የኮንጎ ወታደሮች በኤም23 ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ሲጋዙ
የምስሉ መግለጫ,የኮንጎ ወታደሮች በኤም23 ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ሲጋዙ

ከ 5 ሰአት በፊት

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኤም23 ታጣቂዎች ጋር የገባችውን ግጭት ተከትሎ ፊቷን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያዞረች ይመስላል።

የዋይት ሐውሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደሚያስቀድሙ የተረዳችው በማዕድን የበለፀገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዋሺንግተን ጋር ስምምነት ለመግባት ወጥናለች።

ትራምፕ የልጃቸው ቲፋኒ ባል አባት የሆኑትን ግለሰብ በቀጣናው የአሜሪካን ጉዳይ እንዲከታተሉ ይሾሟቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።

የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ ሀገራቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለመስማማት ዕቅድ እንዳላት እና “በጣም አስፈላጊ የሆኑት ማዕድናትን” ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አክለውም ግንኙነታቸው በማዕድናት ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን “እርግጥ ነው ስለደኅንነትም ማውራታችን የማይቀር ነው” ብለዋል።

የስምምነት ወሬ አሁን የተሰማው ለምንድነው?

ከአማጺያን ጋር እየተፋለመ ያለው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጦር ሠራዊት አደጋ ላይ ነው።

በጎረቤት ሀገር ሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም23 ኃይሎች በማዕድን የበለፀገውን ምሥራቃዊ የኮንጎ ክፍልን እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ።

ከምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጣ ጦር ኃይሎች ለኮንጎ ጦር ድጋፍ እንዲሰጡ ቢላኩም አማፂ ኃይሉን መቋቋም አልቻሉም። የኤም23 ታጣቂዎች ወደ ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል በመገስገስ ዋና ከተማዋ ኪንሻሳን የመቆጣጠር ዓላማ አላቸው።

አሁን ካለበት ሁኔታ አንፃር ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቴሼኬዲ የተለያዩ አማራጮችን መመልከታቸው የማይቀር እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

ባለፈው ወር ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ቴሼኬዲ የትራምፕ አስተዳደር ከማዕድናት ጋር በተገናኘ ፍላጎት ማሳየቱን ተናግረዋል።

አፍሪካ ዩኤስኤ ቢዝነስ ካውንስል የተባለው ድርጅት ደግሞ የኮንጎ ሴናተሮችን ወክሎ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በፃፈው ደብዳቤ “የምጣኔ ሀብት እና ወታደራዊ ጥምረት” ለመፍጠር ፍላጎት አሳይቷል።

አሜሪካ ምን ትጠቀማለች?

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 24 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ ያልተነካ ጥሬ የማዕድን ሀብት እንዳላት ይነገራል። እጅግ ውድ እና ተፈላጊ የሆኑት ኮባልት፣ ወርቅ እና ኮፐር ከእነዚህ ማዕድናት ውስጥ ይመደባሉ።

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ግዙፏ የኮባልት ማዕድን አቅራቢ ናት። ይህ ማዕድን ለጦር መሣሪያ እና ለሕዋ ምርምር እንዲሁም ለኤሌክትሪክ መኪናዎች ባትሪ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን አብዛኛው ማዕድን የሚሄደው ወደ ቻይና ነው።

ኮንጎ በሊቲየም፣ በታንታለም እና በዩራኒየም ክምችቷ ትታወቃለች። እነዚህ ማዕድናት ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው።

ምንም እንኳ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከማዕከላዊ አፍሪካ ወደ አንጎላ የሚዘረጋ መንገድ እየገነቡ ቢሆንም በዲሞክራቲክ ኮንጎ የማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ አልተሰማሩም።

ምንም እንኳ በርካታ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ቢሆንም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ “ለጊዜው ምንም የምናየውም ሆነ የምናስታውቀው ነገር የለም” ብለዋል።

ነገር ግን ትራምፕ አሜሪካ በዓለማችን ቀዳሚዋ “ከነዳጅ ውጪጭ የሆኑ ማዕድናት እና ብርቅዬ ማዕድናት አምራች መሆን አለባት” ሲሉ ያወጡትን ዕቅድ ተከትሎ ከኮንጎ ጋር መግባባት ላይ ብትደርስ የሚደንቅ አይሆንም።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ ምን ትጠቀማለች?

ሀገሪቱ ልታገኘው የምትችለው ዋነኛው ጥቅም “ወታደራዊ ግንኙነትን ማጠናከር ነው” ይላል ለማርኮ ሩቢዮ የተላከው ድብዳቤ።

“ማዕድናት የሚቀርቡበትን መንገድ ለሚጠብቁ” ወታደሮች ሥልጠና መስጠት እና ማስታጠቅ፤ አሜሪካ በኮንጎ “ስትራቴጂክ የሆኑ ማዕድናትን እንድትጠብቅ” ወታደራዊ ካምፕ እንድትቋቁም መፍቀድ እና የተባበሩት መንግሥታትን ወታደሮች በአሜሪካ ወታደሮች መተካት የሚሉት ይገኙበታል።

የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ነገር ግን ይህ ስምምነት ምን ያህል ተጨባጭ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ተንታኞች ቅሬታ አላቸው።

አሜሪካ በኪንሻሳ ወታደራዊ ካምፕ ትገነባለች ማለት ዘበት ነው የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ወታደራዊ ሥልጠና እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ደግሞ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ሒደቶች ናቸው።

ነገር ግን ለጊዜው ከሁለቱም መንግሥታት ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ የስምምነት ወሬ አልተሰማም።

ማሳድ ቦውሎስ የዋይት ሐውስ ኮንጎ የምትገኝበት የምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ አካል የሆነው የግሬት ሌክስ ልዑክ ሆነው ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቦውሎስ የማይክል አባት ናቸው። ማይክል ደግሞ የትራምፕ ልጅ ቲፋኒ ባል ነው።

ሰውዬው ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ በአረብ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች የትራምፕ አማካሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።