኤምሬቶች እየተሻረከ የመጣ ኃይል ነው፡፡ ያኔ አማራን በሚመለከት ሲያራምድ የቆየውን ፖለቲካ ትቶ ከአማራ ኃይሎች ዛሬ ጋር ተጣምሮ ይታያል፡፡ አሁን ደግሞ ትግራይ ውስጥ ካሉ የሕወሓት አንጃዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ይታያል፡፡ ሻዕቢያ የፈለገውን ቢሞክር ትግራይ ውስጥ ያን ሁሉ ወንጀሉንና ግፉን ረስቶ ግንባር ለመፍጠር የሚተባበር ኃይል ሊኖር አይገባም፡፡ በግሌ ምንም ዓይነት ጦርነት መፈጠር የለበትም ከሚሉት ወገኖች ውስጥ ነኝ፡፡ ነገር ግን ጦርነት አይቀሬ ከሆነ ከሻዕቢያ ጋር ከመተባበር ከኢትዮጵያ ጋር ቆሞ የአስመራውን ኃይል ማስታገስ አስፈላጊ ነው ብዬ ነው የምናገረው፤›› በማለት ገልጸው ነበር፡፡
በውጭም በውስጥም የጦርነት ሥጋት ያረገዘው የትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ ለኤርትራ ቅርብ የሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎችም ውስጥ የሥጋት ደመና ያንጃበበባቸው ይመስላል፡፡ የአማራ ክልሉ ጦርነት ገና ሳይበርድ በትግራይ በውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻዎች እርስ በእርስ ግጭት ቢፈነዳ ወይም በትግራይ ድንበር በኩል በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ቢጀመር፣ አጠቃላይ ቀጣናው ወዴት እንደሚያመራ ማንም አያውቅም፡፡ ከሶማሌ ክልል ጋር የመሬት ይገባኛል ግጭቱን ገና ያልፈታው፣ እንዲሁም ከጂቡቲ በኩል ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስተናገደ ያለው የአፋር ክልልም ቢሆን ለአሰብ ወደብ በቡሬ በኩል አዲስ ጦርነት ቢከፈት ወደ ምን ዓይነት ቀውስ እንደሚያዘግም ማሰብ ከባድ ይመስላል፡፡